በዛሬው እለት ስብሰባቸውን ያካሄዱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አባቶች በስብሰባቸው ያነሷቸው – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

በዛሬው እለት ስብሰባቸውን ያካሄዱ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አባቶች በስብሰባቸው ያነሷቸው

1 min read
3

የኦሮሚያ ቤተ ክህነት እንመሰርታለን የሚሉ አካላት ያስቀመጡትን “የ30 ቀን” ቀነ ገደብ ውድቅ አድርገዋል።ጉዳዩም ከስርአተ ቤተ ክርስቲያን አንፃር የቀኖና ጥሰት የተፈፀመበት በመሆኑና ህገ ወጥም ስለሆነ አስቸኳይ ውሳኔ በሲኖዶስ መወሰን እንዳለበትም ተስማምተዋል።
መንግስት ቤተ ክርስቲያኒቷ ለጠየቀችው ጥያቄ ተገቢውን ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን፣በተለያዩ ጊዜ የመንግስት ሀላፊዎች ወደ ቤተክርስቲያኒቷ መጥተውና ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር ተነጋግረው ከሄዱ በኋላ የተስማሙባቸው ጉዳዮች እንደሚጣሱና እንዳልተፈፀሙ በማንሳት “ከእንግዲህ ከመንግስት ጋር የምናደርገው ግንኙነት ምን መምሰል አለበት?” በሚለው ጉዳይ በሰፊው ተነጋግረዋል።

በተለያዩ ሚዲያዎች አባቶች ከመንግስት ጋር ግንኙነት ለማቋረጥ እንደወሰኑ ተረጋግጧል በሚል እየተለቀቀ ያለውን መረጃ ለማጣራት ባደረግነው ሙከራ ምንጫችን እንደገለፁልን ይህን ውሳኔ መወሰን የሚችለው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በመሆኑ ብፁአን የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በአጀንዳነት ቢነጋገሩበትም ውሳኔ አልተላለፈበትም። ለሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጉዳዩን እንደሚያቀርቡትም ታውቋል።
አባቶች በስብሰባቸው “ህዝቡ ተቆጥቷል፤በጊዜ እልባት መስጠት ካልቻልን እኛም ሆንን መንግስት ልናቆመው አንችልም። በአስቸኳይ እልባት መስጠት አለብን” ብለዋል።

ከስብሰባው በኋላ የቋሚ ሲኖዶስ አባላቱ በስልክና በአካል ከፍተኛ ማስፈራሪያ እየደረሰባቸው እንደሆነና ለምእመናንም ሆነ ለሚዲያዎች ምንም አይነት መግለጫ እንዳይሰጡ ተፅእኖ እየደረሰባቸው መሆኑንም ከምንጮቻችን ለማወቅ ችለናል።
ተጨማሪ መረጃ የቋሚ ሲኖዶስ አባላት አባቶች በስብሰባቸው የአዲስ አበባ ከንቲባ ለጥያቄያችን ምላሽ እየሰጡ ባለመሆኑ በቅርቡ በአዲስ አበባ በሚካሄደው ብሄራዊ የኩራት ቀን ላይ ቅዱስ ፓትርያርኩ መገኘት የለባቸውም” በሚል ሀሳብ ላይ ጠንካራ ውይይት አድርጓል ይህንን ተከትሎም አመሻሹ ላይ መንግስት አትሌት ሀይሌ ገብረ ስላሴን ጨምሮ አቶ ብርሀን(የሀዋሳ ኦሲስ ሆቴል ባለቤት) እና አቶ አምሀ የተባሉ ባለሀብቶችን በሽምግልና ወደ ቅዱስ ፓትርያርኩ ቢልክም ቀና መልስ አለማግኘታቸውን ለማወቅ ተችሏል።

አባይ ካጠናቀረው የተወሰደ