የሰሞኑ ቋንቋን ተከትሎ የተከፈተው ዘመቻ - ህብር ራዲኦ – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የሰሞኑ ቋንቋን ተከትሎ የተከፈተው ዘመቻ – ህብር ራዲኦ

1 min read
8

የሰሞኑ ቋንቋን ተከትሎ የተከፈተው ዘመቻ የራሱን የኦሮሞን ቋንቋ ተናጋሪውን ጭምር ተቃውሞ እየገጠመው ነው።የተቃውሞው ጠሪዎች የፖለቲካ ንግድ ያደረጉት መጫወቻ በሀሰት በአፍ መፍቻ እንዳንማር ሊደረግ ነው በሚል ፈጠራ ወጣቱን ለማሳሳት ዘመቻ ከፍተው አልሰራም።አዲሱ ፖሊሲ በአፍ መፍቻ አትሟሩ አላለም።በፌደራሉ የሥራ ቋንቋ እንደ አንድ ትምህርት መሰጠቱ አትራፊ እንጂ አክሳሪ አለመሆኑን በአደባባይ መናገር የጀመሩ አሉ። ተከታዩን ጽሑፍ ሲያነቡ ብዙ ቁምነገር ያገኛሉ ሼር ያድርጉት

የጃዋር የቋንቋ ፖለቲካ አደገኛነት (Muktarovich Ousmanova)

እኔ በነገሌ ቦረና በቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከቆጠርኩ በሗላ፣ በነገሌ ትልቁ መስጊድ በተመሳሳይ ወቅት የቁርአን ትምህርት እማር ነበር። አንድ ክርስቲያን የሰፈራችን ልጅ ትልቅ መስቀሉን አንገቱ ላይ አንጠልጥሎ አጠገቤ ቁርኣን ይማር ነበር። እናቱ ነች የቁርአን የመማር አካሄድ ለልጆች የማስታወስ ችሎታን ይሰጣል በማለት ልጇን በአደራ ለቁርአን አስተማሪያችን የሰጠችው። አስተማሪውም አደራውን ተረክቦ የልጁን እምነት ጠብቆለት ከእኛ እኩል ያስተምረው ነበር። ዛሬ ያ ልጅ የእናቱን እምነት ሳይለቅ የህክምና ዶክተር ነው። እዚያው የተማረበት ቀኤ ያገለግላል።

እኔም የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል በመቁጠሬ ወደ መደበኛ ትምህርት ቤት ስገባ እሳት ተማሪ ሆኛለሁ። አንደኝነትን ተቀምቼ አላውቅም። የትምህርት ስርአቱ ወደ ኦሮምኛ ሲቀየር እኔም የቁቤ ጄኔሬሽን ሆኜ ኦሮሚኛን እያቀላጠፍኩ በመማር አንደኝነቱን ማንም አልነጠቀኝም። ተጨማሪ ውበትና እውቀት ነው የሆነኝ። በኦሮሚኛ ግጥም ውድድር እሸለም ነበር።

ሁለቱም ቋንቋዎች ጠቀሙኝ እንጂ አልጎዱኝም። ለኢትዮጵያ መቆምን በምርጫዬ የተቀበልኩት ነው። እንደኔ በአንድ አካባቢ በአንድ ትምህርት ቤት የተማረው ግርማ ጉተማም የኦሮሞ ብሄርተኝነትን መርጧል። ሁለታችንም ከአማራ ወገን የበቀሉ ምርጥ ምርጥ መምህራን አስተምረውናል። አንድም ቀን በማንነታችን የተለየ ምልከታ አይተንባቸው አናቅም። በጉብዝናችን ግን ሁሌ እንደተወደድን እና እንደተከበርን ነው የማስታውሰው።

የሰው ልጅ ውስብስብ ነው። ማንም አይጠመዝዘውም። የሚያስፈልገን ማንም የማይጨቆንበት ስርአት መገንባት ነው። ከዚያ በተረፈ ቋንቋ የመግባቢያ መሰሪያ ነው። አለቀ። ዛሬ ጉግል እንኳ ይተረጉምልናል። አለም ወደ የማንገምተው ዘመናዊነት እየገሰገሰች ነው። እነ ጃዋር ግን ወደሗላ ይመለሳሉ። የኦሮሚኛ ቋንቋን ለማሳደግ ትጋት ይፈልጋል። ቋንቋው ላይ ምርምር ማድረግ፣ ማሳደግ እና ለሌሎች ኢትዮጵያውያን እንዲዳረስ ማድረግ ይቻላል። ይህ የብዙ ጊዜ ስራ ነው። ቋንቋን የፖለቲካ ማታገያ ማድረግ ግን በዚህ የብሄር መፋጠጥ ውስጥ በህዝቦች መካከል ጥርጣሬ መፍጠር በመሆኑ ለአንድነት አይበጅም።