ለኢትዮጵያ መንግስትና ፓርላማ ፣ ግልጽ ደብዳቤ ( በደብሩ ነጋሽ) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

ለኢትዮጵያ መንግስትና ፓርላማ ፣ ግልጽ ደብዳቤ ( በደብሩ ነጋሽ)

1 min read
6

ተማሪዎችን አማርኛን ከመማር ማገድ፣ ክትባትን ከመንሳት፣ ያነሰ ወንጀል አደለም

የኢትዮጵያ የትምርት ሚኒስቴር ፣ ለ28 አመታት በኢትዮጵያውያን፣ በተለይ በኦሮሞው ወጣት ላይ ሆን ተብሎ የተፈጸመ በደል ለመቀልበስ፣ አማርኛን እስከ 6ኛ ክፍል ድረስ እንዲማሩ በመርሃ-ግብሩ ፣ ቀርጾ ማውጣቱ፣ ይበል የሚያሰኝ ነው። ካንድ ትውልድ ለበለጠ ግዜ፣ የኢትዮጵያውያንን ስብዐዊ  መብት በመንፈግ፣ በሚሊዎኖች የሚቆጠሩን ዜጎች፣ በተለይ ኦሮሞውን፣ ሆን ተብሎ አማርኛ እንድይማሩ ማድረግ፣ ከገዳይ የህጻናት በሽታ ተከላካይ ክትባትን፣ ከመንፈግ ያነሰ ወንጀል አደለም። የዚህ ግፍ ሰለባ የሆኑ ወጣቶችና ወላጆች ሃዘን፣ መንግስትን እንቅልፍ በነሳው ነበር።

ሰሞኑን ኦሮምያ የሚባለው ክልል ከፍተኛ ባለስልጣን መግለጫ፣ ከላይ የተጠቀሰውቅን የትምርት ሚኒስቴርን መርሃ ግብር የሚጥስ ነው። የትምርት ሚኒስቴሩ መርሃ ግብር፣ የተነደፈው ባለፉት 28 አመታት የወያኔና ግብረ~አበሩ ኦነግ ፣ አያሌ ሚሊየን ወገኖቻችን በተለይ ኦሮሚፋ ተናጋሪዎች ፣ አማርኛ እንድይማሩ በማድረግ ፣ ዘመን ተሻጋሪ ለሆነ ድንቁርና እንደዳረጉ እሙን ነው። የሰውዬው አቅዋም ወድያው ሊያስጠቀው በተገባ። ይህ የሆነበት ምክንያት የኦነግ  ሹማምንት ጥፋቱን ስላተረዱት አይደለም። ቢስማሙ ፣ እስካሁን ላደረሱት ኪሳራ መጠየቅ ስላለም ነው። ካፈርኩ አይመልሰኝ ይመስላል።

ለዚህ እጅግ ግዙፍ ወንጀል ዋናው ተከሳሽ ወያኔ ቢሆንም፣ አጋር የኦነግ ሹማምንትም ሆኑ ፣ የአገሪቷ ፓርላማ አባላት ከተጠያቂነት አይድኑም። ወላጅ እንኳን ለልጅ ትምርት እንቅፋት ቢሆን፣ በወንጀል ተከሶ፣ ልጆቹን እስከመነጠቅ የሚያደርስ ቅጣት ይጣልበታል።አንድን ህጻን በወጉ መንከባከብ የወላጅ ግዴታ ቢሆንም፣ የልጁን ሰብዐዊ መብት የመጣስ  መብት ፣ ማንም የለው።

በኔዘርላንድስ ፣ የዛሬ 40 አመታት ግድም፣ የልምሻ  ( ፖሊዎ ወይንም ሽባ የሚያደርግ ተላላፊ በሽታ) ወረርሽኝ ተነስቶ፣ ከ 100 በላይ ህጻናትን ለሽባነት መዳረጉ፣ አገር ያንቀጠቀጠ ጉዳይ ነበር። እጅግ በሰለጠነችና ፣ ተላላፊ በሽታን ከተቆጣጠሩ ቀደምት ሃገራት አንዷ የሆነችው ሆላንድ ይህ መከሰቱ ፣ ብርቱ የህዝብ  ቁጣ  ቀሰቀሰ። በሽታው የተከሰተው፣ በአንድ ያገሪቷ አካባቢ የሚኖሩ ፣ እምነታቸው ክትባትን በማይፈቅድ ማህበረ-ሰብ አባላት ብቻ ነበር። ሆኖም ቀደም ባሉት አመታት፣ ክትባትን እምቢ ማለት፣ የወላጅ መብት ሊሆን ይገባል ብሎ ባመነው የጠቅላይ ግዛቱ አመራር  ግድፈት፣ ያን ያህል ህጻናት ፣ ለዘለቄታ ሽባ መሆን፣ ባገሪቷ ብዙ ቁጭት ፈጥሮ ፣ ህግ አስቅይሯል።

ባጭሩ፣ ይህ የአማርኛን ትምርት በማገድ እና ህጻናቱን በማደንቆር የወደፊት እድላቸውን ማጨለም፣ ከላይ  ከተጠቀሰው ያአውሮጳዋ አገር  አሳዛኝ ተሞክሮ የሚለይ አደለም። ፈረንጆቹ ወድያው ግድፈታቸውን ሲያርሙ፣ የ 28 አመት የቆየውን የኢትዮጵያውያን ወጣት ሰቆቃ እንዲቀጥል፣  መንግስት ከፈቀደ ፣ ያገሪቱ አመራርና የመማክርቱ አባላት በውንጀል ሊከሰሱ ይገባል።  የኢትዮጵያ የትምርት ሚኒስቴር በበኩሉ፣ 28 አመትን አመታት የጥፋት ጉዞ፣ በመቀልበስ፣ ህጻናት የተነፈጉትን አማርኛን የመማር መብት ማስከበር፣ ሊያስመሰግነው ይገባል።

ዛሬ፣ ሸዋ እምብርት ላይ ተወልደው፣ አማርኛ የማይናገሩ ወጣቶች አሳዛኝ እጣ ፈንታ፣ የማንንም ኢትዮጵያዊ ህሊና  ይበጠብጣል።  ከዩኒቨርሲቲ የተመረቁ የኦሮሞ ልጆች አማርኛ ባለመማራቸው፣ በአካባቢያቸው ተወስነዋል። ሚሊዎኖች የገጥማቸውን ፈተና አገር ያውቀዋል። እነኝህ ልጆች ወደው ሳይሆን አማርኛን ያልተማሩት፣ ሆን ተብሎ መንግስት ስለነፈጋቸው ነው። በዚህም የሚጎዱት እነርሱና ዘመዶቻቸው ብቻ አደሉም። የልጆቿን ሙሉ አቅም በማጣቷ ፣ኢትዮጵያም ተጎጅ ናትና። ስለዚህ መንግስት፣ ለ28 አመታት ከፈጸመው ወንጀል፣ ከመቅጽበት ሊታቀብ ይገባል።

ስዊዘርላንድ በዐለም እጅግ የተማሩ ሰዎች ያሉባትና ፣ ከፍተኛ የነፍስ ወከፍ ገቢ ያላቸው ዜጎች አገር ናት ። ሰፊ የቆዳ ስፋትም ሆነ፣ ማዕድናት፣ ወደብ፣ የመሰለ የተፈጥሮ ሃብት የላትም። ሃብቷ፣ የዜጎቿ ብቃት ነው። ማንኛውም ተማሪ፣ ያገሪቱን ዋና ቋንቋቆች ጀርመን፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያንኛ ከ እንግሊዝኛ ጋር ይማራል። ይሄ አበረታቸው እንጂ አልጎዳቸውም። አማርኛን የመሰለ፣ ለሺህ ዘመናት ብዙሃኑን ኢትዮጵያውያንን በማገልገል ላይ ያለ፣ የዳበረ፣ የረቀቀን ቋንቋ፣ በርካታ ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ህጻናትን ፣ ከመንፈግ የባሰ  ትውልድን የሚገድል ወንጀል ምን አለ?