አቶ ታምራት ላይኔን ምን ነካቸው - አቤል አድማሱ – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

አቶ ታምራት ላይኔን ምን ነካቸው – አቤል አድማሱ

1 min read
6

ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ፣ ሁሉን ቻይ አምላክ ሰላምና ጤናውን እንዲያበዛላችሁ ከልብ እመኛለሁ።

ወገኖቼ!

ታምራት ላይኔ

በሀገራችን በኢትዮጵያ ባለፉና ባገደሙ ቁጥር ያወቁና የነቁ እየመሰላቸው ከተፈጣሪ ከተሰጣቸው የአእምሮ ብቃታና ልቀት ውጭ  ውሀ ልኩን ጠብቆ እንዳልተሰራ የግንብ አጥር ላይን የማያስደስት፣እንደቁራ ጩኸት ለጀሮ የማይጥም፣ይሉኝታ ያጣ ፤ የሰውኛ አካሄድ ከመጓዝ አልፈው ከጠባብ የጽንፈኛ አስተሳሰብና ከእብሪት በመነጨ ግለኝነት ሀገርና ህዝብን ብሎም የግለሰብን ስብዕና በሚዳፈር መልኩ እንደተናዳፊ የቀትር እባብ ለመናደፍ ጊዜና ወቅቱን የሚጠብቁ በእኩይ ተግባር የሰለጠኑ ሰዎችን እያየንና ከአጸያፊ አንደበታቸው የሚወጣውን ጽንፈኛ  ቃላት እየሰማን እነሆ ዛሬ ላይ ደርሰናል። የነገውን ደግሞ አንድየ ያውቃል።

በተለይ የሚያሳዝነው ግን ፊደል ቆጥረዋል ተምረዋል የሚባሉት በየዘመኑ በተለያየ መንገድ የስልጣን እርካብ ተቆናጠው እንዳሻቸው ሲያስሩ፣ሲገድሉ፣ሲያፈናቅሉና ህዝቡ በደረሰበት ጭቆና ተማሮ ከሀገር እንዲሰደድ ሲያደርጉ የነበሩ አምባገነን ባለስልጣኖች በተሾሙበት የስልጣን ዘመናቸው ያልሰሩትንና ያልሞከሩትን ባጠቃላይ በተግባር ያላዋሉትን የሀገር ጥቅም ዛሬ እነሱ ከቦታው ተነስተው አዲስ የለውጥ አየር ሲነፍስ ከተደበቁበት ጉድጓድ ብቅ እያሉ  ከወቅታዊ ሁኔታ ጋር የሚጋጭ የተለያዩ አፍራሽ  አስተያየቶችንና ትችቶችን እየሰጡ “የአዛኝ ቅቤ አንጉዋች” ባህርያቸውን እያሳዩን መጥተዋል። ይህ አይንን በጨው አጥቦ እውነተኛና ለህዝብ አሳቢ ሆኖ መቅረብ  ለውጥን ለማደናቀፍ በቃላት የተዥጎደጎደ  (የቲዮሪ) ጋጋታ ከጠቃሚነቱ ይልቅ ከፋፋይና ስርዓት አልበኝነት እንዲስፋፋ መንገድ ከመክፈት በስተቀር  ለሀገሪቱ አሁን ላለባት ችግር የሚያስገኘው ፋይዳ የለውም።

እኛ ኢትዮጵያውያን በትውልድ ሀረጋችን በዘርና በቋንቋ የተለያየን ሳንሆን እርስ በእርሳችን ተጣምረንና ተጋምደን ሀያላን የተባሉትን ያንበረከክን በአፍሪካና በአለም ዙሪያ በጀግንነትና በሀገር ፍቅር ስሜት የታወቅን በየድርሳናቱ የተወደስን ህዝቦች ነን። ዛሬ ግዜ ያመጣብንን መሰናክል በጋራና በፍቅር እናልፈዋለን እንጅ ዘመነኞች እንደተመኙት ሀገራችን አትፈርስም። አርቆ አሳቢ በሆኑ ውድ ልጆቿ ታፍራና ተከብራ፣ በብልጽግና አድጋ አለምን የምታስንቅ ሀገር እንደምትሆን ጥርጥር የለኝም። ወርቅ በእሳት ተፈትኖ እንደሚያሸበርቅም እኛም መከራውን አልፈን ብሩህ ግዜ የምናይበት ዘመን ቅርብ ነው።

መቸም ነገርን ነገር ያነሳዋል እንዲሉ እንደ ኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ጥቅምት 2012 ዓ.ም. ጃዋር መሐመድ በተባለው የኦሮሞ ጽንፈኛ አክቲቪስት በተደረገው ከስነ ስርዓትና ከህግ የወጣ የማናለብኝነት አካሄድ ሀገሪቱ ወደማትወጣው የእርስ በእርስ ጦርነት እንድትገባና በጦርነቱም ዋና ተጠቃሚ የሚሆነው ድብቁ የጽንፈኞች ሀይል በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ባቀጣጠለው የጦርነት እሳት አስከአሁን በውል የታወቀው የ85 ሰዎችን ህይወት ሊቀጥፍ ችሏል።ያልታወቀውን ቤት ይቁጠረው።

ይህ ፍጹም የሰይጣን ወይም በምናባዊ ትርክት የጭራቅ ባህርይ የሆነው ጭፍጨፋ በአሁኑ በ21ኛው ክ/ዘመን መፈጸሙ እጅግ የሚዘገንን ከመሆኑም ባለፈ የጽንፈኞቹ ቡድን ምን ያህል በሰው አምሳል የተፈጠሩ የአጋንንት መጠራቀሚያና የዘመኑ ስልጣኔ ያልገባቸው ከእንስሳት የማይሻሉ ደንቆሮዎች እንደሆኑ ያሳያል። ይህ ደግሞ እንኩዋን እንደዘመናዊ ሰው የአውሮፓውያንን አለባበስ ሙሉ ልብስና ክረቫት ተሽቀርቅረው በየአደባባዩ በየሚዲያው ብቅ የሚሉትን የዘረኝነት አራማጆቹን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ዘር የሆንነውን ሁላችንን አንገት የሚያስደፋ የታሪክ ጥቁር ነጥብ ነው።

ውድ ወገኖቼ

ታዲያ ለዚህ ዘርና ሀይማኖት ላይ ያነጣጠረው በጥላቻና በምቀኝነት የተካሄደው ጥቃት አራማጆች ግለሰቦች እዚሁ በከተማችን ቁጭ ብለው እነሱን ተው ሰከን በሉ ብሎ ልክ ማስገባት ሲቻል በአደጋው ወቅት በሀገሪቱ ውስጥ ያልነበሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር በሴራው ተባባሪነት ለመወንጀል በየአቅጣጫው የሚሰነዘረው አስተያየትና የጠቅላይ ሚ/ሩ የአመራር ብቁ ያለመሆን ተደርጎ መታየት እጅግ አስገራሚ ከመሆኑም ባለፈ አስተያየት ሰጭዎቹ ያመለጣቸውን የስልጣን ጥመኝነት (ስኳር መላስ) በአጋጣሚው የሚያገኙት መስሏቸው ከሆነ እጅግ መሳሳታቸውን ሊያውቁት ይገባል።

ዛሬ የኢትዮጵያ ሰፊው ህዝብ በአስተሳሰብ ከነሱ ከጽንፈኞቹና ከባለስልጣኖቹ ልቆ በከፍተኛ የአስተሳሰብ ማማ ላይ እንደሚገኝ የተገነዘቡት አይመስልም።  ወደቀደመው ነገር ልመልሳችሁና በተለይ ዛሬ ይህችን አጭር ጽሁፍ ላቀርብ የተገደድኩበት ምክንያት የሰሞኑን የኢትዮጵያ ሁኔታን አስመልክቶ አቶ ታምራት ላይኔ ለጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ የላኩት ደብዳቤ ወይም አንተ አላወቅህበትምና ለኔ ተራውን ልቀቀልኝ የሚያስመስልባቸውን ጽሁፍ ጥሩ አንደበት ባለው ጋዜጠኛ ካዳማጥኩ በሁዋላ መንፈሴ ሊቀበለው የማይችል የተቃርኖ ሀሳብ ገጠመኝ። አውጥቼና አውርጀ እሳቸውን በአካል የሚያገኙዋቸው ዘመዶቻቸው ወደታወቀችው የጻድቃኔ ማርያም ጸበል ወስደው እስኪያስጠምቁዋቸውና ከያዛቸው ውሉ ያልታወቀ  የስልጣን ጥመኝነት እስኪሻላቸው ድረስ ይህች ጦማር በበራሪ እንደሚደርሳቸው አልጠራጠርም።

ውድ ወገኖቼ ይህንን ጉዳይ በአንክሮ ተመልክታችሁ ከዚህ በታች በዝርዝር ያስቀመጥኩትን የአቶ ታምራት ስብዕና የሚገልጸውንና እንዲሁም በስልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን ከፓርላማው እንዴት እንደተባረሩ ራሳቸው በአንደበታቸው በተደጋጋሚ እንደገለጹት “የስነምግባር ብልሹነት በማሳየቴ”  ኢህአደግ በኔ ላይ የወሰደውን እርምጃ ተቀብያለሁ ብለው ከፖርላማ አባልነት እንዴት እንደወረዱ የሚያሳየውን ለታሪክ የተቀመጠ ቪዲዮ ተመልክታችሁ እንዲሁም እሳቸው በጠቅላይ ሚ/ር አብይ ላይ ያቀረቡትን ገንቢ ሳይሆን አፍራሽ፣ የአንድነት ሳይሆን የከፋፋይነት አስተያየት ካዳመጣችሁና ለንጽጽር ካስቀመጥኩት የዶ/ር አብይ አህመድ በ አንድ አመት የስራ ግዜ ውስጥ የተሰሩትን አበይት ጉዳዮች ካጤናችሁ በኃላ የራሳችሁን ፍርድ እንድትሰጡ አደራ እላለሁ።

እኔ አቶ ታምራት ላይኔን ከቴሌቪዥን በስተቀር በአካለ ስጋ አላውቃቸውም፣እሳቸውም አያውቁኝም። ነገር ግን ይኸን ስል እሳቸው የስልጣን እርካብ ላይ ተፈናጠው በሚጋልቡበት ግዜ ያደረጉትን የምግባረ ብልሹ አካሄድ አላውቅም ማለት አይደለም።

ከዶ/ር አብይ አህመድ ጋር እንደ አውሮፓ አቆጣጠር July 2018 ዓ.ም ዋሽንግተን ዲሲ በመጡበት ግዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰላምና የአንድነት ጉባኤ አባል ስለነበርኩ በተለያዩ ቀናት ለ2 ግዜ ከቅርብ ርቀት በአካለ ስጋ ከማየቴ በስተቀር በግል አናግሬያቸው አላውቅም። ይህም ማለት የግል እውቂያም ሆነ ግንኙነት የለንም ማለት ነው። ነገር ግን አቶ ታምራት ላይኔም ሆነ ዶ/ር አብይ አህመድ በምወዳት አንዲቱ ሀገሬ ላይ አንዳቸው በሥልጣን ርካብ ላይ እስኪበቃቸው ጋልበው በስነምግባር ጉድለት ከስልጣናቸው የተሰናበቱ አንዳቸው ደግሞ በአሁኑ ግዜ ውጥንቅጡ የወጣን ለ27 አመታት የገማና የተበላሸ የአስተዳደርና የዘረኝነት መጥፎ በሽታን ለመቀየር ደፋ ቀና የሚሉ ናቸው።

ውድ ወገኖቼ

በዚህ ጽሁፍ በምሰጠው አስተያየት አንባቢያን ምናልባት የዶ/ር አብይ አህመድ ጭፍን ደጋፊ አድርጋችሁ ልትገምቱ ትችላላችሁ። የግምታችሁን ግላዊ መብት ልጋፋ አልችልም ነገር ግን እኔ ዶ/ር አብይን የምደግፈው በአጭሩ ይዘው የመጡትን አጀንዳ ተረስቶ የነበረውን ኢትዮጵያዊነት በዘር ከመከፋፈል ይልቅ አንድነት ከጥላቻና ከጸብ ይልቅ ፍቅርና ሰላም የህዝቦች የጋር ብልጽግና እሳቤ “መደመር” ፍልስፍና ቲዮር እጅግ ስለማረከኝ ብቻ ሳይሆን በ1 አመት የስልጣን ቆይታቸው በተግባር ያሳዩን መሬት የወረደው ተጨባጭ እውነታን በመመልከቴ ነው። ከዚህም በላይ በበዓለ ሲመታቸው ቀን በፓርላማው ላይ ቀርበው ቃለ መሀላ ሲፈጽሙ ባደረጉት ታሪካዊ ንግግር በኢትዮጵያ ፓርላማ ታሪክ ላይ ለ45 አመታት ተጠርቶ የማያውቀውን የሁሉን ቻይ አምላክ እግዚአብሄርን ስም ከመጥራት አልፈው ” እግዚአብሄር ኢትዮጵያን ይባርክ፡” የሚለው ቃላቸውን የሰማ ኢትዮጵያዊ ሁሉ እኝህ ሰው እውነትም ለኢትዮጵያ ትንሳኤ የተነሱ ለመሆናቸው ጥርጥር ሊያድርበት አይገባም

እኔ በበኩሌ

ትህትናና ፍቅርን ያሣየ

              የተናገረውን ሆኖ ይሚገኝ

የፈጠረውን እግዚአብሄርን የሚፈራና የሚያከብር የህዝብ ባለሥልጣን በኔ ዘመን አይቼ ስለማላውቅ “አቦ ብርቅ ሆኖብህ ነው!” ልትሉኝ ትችላላችሁ። አሁንም የናንተን ግምታዊ መብት አልጋፍም። ወደ ቀደመው ነገር ልመልሳችሁ! አቶ ታምራት ላይኔ ማን ናቸው? እኔ ዘረኛ ስላልሆንኩ የሳቸው የዘር አመጣጥ አይመለከተኝም

አቶ ታምራት ላይኔ በኢትዮጵያ ታሪክ የሚታወቁት የደርግ አስተዳደር ወድቆ ኢህአደግ ሀገሪቱን በተቆጣጠረበት ዘመን ነፍሳቸውን ይማርና በክቡር አቶ መለስ ዜናዊ ዘመነ መንግስት በአንድ ወቅት ለይስሙላ በተሰጣቸው የጠቅላይ ሚኒስቴር ማእረግ  የአቶ መለስን የግል ማኒፌስቶ (ፖሊሲ) ሳይበረዝና ሳይደለዝ አስፈጻሚ አካል  ከመሆን ውጭ ሀገሪቱ ወይም ወደ ፓርላማ ላመጣቸው ህዝብ የሰሩለት ፋይዳ ያለው ወይም የተመዘገበ በቂ ስራ እንዳልነበራቸውና ባንጻሩም በብልሹ ስነምግባር የታወቁ ስለመሆናቸው በአዲስ አበባና በአካባቢዋ የነበሩ ኢትዮጵያውያን  የሚዘነጉት አይሆንም። ውሎ አድሮም ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር በነበራቸው ይግል ያለመግባባትና የስልጣን ሽኩቻ ወደወህኒ ተወርውረው በእስር እንዲማቅቁ ተደርጓል።

የዚህ ጽሁፍ አላማ የአቶ ታምራት ላይኔን ከስልጣን መውረድና የታሰሩበትን ጉዳይ ዝርዝር ለመተረክ አይደለም። ነገር ግን አሁን እሳቸው የጻፉት በመጽሀፍ ቅዱስ ጥቅስ የተሽቆጠቆጠው ደብዳቤ ይዘቱ ወይም አላማው ምንድን ነው??­­

በመሰረቱ አቶ ታምራት ላይኔ በሥልጣን በነበሩበት ግዜ በእሳቸውና በመሰሎቻቸው አስተባባሪነት የመጣው ህገ መንግስት አንቀጽ 39 መሰረት የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች በዘርና በቋንቋ ተከፋፍለው እንዲኖሩ ወይም ያ ካልተስማማቸው እነሱ እንደሚፈልጉት ካልሆነ ተገንጥለው የየራሳቸውን ቁርጥራጭ ሀገር እንዲፈጥሩ የሚያስችለውን መብት አቶ ታምራት ላይኔ ከስልጣን እስኪወገዱ ድረስ በግምባር ቀደምትነት በመደገፍና ለዘር ልዩነቱ ተግባራዊነት ሌት ከቀን በመስራት ለ28 አመታት የተደረገው የኢህአደግ ጉዞ ያስገኘው ውጤት ውሎና አድሮ ሀገሪቱን ወደ መጨረሻው የመበታተን አደጋ ላይ አድርሷት ነበር።

ወገኖቼ

ይህች ቀደምት ታላቅ ሀገርን ከጥፋት ለመታደግ የአንድነት ጥሪ ይዞ የተነሳው በአቶ ለማ መገርሳ  የሚመራው (ቲምለማ) ተቆርቋሪ ኢትዮጵያውያንን ያካተተ የሀገር ማዳን ስብስብ ውስጥ የተገኙት ዶ/ር አብይ አህመድ የሀገራችን ህልውና ታሪክ በሰጣቸው የጠቅላይ ሚ/ርነት ስልጣን ላላፈው 1 አመት ያደረጉት የለውጥ መሻሻልና ያስገኙትን ውጤት መዘንጋት ወይም መካድ ጤነኛ አእምሮ ካለው ሰው የሚጠበቅ አይሆንም። ለመሆኑ አቶ ታምራት ላይኔ በየትኛው የሞራል ብቃት ተነስተው ነው “አመራሩን አላወቅህበትምና ለሚያውቅ ሰው ልቀቅ።” የሚያስመስል አንድምታ ያለው አስተያየት ሊሰጡ ቻሉ?

ለመሆኑ እሳቸው አባል የነበሩበት መንግስት እንዳደርገው በኢ-ሰብዓዊ ጭካኔ ተነሳስተው የራሳቸውን ህዝብ የጥይት ራት ማድረግ ነበረባቸው? ወይስ ተቃውሞ ሰልፍ የወጣባቸውን ህዝብ ሰብስበው እስር ቤት አጉረው ጥፍሩን እየነቀሉ ለሰሚ ዘግናኝ የሆነ ምርመራ እያደረጉ የሰው ልጅ መፈጠሩን እስከሚጠላ ድረስ ማሰቃየት ነበረባቸው?

እኝህ ጠ/ሚር እኮ ሀገሪቱን የተረከቡት በዘር፣በቋንቋ ተከፋፍላ የገማና የተበላሸ የአልጠግብ ባይ ሙሰኞች ባለስልጣናት አስተዳደር የተነሳ ሀገሪቱ በተቃውሞ እየተናጠች በነበረችበትና የልማት አውታሮች እየወደሙ ባሉበት ወቅት መሆኑ ተረሳ?

ወገኖቼ ሆይ

እኝህ ጠቅላይ ሚ/ር የስራ አጋሮቻቸው በጋራ ሌት ከቀን እየሰሩ ህዝቦቿ በጋራና በፍቅር በመከባበር በሰላም እንዲኖሩና የሀገሪቱ የብዙሀን ብሄረሰቦች የጋራ ሀገርና የልማቱ እኩል ተጠቃሚ እንዲሆኑ የሚያስችል የመደመር እሳቤ ይዘው የመጡ መሪ ከመሆናቸው በላይ በ1 አመት የስልጣን ግዜ ውስጥ እስከዛሬ በሀገሪቱ የማይታወቅ ትህትና፣ፍቅር፣ የአንድነት እስቤና የስራ ተነሳሽነት ያለው የመንግስት ባለስልጣን ሌት ከቀን ደከመኝ ሰለችኝ ሳይል እንቅልፍ አጥቶ ሳይታክት የሚሰራ መሪ አይተን እናውቃለን?

ወገኖቼ ኸረ ግፍ ይሆንብናል ! አፋችንን ሞልተን መንግስት የሰራውን ጥፋት ለመናገር ያልቻልን ሰዎች ነበርን እኮ! ያ ሁሉ እንዴት ተረሳ?! ላለፉት 27 አመታት የተጫነብንን የዘር የቋንቋና የመከፋፈል ችግር ባይኖር ኖሮ ዛሬ ከዚህ የተሻለ የሰላምና አስተማማኝ ፖሊሲ ያለበት ሀገር ልናይ እንችል እንደነበር ጥርጥር የለውም።

ውድ ወገኖቼ፡- እስኪ ለማገናዘብ ይረዳን ዘንድ ከዚህ የሚከተሉትን ባለፈው 1 አመት ያየነውን እንመስክር ፤ ከዛሬ 28 አመታት በፊት የደርግ መንግስት ወድቆ የኢህአደግ መንግስት ሀገሪቱን ሲቆጣጠር በአቶ ታምራት ላይኔ ጠቅላይ ሚኒስትነት መንግስት የወሰደው እርምጃ በሀይማኖት ጉዳዮች ላይ ጣልቃ በመግባት ነው። የመጀመሪያ እርምጃው

1ኛ. በዘመናት የኢትዮጵያ ታሪክና ባህል ከፍተኛ ድርሻ ይዛ የምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ሥርዐቷን ማፈራረስ ነው። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ሀገሪቱ በውጭ ጠላት ስትወረርና ድንበሯ ሲጣስ የሀገሪቱ የቁርጥ ቀን ልጆች በእብሪት የመጣውን ጠላት አሳፍሮ ለመመለስ ለዘመቻ ሲዘጋጅ የቤተክርስቲያኗ ካህናት ታቦተ ህጉን በማስቀደምና ከልጆቿ ጋር በመቆም አይዞህ በርታ በማለትና የጀግናውን የግል ኑዛዜ በመቀበል የቆሰለውን በመርዳት የሞተውን በመቅበር ሀገሯን የጠበቀች ታላቅ ቤተክርስቲያን ነች።

ይህች ጥንታዊት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሀገራችንን ታላቋ ኢትዮጵያ ሲያሰኛት ለኖረውና ለሚኖረው ሀይማኖተ አኩሪ ባህልና ቋንቋ ፊደልና ስነጽሁፍ ስልጣኔ የእደ ጥበባት መሰረት ሆኖ ባለአደራነቱን ጠብቃ የኖረች ልጆቿንም ምድራዊ ስነጥበብ ያስተማረች ባለውለተኛ እናት ቤተክርስቲያን ነች። እንግዲህ ይህችን ቤተክርስቲያን ነው የኢህአዲግ መንግስት ተቀዳሚ ስራ አድርጎ በመነሳት ካህናቱንና ጳጳሳቱን በጠመንጃ አፈሙዝ በማስገደድ ለጥቅምና ለኃላፊ ስልጣን የተገዙ የቤተክርስቲያኒቱን የስራ ኃላፊዎች በመጠቀም ከምዕመናን የቀረበ በማስመሰል በተቆጣጠረው የሚዲያ ማሰራጫዎች ሁሉ ፕሮፖጋንዳና ቅስቀሳ በማድረግ በወቅቱ ኢህአደግ ጠቅላይ ሚ/ር አቶ ታምራት ላይኔ በተጻፈ አንድ ነጠላ ደብዳቤ ስልጣን ላይ የነበሩትን ፖትርያርክ ከስልጣን በማውርድ በምትካቸውም በኢህአደግ መመዘኛ ታጋይ ናቸው የተባሉትን ጳጳስ ከሚኖሩበት ሀገረ አሜሪካ በማስመጣት የቤተክርስቲያኗ መተዳደሪያ ደንብ ሆኖ ለዘመናት የኖረውን የፍትሐ ነገስት ህግ በመሻር በፖትርያርክ ላይ አዲስ ፖትርያርክን እንዲመረጥ አስደረጉ። በዚህ ብቻ ሳያበቃ የቀድሞውን ህጋዊ ፓትርያርክ ብጹዕ አቡነ መርቆርዮስን በልዩ ልዩ ዘዴ በማስፈራራት ከሀገር ወጥተው እንዲሰደዱ ተደረገ። በተሰደዱበት ሀገር ኬንያ ቅጥረኛ ነፍሰ ገዳይ ተልኮ ሊገደሉም እንደነበር የማይረሳ የታሪክ ትዝታ ነው። ይህም በአሜሪካን የህዝብ ደህንነት በኩል በመታወቁም በአስቸኩዋይ ወደ አሜሪካን እንዲሄዱ ተደርጎ በሥደት ሀገር እንደሳቸው በልዩ ልዩ ማስፈራራት የተሰደዱትን አበው ሊቃነ ጳጳሳትና ካህናትን አስተባብረው የስደት ሀገር ሲኖዶስ አቋቁመው በጸሎትና በምህላ ለሀገራቸው ሲጸልዩ ቆዩ።

ታዲያ አቶ ታምራት ላይኔ በኢትዮጵያ የእስር ግዜያቸውን ጨርሰው ወደ አሜሪካን ከመጡ በኃላ በሰጡት መግለጫ ይህንን ጉዳይ እሳቸው እንደፈጸሙትና እንደመሩት ተናዘው ይቅርታ ጠይቀዋል። ታዲያ ዛሬ እራሳቸውን እንደንጹህ ቆጥረው ሰው ለመውቀስ መድፈራቸው ምን ይባላል?

እንግዲህ ይህች ከፍተኛ ታሪክ ያላት ቤተክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ ለ28 አመታት ምዕመኑ ሲያዝኑና ሲያለቅሱ የኖሩበትን የጸብ ግርግዳ ለማፍረስ በተለያዩ አስታራቂዎች ለአመታት የተሞከረው ሙከራ ሳይሳካ ቆይቶ በመጨረሻ ወደ ሥልጣን መንበር የመጡት ክቡር ዶ/ር አብይ አህመድ ቀና ኢትዮጵያውያንን መንግስታዊና ከመንግስት ውጭ የሆኑ ሰዎችን አስተባብረው ባደረጉት ያላሰለሰ ጥረት የ28 አመቱን የጸብ ግድግዳ አፍርሰው  ለሥራ ጉብኝት በሄዱበት አውሮፕላን ቅዱስ ፓትርያርኩን የሲኖዶስ አባላትንና የሰላም ጉባኤ አባላትን ሰብስበው ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ለዘመናት በአንድነት የኖረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንን ወደ ቀደመ ክብሯ እንድትመለስ በማድረግቸው በአለም ዙሪያ ያሉ የሀይማኖቷ ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ የሌሎችም ቤተ እምነቶች ምዕመናን ተደስተዋል። ታዲያ አቶ ታምራት ላይኔ ለግል ለሥልጣንና ቤተክርስቲያኗ እንድትበታተን ለሚፈልጉ የመንግስት ባለስልጣናት እወደድ ብለው ያሳደዱዋቸውን ቅዱስ ፓትርያርክ ዶ/ር አብይ ወደ እናት ሀገራቸው ወደ ቤተክርስቲያናቸው መደመራቸው መጥፎ ምግባር ይሆን? ወይስ የዶ/ር አብይ ለሰላም መቆም የአብ አስተዳደር ያለማወቅ ሆኖ ታይቷቸው ይሆን? በጻፉት ደብዳቤ ያንን ያህል ወቀሳ ያዥ ጎደጎዱት?

ውድ ወገኖቼ፡-

በሁለተኛ ደረጃ አቶ ታምራት ላይኔ የሚመሩት የኢህአደግ መንግስት ወደስልጣን ሲመጣ ከሰራቸው እኩይ ተግባር አንዱ የእስልምና ሀይማኖት ሊቃውንቱን ለሁለት በመክፈልና የተለያዩ ስም በመለጠፍ አንዳንዶቹንም ሊቃውንት ወደ እስር ቤት በማጎር ለ 28 አመታት የኢትዮጵያዊ ሙስሊሙ ህብረተሰብ በችግር ሲታመስ ይኖር ነበር። ሆኖም ዶ/ር አብይና የስራ ባልደረቦቻቸው በወሰዱት ያላሰለሰ ጥረትና ከፍተኛ አንድነትን የመፍጠር ስራ እነሆ የሙስሊሙ ህዝብ በአሁኑ ግዜ ስምምነት ላይ ደርሶ አንድ ወጥ የሆነ በምክር ቤት የሚተዳደር ጉባኤ በማቋቋም ሰላም ሰፍኖ ይገኛል። ታዲያ ይህንን አይነቱን የተቀደሰ ስራ የሚሰራን ጠ/ሚር እንዳልሰራና እንዳላዋቂ የመቁጠር አባዜ ለአቶ ታምራት ላይኔ ብቻ የተሰጠ፣ እኔ ከሌለሁበት የሚል ወጥ ረገጥ ጸባይ ምን ይሉታል?

ውድ ወገኖቼ

በ3ኛ ደረጃ ኢህአደግ ወደስልጣን ሲመጣ ከሀይማኖቶች ጉዳይ ቀጥሎ በፖሊሲ ደረጃ ነድፎ የተነሳበት ዐቢይ ጉዳይ የብሄር ብሄረሰቦችን መብት ለመጠበቅ በሚል የሀሰት ባዶ ቃል የተነሳ በአቶ ታምራት ላይኔ አጋፋሪነት የተበተነው የዘረኝነት መርዝ በሁለቱ ታላላቅ ብሄሮች አማራና ኦሮሞ መካከል መተማመን እንዳይኖር በኦሮሞውና በአማራው መካከል የእርስ በእርስ ጥላቻ እንዲፈጠር የዚህ የጥፋት ስራ ሊቃውንት የሆኑ የዘረኞችን ቡድን በማስተባበር በተዘጋጀ በረቀቀ እቅድና ፕላን ሚስጢራዊ ስልጠናን በመስጠት በአማራው ላይ ልዩ ልዩ ጥላቻን የሚቀሰቅሱ ጹፎች በማዛመት ” የአማራው ህዝብ በኦሮሞ ህዝብ ላይ ከአስተዳደር ጀምሮ የዘር ጭቆና ሲያደርግበት እንደቆየና አሁን ግዜው የበቀል እንደሆነ በአደባባይ በግልጽ በመናገር በለው ይህንን ነፍጠኛ” በማለት እስከዛሬ በታሪክ ተመዝግቦ የሚኖረውን የአርሲን፣የከፋን፣የጅማን እንዲሁም በሌሎች የኦሮሞ ክፍሎች በአማራው ተወላጅ ወይም አማራ ይመስላሉ በተባሉ ሁሉ የተደረገውን ጭፍጨፋ በማን የተፈጸመ ሆኖ ነው ዛሬ አቶ ታምራት ላይኔ ይህንን አጸያፊ የዘረኝነት ጥላቻን ለማስወገድና ሰላምን ተከባብሮ መኖርን ለመፍጠር የሚደክሙትን ዶ/ር አብይን ለመተቸት የተነሱት? ለመሆኑ ይዘግይ እንጅ የተረሳ መስሎዋቸው ይሆን?

 

ዶ/ር አቢይ አህመድ አቶ ታምራት ላይኔ በጽሁፋቸው ስለው ያቀረቡልን። ሀገር የመምራት ችሎታ የሌላቸው አድርገው ቢያቀርቧቸውም እኛግን በተግባር ያየነው የተለየ ነገር ነው እዚህ ላይ አጭር ምሳሌ ለመጥቀስ በኤርትራና በኢትዮጵያ ህዝብ መካከል የግል ጸብ ወይም ቂም በቀል ሳይኖር መሪዎቹ በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው መፍታት የሚገባቸውን ነገር ወደጎን ትተው በሁለቱ መሪዎች መካከል በተፈጠረ የኢጎ ጠባይ ወይም “አወቅሁሽ ናቅሁሽ” በተፈጠረው የድንበር ጦርነት አያሌ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን እንደተሰው የታሪክ መዝገብ ይነግረናል። እንግዲህ በዚህ ለ20 አመታት ተለያይቶ የነበረውን ሁለቱን ህዝብ በአጭር ግዜ ውስጥ በሰላም እንዲገናኙ ያደረጉና ያንንም በተግባር ያሳዩ ጠቅላይ ሚ/ር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው። ታዲያ ይህን የመሰለ የህዝቦች ሰቆቃ ሆኖ የቆየን ችግር መፍታትና የሁለቱን ሀገሮች ህዝብ እንዲገናኝ ማድረግ የችሎታና የእውቀት እጥረት ሆኖ ለአቶ ታምራት ላይኔ ታይቷቸው ይሆን?

የተከበሩ አቶ ታምራት ላይኔ!

የይቅርታና የርህራሄ አምላክ ወደሆነው የድንግል ቅድስት ማርያም ልጅ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መንግስት የሚያስገብዎትን የንስሀ ዘመን የጀመሩ መስሎኝ እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወንድምዎ እጅግ ተደስቼ ነበር በተለይ ያሳደዱዋቸውን ቅዱስ ፓትርያርክ  ተንበርክከው ይቅርታ ሲጠይቁ እውነትም እኚህ ሰው ወደ ክርስትናው ተመልሰዋል ብዬ ነበር ለካ ውሎ ሲያድር ጉድና ጅራት ወደኃላ እንዲሉ ያጠለቁት የክርስትና ጭንብል ራስዎ በአደባባይ አውጥተውታል።

እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ወገንዎ ልምከርዎና ለርስዎም ከእንግዲህ ወዲያ ስልጣን አያስፈልግዎም። ወደ ፈጣሪ የሚጠሩበት ግዜ ሩቅ ስለማይሆን “ስኳር የመላስ ምኞትዎን” ትተው አርፈው ቢቀመጡ ይመረጣል። እንደልብዎ አንዴ አሜሪካ አንዴ ኢትዮጵያ እያሉ የመኖርዎ መብትዎና የእረፍት ግዜዎን ጥሩ ጥሩ ሀገር የሚገነቡ አንድነትን የሚያጸኑ ከዘረኝነት ጸዳ ያሉ ጽሁፎችን እየጻፉ ያችን እየሸጡ ቢኖሩ ይበቃዎታል። ከዚህ ውጭ አሁን የተጀመረው አዲስ ለውጥ ምንም መስዋዕትነት ቢከፈልበትም ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድም ሆኑ ለዚህ ለውጥ፣ የጀርባ አጥንት ሆነው የሚያገለግሉ የመንግስት ባለስልጣናት መልካም የኢትዮጵያዊ አላማ ያላቸው የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ትብብር ኢትዮጵያ ታፍራና ተከብራ ትኖራለች እኛ እናልፋለን ሀገር ግን ለዘላለም ትኖራለች።

ሁሉን ቻይ አምላካችን ሀገራችን ኢትዮጵያን በውስጧ የሚኖሩትን ብሄር ብሄረሰቦች በሙሉ ይጠብቅልን።

አሜን

አቤል አድማሱ

ካናዳ ቶሮንቶ