"ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ይታወቁ የነበረው በአካል ላይ ጥቃት በማድረስ፣ አሰቃቂ የማሰቃየት ተግባር በመፈጸም ጭምር ነበረ" - ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

“ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ይታወቁ የነበረው በአካል ላይ ጥቃት በማድረስ፣ አሰቃቂ የማሰቃየት ተግባር በመፈጸም ጭምር ነበረ” – ዶክተር ዳንኤል በቀለ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር

1 min read

• ኢትዮጵያ ውስጥ ከአንድ ዓመት በፊት አዲስ የፖለቲከ ምዕራፍ ተከፍቷል። የተፈጠረውን መልካም ዕድል በመጠቀም በአገር ውስጥ የዴሞክራሲ ተቋማትን በአዲስ መልክ ለማደራጀትና ለማጠናከር ለሚደረገው ስራ የበኩሌን አስተዋጽኦ ለማበርከት የቀረበልኝን ጥሪ በበጎ መልክ ለመቀበል ወስኛለሁ።

• አሁን የደረስንበት ምዕራፍ በብዙ ትግል የተገኘ ነው። ብዙ ሰዎች ህይወታቸውን፣ ደህንነታቸውን፣ አካላቸውን፣ ንብረታቸውን ያጡበት ሂደት ነው።

• በመሆኑም በእዚህ ወቅት ያለን ሰዎች ደግሞ ይህንን ጊዜ በኃላፊነት ስሜት ተረክበን የምንችለውን አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን። ወደእዚህ ተመልሼ በእዚህ ስራ ላይ ለመሰማራት የወሰንኩትም በእዚሁ ስሜት ነው።

• የዴሞክራሲ ተቋማት ተብለው የሚታሰቡት እንደምርጫ ቦርድ፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽንና የመሳሰሉት ተቋማት ሙሉ ለሙሉ በመንግስት ስር ሆነው የመንግስት መጠቀሚያ መሳሪያ ወይንም የፕሮፖጋንዳ መሳሪያ እየሆኑ ሲያገለግሉ እንደነበሩ ይታወቃል።

• ዋናው የሚፈለገው የሰብአዊ መብት ጥሰቱ እንዲሻሻል፣ እንዲለወጥ ወይም በተደጋጋሚ እንዳይፈጸም ተገቢው የእርምት ርምጃ እንዲወሰድ ማድረግ አጥፊዎችንም ተጠያቂነታቸው እንዲረጋገጥ ማድረግ ነው። ይህንን ለማድረግ ሁል ጊዜ የግድ እያንዳንዱ ጉዳይ በሙሉ በአደባባይ መመዘገብ አለበት ማለት አይደለም።

• አሁን ባለንበት ወቅትና የፖለቲካ ምዕራፍ ሙሉ ለሙሉ ነጻ እና ገለልተኛ ነው። ይህም ማለት ለምሳሌ ኮሚሽኑን በኃላፊነት ለማስተዳደር ምክር ቤቱ አደራና ኃላፊነት ከሰጠኝ ጀምሮ ምን መስራት፣ እንዴት መስራት፣ ምን ማለት እንዳለብኝና እንደሌለብኝ የሚያዝዘኝ ማንኛውም አይነት የመንግስት ባለስልጣን የለም፣ ሊኖርም አይችልም ቢኖርም አልቀበልም። ስራችን ውስጥ ጣልቃ የሚገባ የመንግስት አካል የለም።

• አሁን ኢትዮጵያ ካለችበት የፖለቲካ ምዕራፍ አንጻር በጸረ ሽብር ሕጉ መሰረት ሊቀርብ የሚገባ ሕግ አለ ብዬ አላምንም። የኢትዮጵያ መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ደግሞ የማይሸፍናቸው የጥፋትና የወንጀል አይነቶች የሉም። ስለዚህ ተፈጽሟል ተብሎ የሚታሰብና የሚታመን በማስረጃ ሊረጋገጥ የሚችል ወንጀል ካለ በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ መሰረት ነው መታየት ያለበት።

• ከዚህ በፊት ኮሚሽኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰራ ምርመራ አካሂዶ የምርመራ ውጤቶቹንና ምክረ ሃሳቦቹን ለሕዝብ ሳይሆን ይፋ ሲያደርግ የነበረው ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለመንግስት ብቻ ነበር የሚያሳውቀው። ግን ይህ የተሳሳተ አሰራር ነበረ። በይፋ መታወቅ ያለበት ወደፊትም የምንሰራው ግኝቶች በሙሉ ይፋዊ መግለጫ ነው የሚሆኑት።

• እንዳስፈላጊነቱ ጉዳዮ ከሚመለከታቸው አካላት ጋራ የሚመለከተውን መስሪያ ቤት ኃላፊ በመጥራት በማነጋገር፣ ምክረ ሃሳብ በመስጠት፤ ጉዳዮ እንዲለወጥ እንዲሻሻል የማድረግ ስራ እንሰራለን። ከዚህ በተጨማሪም እንደየነገሩ ሁኔታ ዋና ዋና የምርመራ ግኝቶችና ውጤቶቻችን እንዲሁም ምክረ ሃሳባችንን አስፈላጊ በሆነ የሰብአዊ መብት ጉዳዮች ላይ ያለንን አስተያየት በይፋ ለህዝብ የሚገለጽ ይሆናል።

• በተለመደው መሰረት የቅድሚያ ማስታወቂያ ሳይሰጥ በድንገት በአዲስ አበባ ከተማና ከከተማ ውጪም በእስር የሚገኙ ሰዎችን ጎብኝተናል። በእዚህ ሂደት ውስጥም ስለእስር ቤቶች አያያዝና ስለተለያዮ አሳሪዎች ታስረው ስለሚገኙበት ሁኔታ ለመረዳት ጥረት አድርገናል።

• በተለይም በፖለቲካ አቋማችን፣ በፖለቲካ ስራችን፣ በአስተሳሰባችን፣ በሙያችን ጋር በተያያዘ ነው የታሰርነው እንጂ መንግስት እንደሚለው በሌላ ወንጀል የታሰርን ሰዎች አይደለንም ብለው ቅሬታ የሚያቀርቡ ሰዎች ጉዳይ በሚመለከት ጉዳያቸው ያለበትን ሁኔታ ለመመልከት ጥረት አድርገናል።

• ማረሚያ ቤቶቹም ያለቅድሚያ ማስታወቂያ ተቀብለው አስተናግደውናል። ገብተን የእስር ቤቶቹን ሁኔታም ለማየት ችለናል። የታሳሪዎች ጉዳይ በምን ሁኔታ እንደሚገኝ ለማየት ችለናል። በኮሚሽኑም ውስጥ ስልታዊ ክትትል የሚያደርገው የስራ ቡድንም በተለያዮ እስር ቤቶች አስቀድሞ ማስታወቂያ እየሰጠም ጭምር ስልታዊ ክትትል ማድረጉን ቀጥሏል።

• የሰብአዊ መብት ግንዛቤ ማስፋትም ቀጥሏል። የሰብአዊ መብት ጥሰት ደርሶብናል ብለው አቤቱታ ከሚያቀርቡ ሰዎችም የመመርመርና የማጣራት ስራዎች ቀጥለዋል።

• ሰኔ 15 ቀን 2010 ዓ.ም ከተከሰተው ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የተያዙ ናቸው የሚላቸውን የአብን የፖለቲካ ፓርቲ አመራርና አባሎችን ነበር። አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የሚገኘው የባልደራስ ምክር ቤት አባላትና ከኦነግ ሸኔ ቡድን የሚባሉትን እስረኞችን ጎብኝተናል።

• አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ከጎበኘናቸው እስረኞች ውስጥ ቢያንስ ሶስት ሰዎች በጋዜጠኝነት ስራ ላይ ተሰማርተው የነበሩ ሰዎች መኖራቸው እጅግ አሳስቦኛል (ይህ ቃለ ምልልስ የተደረገው ጥቅምት 18 ቀን ማለዳ ላይ ሲሆን በዕለቱ ታስረው የነበሩት ተፈትተዋል)።

• እርግጥ መንግስት የተጠረጠሩበት ሌላ ወንጀል አለ የሚለውን ብገነዘብም እስካሁን ተጠርጣሪዎቹ ላይ ከተደረገው የምርመራ ስራና ከተጠየቁት ጥያቄዎች አንጻር አብዛኛው ከመደበኛ ስራቸው ጋር የተገናኘ ስለሚመስል ጋዜጠኞቹ እስር ላይ መሆናቸው እጅግ አሳስቦኛል።

• ሌሎችም ታሳሪዎች የእስር ሁኔታቸው ከመደበኛ የፖለቲካ ወይንም የሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋች ስራቸው ጋራ የተያያዘ ሆኖ ከተገኘ እጅግ አሳሳቢ ነው።

• የእኔ አስተያየት እጅግ ያሳሰቡኝ ሁለት ነገሮች በአንድ ወንጀል የተጠረጠረ ሰው መንግስት ወንጀል ፈጽሟል ብሎ የሚያምን ከሆነ ወንጀሉን የመመርመር፣ የማጣራትና ተገቢውን ክስ የማቅረብ ተግባርና ኃላፊነት አለው።

• ስለዚህ አሁን ሰዎችን አስረን ምርመራ እናካሂዳለን የሚለው ከዚህ በፊት የነበረው የምርመራ ስራ እየተለመደ እንዳይሄድ አሳስቦኛል። ሁለተኛው ከታሳሪዎቹ ከፊሎቹ የፖለቲካ፣ የሚዲያና በሲቪል ማህበረሰብ ተሟጋችነት ስራ ውስጥ የሚሳተፉ ሰዎች መሆናቸው አሳሳቢ ጉዳይ ነው። ሌላው የሚያሳስበኝ ጉዳይ የጸረ ሽብር ሕጉ ለጊዜ ቀጠሮ መጠየቂያ ምክንያት መሆኑ ነው።

• ታሳሪዎች ረጅም ጊዜ አላግባብ ቆይተናል፣ እስር ቤት ደረጃውን የጠበቀ አይደለም፣ የፍርድ ቤት ሂደቱ በሚገባው መጠን እየተፋጠነ አይደለም፣ የታሰርነው አላግባብ ነው ከሚሉ ቅሬታዎች ውጪ በእስር ቤት የእዚህ አይነት የአካል ጥቃት ደረሰብን የሚል አቤቱታ አልሰማንም።

•ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ እስር ቤቶች ይታወቁ የነበረው በአካል ጥቃት በማድረስ፣ አሰቃቂ የማሰቃየት ተግባር በመፈጸም ጭምር ነበረ። ይህ ከእንግዲህ ሊፈጸም፣ ሊሰማም የሚገባው አይደለም። ይህ አንድ መሻሻል ነው።

• በሌላ በኩል ታሳሪዎች ከወዳጆቻቸው፣ ቤተሰቦቻቸው፣ ከዘመዶቻቸው፣ ከህግ አማካሪዎ ቻቸው ወይም ከሃይማኖት አባቶቻቸው ጋር በማንኛውም ጊዜ በነጻነት የመገናኘትና የመጎብኘት መብት እንዳላቸውም ተገንዝበናል ይህም ጥሩ መሻሻል ነው። መሻሻሎች አሉ ግን ደግሞ ብዙ ተግዳሮቶች እንዳሉም አይካድም።

• የእስር ቤት አያያዝ ሁኔታ በተለይ ማረሚያ ቤቶች በተቻለ መጠን ደረጃቸውን ከሚጠበቀው አለም አቀፍ መስፈርት ጋር ለማስተካከል ጥረት እየያደረጉ መሆኑን እገነዘባለሁ።

• ኢትዮጵያ ውስጥ ባለው የአቅም ውስንነት የተነሳ አብዛኞቹ ማረሚያ ቤቶችና እስር ቤቶቻችን በአለም አቀፍ ደረጃ በሚጠበቀው ልክ የተሟሉ እንዳልሆነ ይታወቃል።

• የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሊሻሻል የሚችለው የፖለቲካ ቀውሳችን እስከ ተፈታ ድረስ ነው። የፖለቲካ ቀውሱ መፍትሄ ካላገኘ የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታው አይሻሻልም።

• ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአንዳንድ ከተሞች ላይ የተከሰተው ውዝግብና አመፅ የተቀላቀለበት ነውጥ በይዘቱም በውጤቱም ትንሽ ለየት ያለ ነው።ለየት የሚያደርገውም የህግ የበላይነትን በአደባባይ የተገዳደረ ክስተት መሆኑ ነው።

• በዚህም ሂደት ቁጥራቸው ከ70 እስከ 80 የሚደርሱ ሰዎች እስካሁን ድረስ መሞታቸው ይታወቃል። ከዚህ ውስጥ ወደ 10 የሚያህሉት ከፀጥታ ሃይሎች ጋር በተፈጠረ ግብግብ በጥይት ተመተው የሞቱ ሲሆን፤ ከፍተኛ ቁጥር ግን እጅግ በሚያሳዝን ሁኔታና ግፍና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በየቤታቸው፥ በየመንገዱ ላይ በዱላና በስለት ተደብድበው የተገደሉ ሰዎች ናቸው።

• ሌሎችም ደግሞ በመቶዎች የሚቆጠሩ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ እና መካከለኛ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ናቸው። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የግለሰቦች የህዝብ የመንግስት ንብረት በእሳት ተቃጥሎ እንዲወድም ተደርጓል።

• የሃይማኖት ተቋማት ሆን ተብሎ ተጠቅተዋል፣ ወድመዋል። ስለዚህ እነዚህ ሁሉ ነገሮች ስንመለከታቸው በጣም አሳሳቢ የሆነ የስርዓት አልበኝነት አዝማሚያ ናቸው። ይህም የህግ የበላይነትን በከፍተኛ ሁኔታ ተፈታትኗል።

• ስለዚህ በዚህ ጥፋት ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተሳታፊ የሆኑ ተጠያቂነታቸው መረጋገጥ መቻል አለበት። በምርመራ ሂደት ውስጥ ንፁህ ሰዎች ተቀላቅለው እንዳይጠቁ የበለጠ ጉዳት እንዳይደርስ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባል ብዬ አምናለው።

• የሽግግር ወቅት የፍትህ አስተዳደር አራት መሰረታዊ አላማዎቹ አሉት።ባለፈው የፖለቲካ ምዕራፍ ተፈጸመ የተባለው ነገር እውነት ስለመፈጸሙ ወይም አለመፈጸሙ እውነትን ማውጣት (discovery of the truth) አንዱ ነው፣

• ፍትህን ማረጋገጥም ሌላው ዓላማው ሲሆን፤ ከባድ የሆነ የጥፋት ወንጀል የፈጸሙና በከፍተኛ ደረጃ ተጠያቂነታቸው ሊረጋገጥ የሚገባቸውን ሰዎች ተጠያቂነታቸውን ማረጋገጥ ነው።

• ጉዳተኞችን መካስና መጠገን ሶስተኛው ዓላማው ነው። አራተኛው ደግሞ ለሰብአዊ መብት ጥሰቱ ምክንያት የነበሩ ህጎችን ፖሊሲዎችን፣ልምዶችንና አሰራሮችን ማጥናትና በድጋሚ ለሰብአዊ መብት ጥሰት ምክንያት እንዳይሆኑ እንዲሻሻሉ ማድረግ ማለት ነው።

• ባለፈው የፖለቲካ ምዕራፍ ብዙ የሰብአዊ መብት ጥሰት የደረሰባቸው፣ የሞቱ ሰዎች፣ የአካል ጉዳት የደረሰባቸውና ንብረታቸው የተወሰደባቸው ሰዎች ይኖራሉ። እነዚህ ጉዳተኞች ከፊሎቹ በህይወት የሉም፤ ከፊሎቹ ግን አሁንም ያሉና የአካላዊና የስነ ልቦናዊ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ሊሆኑ ይችላሉ። ስለዚህ ጉዳተኞች መካስ፣ መጠገንና መታገዝ አለባቸውና ይህንን ማድረግ መቻል ነው።

አዲስ ዘመን ቅዳሜ በታህሳስ 22 ቀን 2012 ዓ.ም ዕትሟ በእንግዳ አምዷ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ አጠቃላይ ስለአገሪቱ ስለሰብዓዊ መብት ጉዳይ የተናገሩትን ይዛለች።

(ኢፕድ)