የዓባይ ወንዝ አወራረድና የአዴፓ አሰላለፍ - ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የዓባይ ወንዝ አወራረድና የአዴፓ አሰላለፍ – ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር)

1 min read
2

የከፍታው ቀን ከሽፏል፤ የኩራቱ ቀንም ከወሬ አልዘለለም። መደመር ከአንደኛ ደረጃ ት/ቤት የሂሳብ ስሌት ውልፍ አላለም፡፡ የለውጥ ኃይል ተብየው ለውጡን ውጤታማ የማድረግ አደራውን ከመወጣት ይልቅ እንደገና ወደ ስልጣን ሽኩቻ ውስጥ ገብቷል፡፡ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ሆነ አዲሱ የክልሉ መንግስት ለክልሉ ሕዝብ ችግሮች መፍትሔ ከማፈላለግ፣ በድርጅት ስም በውስጡ የተሰገሰጉትን የህወአት ተላላኪዎችን ከማጽዳትና ከመንቀል ይልቅ ቀን እየመረጠ የራሱን ስያሜ በመሰየም በዓላትን እየጠበቀ ጽዳትና ችግኝ መትከል፣ አሸንድየ ሻዳይና ሶለል ማክበር የክልሉ መንግስትም ሆነ ድርጅቱን ከኪሳራ የሚያድነው አይደለም፡፡

ከተማ ማጽዳትና ባህልን ማልማት ህዝብና ስነልቦናን ማልማት ነው። ሁላችንም የተገነባነው ከባህሎቻችን ባገኘነው መልካም እሴት ነው። ባህል በውስጡ እሴት፣ ወግና ልማድ፣ እምነትና ሃይማኖት፣ ማህበራዊ ሚናና ደረጃን ጨምሮ የያዘ ቢሆንም ቅድሚያ የክልሉ ሕዝብ በክልሉ ተረጋግቶ መኖር፣ ሰርቶ መግባትና ወልዶ መሳም እስካልቻለ ድረስ የአገር ቆሻሻ በማንሳትና አገር ምድሩን ችግኝ ብንተክል ያውም የአማራ ደን ኢንተርፕራይዝ ድርጅት ለሚቆርጠው ደን የቱንም ያህል ብንዘክር በክልሉ መረጋጋትን አይፈጥርም፡፡

የአማራ ክልል ሕዝብ በረሃብ፣ በስደት፣ በመፈናቀል፣ በጎጥ በመከፋፈል፣ ፖለቲከኞች በሚቀሰቅሱት ግጭት እየተሰቃየ ባለበት ወቅት ከሰኔ እኩሌታ ማግስት ወደ ሥልጣን የመጣው አዲሱ የክልሉ ካብኔ እስካሁን ከጫጉላ ቤቱ (ከብሉ ናይል ኢንተርናሽናል ሪዞልት) አለመውጣቱን ስሰማ የዓባይ ወንዝ አወራረድ ታወሰኝ፡፡ በየዕለቱ ይህን ወንዝ መመልከት ከመደበኛ ሥራየ ያልተናነሰ ነው፡፡ ሰርክ በዚህ ወንዝ ድልድይ ስመላላስ የወንዙን አወራረድና የውሃ መጠን ቃኝቼ ቀና ስል በአንድ ተጀመሮ ባላለቀ ሕንጻ ተከልሎ ያለውን የቀድሞውን ብአዴን የአሁኑ አዴፓ ጽ/ቤት ስመለከት የወንዙ አወራረድ፣ የውሃ መጠን ማነስና በድርጅቱ ሥር የተጠለሉ አመራር ተብየዎች በዓይኔ ህሊናየ ሳስታውስ የአዲሱ ካብኔ ከጫጉላ አለመውጣትና ብአዴን ስሙን ከመቀየሩ ውጭ እንደ ዓባይ ወንዝ አወራረዱ መዛነፉ ብዕር እንዳነሳ አስገደደኝ፡፡

በባህር ዳር ከተማ ያለውን የዓባይን ወንዝ ላየውና ላስተዋለው የውሃው መጠን ከማነሱ በላይ አወራረዱ የተዘበራረቀና መስመር ያጣ ነው፡፡ የዓባይ ወንዝ የውሃ መጠኑ መቀነስ ምክንያቱ ለማወቅ ብጠይቅም ለጥያቄየ አጥጋቢ ምላሽ የሚሰጠኝ ባለገኝም በጅምላ ከላይ ተገድቦ ነው የሚል ምላሽ ባገኝም አዴፓም አሰላለፉን እስካሁን ያላስተካከለ ከላይ ተገድቦ ይሆን? ወይስ ድርጅቱ መስመር ተዛንፎና ቀደም ሲል ይከተለው የነበረው የወያኔ መስመር እያንገዳገደው ይሆን? ድሮውንስ መች የአማራ ሕዝብ መስመር ተከተሎ ነው ስለ መስመር የምትፈተፍተው እንዳትሉኝ አደራ ወዳጆቼ፡፡

አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት እስከታችኛው ያለውን መዋቅር ፈትሾ የለውጥ ሃይሎችን ለይቶ በድርጅቱ ባቡር ማሳፈር ሲገባው ዛሬም ድረስ ከለውጥ በፊት በሥልጣን ኮርቻ ላይ የነበሩትን አራሙቻ አመራሮችን በአሮጌ ፍርጎ አሳፍሮ መንገዛገዙ ካለፉት ዓመታትና ከቅርብ ጊዜው ከሰኔ 15ቱ የአመራሮች የእርስ በርስ ዕልቂት አለመማሩንና ወደ ለውጥ አለመግባቱን ያመላክታል፡፡

በክልሉ መንግስታዊ መዋቅር እየተፈጸመ ያለው ህገ-ወጥ ተግባር ለጆሮ የሚሰቀጥጥ ነው፡፡

ስልጣን በቅንነት የሚሸከሙት ኃላፊነት እንጅ በብልጠት የሚንጠላጠሉበት ኮርቻ አይደለም፡፡ ነገር ግን እድለኞች አይደለንምና ይህ ሆኗል፡፡ ይህንን ያልተረዳው ፖለቲካችን ደግሞ ገደል አፋፍ ላይ እንድንቆም አስገድዶናል፡፡ ዛሬም ቢሆን በግምት ከመንደፋደፍ በዘለለ በዘላቂ መሰረት ላይ ለማተኮር መጣር የሚያስፈልግ ይመስለኛል፡፡

የትናንት ችግሮች ለዛሬ ሳይተርፉ ራሳቸውን ችለው የሚያልፉ ቢሆን ኖሮ መልካም ነበረ እንደዚያ ባለመሆኑ ምክንያት ትናንት የተፈጠሩ የፖለቲካ ስህተቶች ዛሬን እንቅፋት የበዛበት ለነገ ደግሞ ደብዘዝ ያለ ዕይታ እንዲኖረን አድርገውናል፡፡ ከዚህ አኳያ የትናንትናው ኢህዴን/ብአዴን የዛሬው አዴፓ የሰራቸው ስህተቶች የአማራ ህዝብ ዛሬ ለገባበት አጣብቂኝ ግንባር ቀደም ድርሻ የነበረው መሆኑ የሚካድ አይደለም፡፡ ዛሬም ድረስ በክልሉ ሕዝብ አመኔታ በማጣቱ ዕውር ድንብሩን የሚጓዝ ደጋፊ አልባ ድርጅት መሆኑን ማሳያዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የኤርትራ መገንጠልና የአሰብ ባለቤትነት ጉዳይ፣ የኢትዮጵያን ህልውናና የህዝቦቿን ደህንነት አደጋ ላይ የጣለው የህገ መንግስት ጉዳይ፣ በህዝቦች መካከል የነበረውን መልካም ትስስር አደጋ ላይ የጨመረና የዜጎችን መብት ትቢያ ላይ የጣለ የክልሎች ህገ መንግስትና የወሰን አቀማመጥ ጉዳይ፣ በአዲስ አበባ ዙሪያ በሚታየው የፖለቲካ ጡዘትና ያለው ጣልቃ ገብነት፣ የወልቃይትና የራያ አማራነትና የቅማንት ማንነት  በመሳሰሉት ጉዳዮች…ትናንት በተሰራ ስህተት እጁ ያለበት በመሆኑ ሰርክ ሰላም የሚነሱት ይመስሉኛል፡፡

በክልሉ ህዝብ ዘንድ ተሰሚነትን ለማምጣትና ተቀባይነት ለማግኘት ከይስሙላ አጀንዳ ተላቆ ሕዝቡን ማድመጥ የድርጅት መስመሩን ካረጁና ካፈጁ  አመራሮች በማጽዳት ክልሉ ላጋጠመው ውስብስብ ችግር ተጨማሪ እዳ ከመሆን በዘለለ የመፍትሄ አካል የሚሆን በእውቀት፣ በስነ ምግባር፣ በዓላማ፣ በጠንካራ ስነ ልቦና እንዲሁም በሥራ መውደድ የታነፀ አመራር መገንባት ወሳኝ ሥራ መሆኑን መዘንጋት አይገባም፡፡ ምክንያቱም እንደ ሀገርም እንደ ዜጋም ዛሬ ፈተና ለሆኑብን ችግሮች ማለትም ስርዓት ለማበጀትና ስርዓት ለማክበር፣ ከራስ ወዳድነት የራቀ፣ ሀላፊነት የሚሸከም ተመራማሪና ፈጣሪ ማህበረሰብን ለማግኘት ትክክለኛው መንገድ ይህ ስለሆነ ነው:: ስለዚህ አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በኔትወርክ፣ በወንዝ ልጅነትና በስመ የደርጅት አባልነት እየተጠራሩ የመንግስት ተቋማትን የመውረር አባዜ በመላቀቅ የክልሉንና የሕዝቡን ችግር የሚፈቱ አመራሮች የሚሰበሰቡበት ድርጅት መሆን ይጠበቅበታል:: አዴፓ አሰላለፉን ማስተካከል ካልቻለ የሚያምነውም ሆነ የሚከተለው ሕዝብ አይኖርም፡፡ ዛሬም የሆነው ይኸው ነው፡፡

የክልሉ ሕዝብ አዴፓን አምኖ መኖር አይሻም፡፡ አካሄዱ ስንቁን እንደተቀማ መንገደኛ ጉዞውን ያቋረጠና መስቀለኛ መንገድ ላይ የቆመ ድርጅት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ደርጅቱ ሲወለድ የተጠናወተው ልክፍት መሆኑን እማኝ አያሻኝም፡፡ ካለፉት ታሪኮች መማር ያልቻለ፣ ታጥቦ ጭቃና ኮማ ውስጥ ያለ ድርጅት ነው ቢባል ማጋነን አይደለም፡፡

አዴፓ ውስጡን ከማጥራት ይልቅ ክልሉንና ሕዝቡን ችግር ውስጥ በመክተት ሕልውናን የማጥፋት ጉዞ ላይ ነው። በየደረጃው ያለው አመራር ለውጥ ለውጥ እያለ አዳራሽ ላይ ወጥቶ ቢሰብክም ሕዝቡ ሊያምናቸው አልቻለም፡፡ በሕዝብ ያልታመነ ድርጅት ደግሞ ባይሞትም ከከሰሙት አይሻልም፡፡ በድን ድርጅት፡፡

አዴፓ የመዋቅር ለውጥ ማድረግ ባለመቻሉ በከሰረ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፖሊሲ የሚዘባነኑ ሌባ አመራሮቹን አቅፎ ከቀጠለ ክልሉ ክልልና ወሰን አልባ ሕዝቡ ደግሞ  የሰቆቃና ችግር ገፈት ቀማሽ ይሆናል፤ ከዚህ ሁሉ በፊት ስልጣኑን አንቆ የያዘው አዴፓም ሆነ የክልሉ መንግስት በአዲሱ ዘመን ስር ነቀል የመዋቅር ለውጥና የተቋማት ሪፎርም በማድረግ አሰላለፉን ማስተካከል ይገባል ባይ ነኝ፡፡ አለበለዚያ “ሳያሽ የበላ ዝንጀሮ ሲስል ያድራል” ነውና ከወዲሁ ይታሰብበት እላለሁ፡፡

ድራንዝ ጳውሎስ (ከባህር ዳር)