ውጭ ጉዳይና መደመር (ያየሰው ሽመልስ) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

ውጭ ጉዳይና መደመር (ያየሰው ሽመልስ)

1 min read

ጊዜው ጊዜ የሚሰጥ አይደለም፡፡መፍጠኑ ሳያንስ በየማለዳው በአዳዲስ ነገር ይታጀባል፡፡ስለ አንደኛው ነገር የጀመርነው ውይይት ሳይጠናቀቅ፣ሌላኛው ይከተላል፡፡በዚህም ምክንያት ከአንድ ሳምንት በፊት ጀምረነው የነበረውን በ‹መደመር› መጽሐፍ ላይ የሚደረግ ሒስ ሁለተኛው ክፍል ሳይነበብ ቀረ፡፡በቀደመው ንባብ መጽሐፉ ቆመለታለሁ ወይም ቆሜበታለሁ የሚለውን ‹መደመር› አገር በቀልነት ያላስቀመጠ፣የርዕዮተዓለም መጣረስ ያለበት፣የአገራችንን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ተቃርኖዎች ያላገገናዘበ፣ለእርሱም መፍትሔ ያላስቀመጠ፣መጽሐፉ ‹አቅላይነትን› ዋነኛ የመደመር ሳንካ  አድርጎ ቢያስቀምጠውም፣ድርሰቱ ግን የአገሪቱን ችግሮች ያቀለለና አሳንሶ የሚያይ፣እንደሆነ አስነብበናል፡፡

መደመር በራሱ ምንድን ነው የሚለውን ጥያቄ በግልጽ አላብራራውም-መጽሐፉ፡፡አንዳንዴ እሳቤ ይለዋል (ገጽ  II, IV, V, 35, 42, 44)፡፡ሌላ ጊዜ ደግሞ ማዕቀፍ ሱል ይጠራዋል( ገጽ iv)፡፡ ፍልስፍና ሲልም ደጋግሞ የገለፀባቸው ገፆች አሉት (ገጽ III,4,49, 73)፡፡መነጽር ሲልም ይበይነዋል (ገጽ 4).፡፡በዚህ መልኩ 280 ገፆችን የተጓዘው ይህ መልከ መልካም መጽሐፍ፣በመጨረሻው ክፍል የውጭ ጉዳይ ግንኙነትን ከመደመር አንፃር ቃኝቷል፡፡ይሔኛው ክፍል በ26 ገፆች (241-267) የቀረበ ነው፡፡

የመደመር መነጽር፣ለዓለማቀፉ አሰላለፍ

መጽሐፉ በውጭ ጉዳይ ምዕራፉ ላይ በቀደሙት መንግሥታት ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን በአወንታዊ ጎኖች ያስቀምጣል፡፡‹‹ሀገራችን ውዝፍ ሥራ ሳይሆን የዐቅም ክምችት ከፈጠረችባቸው መስኮች አንዱና ትልቁ የውጭ ግንኙነትና የዲፕሎማሲ መስክ ነው›› ይልና በቀደሙት መሪዎች የተሰራው የውጭ ግንኙነት ሥራ  ለአሁኑ ዘመን ‹ትልቅ ወረት ነው› በማለት ይገልፀዋል፡፡

ይሁን እንጂ ይህንን ‹ክምችት› እንዴት ማስቀጠል እንደሚቻል አይጠቁምም፡፡ይልቁንም በማይገቡ ቃላት፣በተደረቱ አገላለፆች ግራ ያጋባል፡፡ይህ ሳያንስ እርስበርሳቸው የሚጣረሱ ጉዳዮችን ያስቀምጣል፡፡‹‹የዓለም አቀፍ ግንኙነት የኃይልና የተዋረድ መዋቅር ከፍተኛ ለውጥና ነውጥ እየተስተዋለበት ይገኛል ›› (ገጽ 241) የሚለው ዐረፍተ ነገር አንብቦ ለመረዳት ካቃቱኝ አንዱ ነው፡፡‹‹ነባሩ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ሥርዓትና ተዋረድ ቢዳከምም አዲሱ የኃይል ግንኙነትና መዋቅር ገና ቅርጽ አልያዘም››(ገጽ 245) የሚለውም ባነበው ባነበው አልገባህ ያለኝ ሌላው ገለፃ ነው፡፡እንዲህ እያልን የምንዘረዝራቸው ነገሮች ቢኖሩም ለጊዜው ትኩረታችንን በይዘቱ ላይ እናድርግ፡፡

ስለ ኃያላን ሀገራት ፉክክር በሚያወራበት ክፍል ላይ (ገጽ 242) ከሶቭየትና በርሊን ግንብ መፍረስ በኋላ ‹‹ዓለማቀፋዊ መረጋጋትን በአንፃራዊ  መልኩ ያሰፈነ፣ነፃ ገበያን መሠረት ያደረገ፣የአንድ ዋልታ የዓለም ሥርዓትን ማስፈን›› መቻሉን ይገልፃል፡፡ይህ በእውነቱ የዓለምን የፖለቲካ አሠላለፍ አለመረዳት ነው፡፡የተጠቀሰው ዘመን ከፍተኛ አለመረጋጋት የሰፈነበት፣ሽብርተኝነት ያየለበት፣መንግሥታዊ ግልበጣዎች የበረከቱበት፣አሜሪካ የልብልብ ተሰምቷት ከኢራቅ እስከ ሊቢያ፣ከአፍጋኒስታን እስከ ሶማሊያ የዘመተችበት፣የእርስበርስ ጦርነቶች የተካሄዱበት፣ብዙ አዳዲስ አገራት ሲመሠረቱ በድንበር ይገባኛል የተፋጠጡበት ዘመን ነው፡፡በጭራሽ ሠላም ሰፍኗል የሚባልበት ዘመን አይደለም፡፡ሌላው ቀርቶ የመደመር ደራሲ ለሠላም ማስከበር ሥራ ዘምቻለሁ የሚሉበት የሩዋንዳ ጉዳይና፣ በሬዲዮ ኦፕሬተርነት የተሳተፉበት የኢትዮጵያ-ኤርትራ ጦርነት የተካሄደው በዚሁ ‹አንፃራዊ ሠላም ሰፍኗል› ባሉበት ዘመን ነው፡፡እናም ይህ ድምዳሜ ያልተጠናና ሀቅ ላይ ያልተመሠረተ ነው፡፡

ሌላኛው የዚህ ገለፃ ድፍረት ‹‹ነፃ ገበያን መሠረት ያደረገ የአንድ ዋልታ የዓለም ሥርዓት›› ሰፍኗል የሚለው ነው፡፡ይህ ቅልጥ ያለ የሊብራል አስተሳሰብ ተጽእኖ የወለደው አገላለጽ ነው፡፡ቻይና የዓለማችንን ሁለተኛ ግዙፍ ኢኖኖሚ በፍጥነት የገነባችውና ኮሙዩኒዝም ከተንኮታኮተ በኋላ ጠንክራ የወጣችው እነ አሜሪካ በሄዱበት የነፃ ገበያና መደመር መጽሐፍ ‹የአንድ ዋልታ የዓለም ሥርዓት› ባለው መንገድ አይደለም፡፡በለየለት የሦሻሊስት ርዕዮት ተመርታ ነው፡፡የላቲን አገሮች (እነ ብራዚል) ሚሊዮኖችን ከድኅነት አላቅቀው በዓለም ፖለቲካል ኢኮኖሚ ላይ ብቅ ያሉት ዓለም የአንድ ዋልታ ስለሆነች ሳይሆን ባለብዙ ዋልታ (Multipolar) ስለሆነች ነው፡፡

በገጽ 243 ላይ ‹‹በአሁኑ ወቅት በመደረግ ላይ ያለው የጂኦ ፖለቲካዊ ውድድሮች ላይ ርዕተዓለም ያለው ሥፍራ ተመናምኖ፣ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ማግኘት ወሳኝ የሆነበት ዓለማቀፋዊ ሁኔታ ተፈጥሯል››የሚል አገላለጽ አለ፡፡ይህ ጥቅል ድምዳሜ መሆኑ ሳያንስ በሌላኛው የዚሁ መጽሐፍ ክፍል ጋር ከተጠቀሰው ሀሳብ ጋር በቀጥታ ይላተማል፡፡

በአንድ በኩል አሁን ርዕዮተዓለማዊ የፖለቲካ ውድድሮች ከዓለማቀፍ ግንኙነት እንደወጣ ይገልጽና በሌላ በኩል ደግሞ ኢኮኖሚያዊ የበላይነት ለማግኘት የሚደረግ ሽኩቻ እንዳለ ይገልፃል፡፡ታዲያ ኢኮኖሚያዊ ፉክክሩስ ያለ ርዕዮተ-ዓለም ይሆናል እንዴ?! በርግጥ ደራሲው ርዕዮተዓለምን ባግባቡ እንዳልተረዱ ተደጋግሞ የተገለፀ ነው፡፡በዓለማቀፍ ግንኙነት ውስጥ በርካታ ርዕዮቶች አሉ፡፡ሪያሊዝም፣አይዲያሊዝም፣ሊብራሊዝም፣ሶሻሊዝም ወዘተ አሉ፡፡አገራት የውጭ ግንኙነት ሥራቸውን የሚያከናውኑት ከነዚህ በአንዱ ወይም አንዱን ከሌላው እያዳቀሉ ነው፡፡

ለምሳሌ ቻይና በማኦ ዜዱንግ ዘመን የወጣውን የውጭ ጉዳይ መርሆዋን አሁንም አልቀየረችም፡፡የውስጥ ጉዳዬ የውጭ ግንኙነት ሥራዬን ይወስነዋል ብላ የምታስብ በሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለም የምትመራ አገር ነች፡፡አሜሪካ እስከ ትራምፕ መምጣት ድረስ ሁሉንም ነገር በኃይል አሸንፈዋለሁ የምትል የሪያሊዝም አምላኪ ነበረች፡፡አሁን ትንሽ ቀየር አድርጋው መርካንታሊስት (የውጭ ኩባንያዎች/ድርጅቶች/ሰዎች እንዳይገቡ የምትከለክል) ሆናለች፡፡የBRICS አባል አገራት በልማታዊ መንግሥት የሚመሩ ናቸው፡፡እናም መደመር መጽሐፍ እንደሚለው ርዕዮተዓለም ላይ መሠረት ያደረገ ፉክክር አልተመናመነም፡፡

አስገራሚው ነገር ይህ በገጽ 243 ላይ የሰፈረው ‹ርዕተዓለም ያለው ሥፍራ ተመናምኗል› ብሎ የሚነሳው ገለፃ፣በገጽ 245 ላይ ከቀረበው ‹‹ብዙ ኃይሎች ያቀፈው የጂኦ ፖለቲካዊ ርዕዮተዓለማዊ ክርክር›› የቀይ ባሕርንና ፀጥታና ውኅደት እየጎዳው መሆኑን ከሚያትተው መከራከሪያ ጋር በቀጥታ ይጣረሳል፡፡እላይ የለም ብሎ አሁን ደግሞ አለ ይላል፡፡

በገጽ 244 ደግሞ ‹‹የተለመዱና የቆዩ ምዕራባዊ ኃይሎች ተጽእኖ የማሳደር አቅም እየተዳከመ ነው›› ይልና፣እዚሁ ገጽ ላይ ‹የሀገራትን የኢኮኖሚ ነፃነት የሚገዳደሩ ክስተቶች መፈጠራቸውን› ይገልፃል፡፡ይሄም ሌላ እርስበርሱ የሚናከስ ነገር ነው፡፡መቼም የአገራትን የኢኮኖሚ ነፃነት የሚፈታተኑት እነ ዓለም ባንክና አይኤምኤፍ ናቸው፡፡ወይም አሜሪካና የአውሮጳ ሕብረት ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህ የምዕራባዊ ኃይል አይደሉም እንዴ?!

መጽሐፉ ቋሚ ነገር ይዞ ጥልቀት ያለው ትንታኔ አይሰጥም፡፡የተዘበራረቁና ተመጋጋቢ ያልሆኑ ዐረፍተነገሮችን፣ምዕራፎችንና ገለፃዎችን የያዘ ነው፡፡በአሁኑ ወቅት ያለው ‹የሃያላን ፉክክር ከፖለቲካዊና ወታደራዊ ይልቅ ኢኮኖሚያዊ መልክ እየያዘ መጥቷል››(ገጽ 243) ይላል፡፡ ይህንን ላነበበ የመደመር ደራሲ ከቢሮአቸው 640 ኪሎሜትር ርቀት፣በጅቡቲ ባሕር ላይ የቻይና፣የአሜሪካ፣የፈረንሳይ፣የቤልጅየምና የሌሎች አገራት ወታደር የሰፈረው ለንግድ ነው ብለው አስበው ይሆን ያስብላል፡፡ቱርክና ግብጽ በምሥራቅ አፍሪቃ የሚዳክሩት በየትኛው ኢኮኖሚያዊ ፉክክር ውስጥ ለመቀጠል ነው? ለወታደራዊ ብልጫና ውድድር አይደለምን? ሩሲያና አሜሪካ በአሊፖ ላይ ደም የተፋሰሱት (ያፈሰሱት) ለየትኛው ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ነው? አሜሪካ በምትመራው የፀረ ሽብር ውጊያ ላይ እነ ሩሲያና ቻይና ያልተሳተፉት ወታደራዊ ልዕልናቸውን በሌላ መድረክ ለማሳየት አይደለምን? ይህ እንግዲህ የመደመር መጽሐፍ ሸውራራ ዕይታ ነው!

መጽሐፉ በአሁኑ ወቅት ያለውን ዓለማዊ ሁኔታ ተጽእኖ ከሚያሳድሩ ተዋንያን መካከል መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን መጥቀሱ መልካም ነው፡፡ከቀዝቃዛው ጦርነት ወዲህ የሰብዓዊ መብትና የዴሞክራሲ ተከራካሪ ነን ያሉ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት (እነ አመንስቲ፣ድንበር የለሽ የጋዜጠኞችና የሃኪሞች ማኅበር ወዘተ) በሀገራት የውጭ ግንኙነት ላይ ሚናቸውን እያሳደሩ ነው፡፡የእነዚህ ተጽእኖ ቀላል አለመሆኑን በተደጋጋሚ አይተነዋል፡፡ይህ መጽሐፍ ግን እነዚህን ተዋንያን ከኢትዮጵያ ጋር አገናኝቶ ይተነትናል ተብሎ ሲጠበቅ፣የማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃንን እንደ አንድ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተዋንያን ይወስድና ከአሜሪካ በስተቀር ሌሎች መንግሥታት የእነዚህን ድርጅቶች ባለቤቶችና አመራሮች መጠየቅ አለመቻላቸው ያስቆጨዋል፡፡ደራሲው በማኅበራዊ መገናኛብዙሃን ቅስቀሳና በዚሁ የመገናኛ ዘዴ በተመራ አመጽ ሥልጣን እንደያዙ ረስተውት፣‹ሀገራዊ ደኅንነታችን የሚፈታተን ነገር ሲገጥመን› እነርሱን መጠየቅ አልቻልንም ዓይነት ብሶት ጽፈዋል፡፡

መደመርና የኢትዮጵያ ዓለማቀፋዊ ግንኙነት

ምዕራፍ አሥራ ስድስት ኢትዮጵያ ማንንም አገር ወርራ እንደማታውቅ፣ካልነኳት የማትነካ፣አፓርታይድንና መሠል የውጭ ጭቆናዎችን እንደተቃወመች፣የባለ ብዙ መድረኮችን እንደመሠረተች፣በብዙ አገራት ውጤታማ ሠላም አስከባሪ እንዳሰማራች በሚያትቱ ተለመዱና ደጋግመን በሠማናቸው አንቀፆች ይጀምራል፡፡ገጽ 252 ሲደርስ ደግሞ ‹‹የሀገራችን አንዱ የተሰሚነት አቅም ምንጭ በቀጣናው ውስጥ ካላት የሠላም ማስከበር ሚና ጋር የተያያዘ ነው›› ይላል፡፡ይህ እውነትነት ቢኖረውም ሁሌም የማይሠራና የማያስኬድ ነው፡፡በአንድ በኩል የሠላም ማስከበር ሥራ የድሃ አገራት ተግባር ነው፡፡ሀብታም አገሮች ሰላም አስከባሪ ሲልኩ ብዙም አይታይም፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ኢትዮጵያ ሠላም አስከባሪ ስላሰማራች በዓለማቀፍ የዲፕሎማሲ መድረክ ላይ እንደማታሸንፍ ቢያንስ ያለፈው ዓመት የአፍሪቃ ሕብረት ስብሰባ (ኢትዮጵያን አብዝቶ የኮነነው መድረክ) እና በሶማሊያ ወረራ ጊዜ እነ አሜሪካ የሠሩት ሸፍጥ (ከዚያ በፊት በኮሪያም ከቦንጎም ሠላም አስከባሪ መላካችን ይታወቃል) ማሳያ ነው፡፡

‹‹የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ ፉክክርንና ትብብርን አስታርቆ የሚጓዝ ይሆናል››(ገጽ 255) ቢልም እንዴት መታረቅ እንዳለባቸው፣ማን እንደሚያስታርቃቸውና ለምን ማስታረቅ እንዳስፈለገ አያብራራም፡፡ዓለማቀፍ ግንኙነት ግን ያለ ፉክክር (በተለይ ንግዱ) አይሠራም፤ያለ ትብብርም (በተለይ የጋራ ሠላምና ፀጥታ) አይፀናም፡፡ደራሲው እዚህ ጋር የሳባቸው ግጥም መሠል አፃፃፋቸው እንጂ ትርጓሜው አይመስልም፡፡እናም ፉክክርና ትብብር ምንድን ነው የሚለውን አይበይኑልንም፡፡ይልቁንም ‹‹የመደመር የውጭ ግንኙነት እሳቤ፣እስከዛሬ በተጓዝንባቸው መንገዶች በገነባው ስም ላይ ተጨማሪ ስኬቶችን መጨመርና በማሳደግ ላይ የሚመሠረት ነው›› በማለት ይቀጥላል፡፡ምንድን ነው የሚጨመረው?ከውጭ አገራትና መንግሥታት ምንድን ነው የምንፈልገው? የሚለውን አያብራራም፡፡ከሁሉም በፊት ግን ከአሁን በፊት የነበሩት መንግሥታት በሙሉ የውጭ ግንኙነት ሥራዎችን ያከናወኑት የነበረውን በማስቀጠልና አዳዲስ በመጨመር ነው፡፡ከአጼ ቴዎድሮስ እስከ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድረስ ሁሉም ሰዎች ለአገሪቱ የውጭ ግንኙነት ሥራ አዳዲስ እሴት እየጨመሩ የመጡ ናቸው፡፡አዲስ ይጨመራል ከተባለም በመደመር ዘመን የተጀመረ አዲስ ግኝት ሊሆን አይችልም፡፡ግዴታና መሆን ያለበት እንጂ!

መሠረታዊ ስህተቶች

መጽሐፉ በተለይ የውጭ ጉዳይን በተመለከተ በርካታ የትርጓሜና የጽንሰሐሳብ ጉድለት ያለበት ነው፡፡

1ኛ-‹‹የውጭ ግንኙነት እሳቤያችን ጥቅምን ሳይሆን ግንኙነትን ያስቀደመና ችግሮችን ለመፍታት ቀዳሚው ነገር ግንኙነትን ማደስ ነው ብሎ የሚያምን ነው›› ገጽ255፡፡ይህ በመሠረታዊነት ሳይንቲስቶቹ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲን ከተረጎሙበት ብያኔ የተቃረነ ነው፡፡አንዲት አገር በዓለማቀፍ መድረክ ላይ በምታደርገው መስተጋብር ልታሳካው የምትፈልገው ጥቅም አለ፡፡እርሱም ብሔራዊ ጥቅም (National Interest) ይባላል› የሚል ነው፤የዘርፉ አጥኚዎች የተስማሙበት ድምዳሜ፡፡ የመደመር ደራሲ ግን ‹ጥቅም አናስቀድምም› ብለዋል፡፡

ይህቺ ድሃ አገር በውጭ ግንኙነት ሥራዋ ማሳካት የሚገባት፣ድህነቷን የሚቀርፍ፣ዴሞክራሲያዊን የሚያሻ  ሽል፣ ሠላሟን የሚያሰፍን ተግባር እንዳላት እሙን ነው፡፡ይሁን እንጂ ይህ ቀዳሚ ተግባር እንዳልሆነ ተጽፏል፡፡ጭራሽ ‹‹ብሔራዊ ጥቅማችንን በምክንያታዊ ንግግር ልንበይነው የምንችል ነገር ነው›› ይላል፡፡ብሔራዊ ጥቅም ሊተነተንና ተደራሽ ሊሆን በሚችል ፖሊሲ እንጂ ‹በምክንያታዊ ንግግር› ሲቀርብ ተሰምቶም ታይቶም አይታወቅም፡፡

2ኛ-መጽሐፉ በገጽ 256 ‹‹ብሔራዊ ጥቅምን በመበየን ረገድ ከሀገራዊ ብሔርተኝነት ስሜት በራቀ መልኩ ጥቅማችንን የሚያስከብር መንገድ መከተል ይኖርብናል›› ይላል፡፡እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው ጥቅስ ውስጥ ‹የምናስቀድመው ጥቅም የለም› ብሏል፡፡አሁን ደግሞ ተመልሶ ‹ጥቅማችንን ከብሔርተኝነት ርቀን ማስከበር አለብን› እያለ ነው፡፡ቅድም የለም የተባለ ጥቅም አሁን ከየት እንደመጣ ግን ደራሲው አያብራሩም፡፡እንደገና ይህንን አቋም የሚያፋልስ ገለፃ በገጽ 257 ላይ እንዲህ ተነብቧል፡፡‹‹የውጭ ግንኙነት ሥራችን ሊያተኩርባቸው የሚገቡ ዋናዋና ጉዳዮች ጎረቤት አገራትን ማስቀደምና ብሔራዊ ክብርን ከፍ ማድረግ ናቸው›› ይላል፡፡ብሔራዊነት (ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት) መነሻ ሊሆን እንደማይችል ሲገልጽ ቆይቶ እንደገና ዋና ጉዳያችን ‹ብሔራዊ ክብርን ከፍ ማድረግ ነው› ይላል፡፡ሌላኛው እዚህ ጋር ያለው እውነት ‹መደመር ከኢትዮጵያን ጥቅም ይልቅ (ገጽ 255)፣የጎረቤትን አገራትን ጥቅም እንደሚያስቀድም (257) መገለፁ ነው፡፡ደራሲው ‹የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ነኝ› እያሉ እንደዋዛ ደጋግመው የገለፁዋት ነገር እውነት ትሆን እንዴ? የሚል ጥያቄም ታጭራለች፡፡ይህ መጽሐፍ ወደ ፖሊሲ ከተቀየረ፣ኢትዮጵያ ከራሷ ይልቅ ለጎረቤቶቿ የምትሠራ ብቸኛ አገር ሊያደርጋት ይችላል፡፡

የዚህ ገለፃ ሌላኛው ስህተት ብሔራዊ ክብርንና ኩራትን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መነሻ ማድረግ ተገቢ እንዳልሆነ ማስቀመጡ ነው፡፡የትኛውም አገር የውጭ ግንኙነትን ሲፈጽም ታሪካዊና አሁናዊ ኩራቶችን፣እንዲሁም ክብርን ማዕከል አድርጎ ነው፡፡አጼ ምኒልክ የውጭ ግኑኝነት ሥራዎችን በሚኒስቴር ደረጃ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲመሩ፣በአድዋ ላይ የተቀዳጁት ድል ኩራት ሆኗቸው ነው፡፡ለዚያም ነው አውሮጳውያኑ ተሸቀዳድመው በአዲስ አበባ ኤምባሲ የከፈቱት፡፡ከዚያም በኋላ የመጡት የኢትዮጵያ መንግሥታት ይህንን ድል እንደ ብሔራዊ ክብር ይዘውት በኩራት የውጭ ግንኙነታቸውን የሰሩት ጠቃሚነቱን ስለተቀበሉት ነው፡፡ዶናልድ ትራምፕ ‹አሜሪካ ትቅደም› ያሉት ብሔራዊ ክብራቸውን ቅድሚያ ስለሰጡት ነው፡፡ሺ ጂንፒንግ የቻይናን ልዕለ ኃያል ለማስመስከር በውጭው ዓለም የሚዳክሩት ቻይናዊ ብሔርተኝነታቸውን አስቀድመው ነው፡፡ሞዲ የሕንድ ብሔርተኝነትንና ኩራትን ወደ ጎን ብለው አይደለም በዓለማቀፍ ተቋማት ላይ ቦታ ይኑረኝ እያሉ ያሉት፤ክብርና ኩራት ያላት አገር አለችኝ ብለው እንጂ!

 

3ኛ- ‹‹ወዳጅና ጠላት ብሎ ነገር የለም የሚል መርሕ የምንከተል ይሆናል›› (ገጽ 257) የሚለው ገለፃ ከተፈጥሯዊ የፖለቲካ ትርጓሜ ጋር መጣረሱ ሳያንስ፣እዚያው ገጽ ላይ ‹‹ከአጋም የተጠጋ ቁል   ቋል ሲያለቅስ ይኖራል የሚለውን መርሕ መከተል ይኖርብናል›› ብሎ ባመጣው ገለፃ ይጣፋል፡፡ወዳጅና ጠላት ከሌለ አጋምና           ቁልቋልን ምን አገናኛቸው? የሚለውን ጉዳይ አያብራራም-መደመር፡፡

ቀድሞ ነገር አንዲት አገር በዓለማቀፍ መድረክ ልታሳካው የምትፈልገውን ጥቅም የሚፃረር ኃይል ከገጠማት ያ ጠላት ነው፡፡ሄነሪ ጆንስ ‹‹በዓለማቀፍ ግንኙነት ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላትና ወዳጅ የለም›› ሲል የተናገረው፣ይህንን ጥቅም የሚገዳደር ኃይል ጠላት ሊሆን እንደሚችል ለመጠቆም ነው፡፡ለምሳሌ ግብጽ ኢትዮጵያ የምትባል አገር ከካርታ ላይም ብትጠፋ ትመርጣለች፡፡ኢትዮጵያን እንደ ብሔራዊ የደኅንነት አደጋ አድርጋ ታያለች፡፡ታዲያ ይቺን አገር ወዳጅም ጠላትም ብሎ ማለፍ ተገቢ ነው? ከዚህ በላይስ አቅላይነት ከየት ይመጣል ? ኢትዮጵያ በሃይማኖት፣በድንበር (ከሁሉም ጎረቤቶቿ ጋር አልተካለለችም)፣በሀብት (በርካታ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞች ያሏት) በሌሎችም ምክንያቶች አሁናዊና ታሪካዊ ልዩነት ያላት አገር ነች፡፡በረዥሙ ታሪኳ ውስጥም የክፉ ቀን አጋሮች (ሩሲያ፣ሜክሲኮ ወዘተ) አሏት፡፡እና ይቺ አገር ወዳጅም ጠላትም የላትም ብሎ መደምደም እንዴት ይቻላል? ግብጽን ወዳጅ፣ሳዑዲ አረቢያን አጋር የሚያደርግ ጥበብስ ምን ይሆን?ኢራንና ሳዑዲ፣እስራኤልና አረቦቹ ወዳጅም ጠላትም ሳይሆኑ የሚኖሩበት ዓለም ምን ዓይነት ይሆን?

4ኛ-‹‹ከጎረቤቶቻችን ጋር በሠላምና ፀጥታ ጉዳዮች ያለን ግንኙነት ብዙ ክፍተቶችና በእንጥልጥል የቀሩ ብዙ ጉዳዮች ያሉበት ነው›› ገጽ 259 የሚለው ገለፃ ኢትዮጵያ ቢያንስ ከጅቡቲና ከሱዳን ጋር ስትራቴጂካዊ የሠላም ሥምምነት መፈራረሟን የረሳ፣ጥቅል ድምዳሜ ነው፡፡አረቦችን በተመለከተ ደግሞ ‹‹እንደ ችግርና ታሪካዊ ጠላት ሳይሆን እንደ ዘላቂ ጎረቤትና አጋር ማየት ይገባል›› (ገጽ 260) ይላል፡፡ኢትዮጵያ ስትወረር ጠብመንጃ ሲያቀብሉ የነበሩ፣ተገንጣዮችን ሲያስታጥቁ የኖሩ፣በሃይማኖት ምክንያት ግጭት ለመፍጠር የሚታትሩ፣የሽብር ቡድኖችን የሚያስታጥቁ የአረብ መንግሥታትን ጠላት አድርገን እንዳናይ የሚመክረን መደመር መጽሐፍ፣ በምን መሥፈርት ከጠላትነት መዝገብ ማውጣት እንደሚገባን ግን አያመላክተንም፡፡

5ኛ- ይህ መጽሐፍ በኢትዮጵያዊ  (ለዚያውም በመሪ) ለኢትዮጵያዊያን አልተፃፈም እንዴ የሚያስብለው ነጥብ የሚመዘዘው ከአተያዩ ነው፡፡‹‹ሀገራዊ ክብራችንን የሚፈታተነውና ዜጎችን ለከፍተኛ ውርደትና ስቃይ የዳረገው ስደት ነው›› (260) ይልና በቀጥታ ከሀብታሟ አሜሪካ የተቀዳን ‹ዜጋ ተኮር› ዲፕሎማሲን መፍትሔ አድርጎ ያቀርባል፡፡የስደት ምክንያቱ ድህነት ነው፡፡በአገር ውስጥ ያለው ድህነት ከተቃለለ ሰው ለምን ይሰደዳል? ታዲያ ውርደቱ የሚመነጨው ከድኅነት እንጂ ከስደት ነውን? መደመር መልስ የለውም፡፡ከውጭ ወደ ውስጥ የሚመለከት ለድሃ አገር የማይሆን የተዛነፈ ዕይታ የሚሆነውም ለዚህ ነው፡፡ይልቁንም ከአጼ ቴዎድሮስ ጀምሮ የመጣንበትን ፀረ-ድህነት የውጭ ግንኙነት ሥራ ክፉኛ ይኮንነዋል፡፡

መጽሐፉ እንዲህ እያለ ይቀጥላል፡፡ ‹አንድ ሰው አልፃፈውም እንዴ› የሚያስብሉ ብዙ መጣረሶች የሞሉት ነው፡፡ ለዚህ አምድ የሚመቹትን ብቻ መረጥን እንጂ ከጫፍጫፍ እርስበርሱ እየተምታታ የሚዘልቅ ‹መልከመልካም› መጽሐፍ ነው፡፡በሁለት ክፍል ያደረግነውን ዳሰሳ በዚሁ እናብቃ!