"በሀሳቡ የማያሸነፍ በጠመንጃ ይመካል"መ/ ሐዲስ እሸቱ (በታምሩ ገዳ /ህብር ራዲዬ) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

“በሀሳቡ የማያሸነፍ በጠመንጃ ይመካል”መ/ ሐዲስ እሸቱ (በታምሩ ገዳ /ህብር ራዲዬ)

1 min read
1

በሀሳብ የበላይነት የማያምኑ ሰዎች ሽንፈታቸውን የሚገልጹት በመሣሪያ እና በጉልበት ብቻ እንደሆነ፣ወጣቱ ትውልድም የማንም ፖለቲካ ሀይል መጠቀሚያ ሳይሆን ፣ይልቁንም ለሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አስተሳሰብ ይዞ መጓዝ አለበት ሲሉ አንድ ታዋቂ የሐይማኖት መምህር ገሰጹ።

በሐይማኖታዊ አስተምሮታቸው እና በምክሮቻቸው በበርካታ ኢትዬጵያኖች ዘንድ በተለይ ደግሞ በማህበራዊ መገናኛዎች አማካኝነት በስፋት የሚታወቁት በ ኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን(ኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን )ውስጥ የሐዲስ ኪዳን ተርጓሚ መምህር የሆኑት መጋቢ ሐዲስ እሸቱ አለማየሁ ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት በሁለት ሲኖዶስ ተከፋፍላ የነበረችው የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ወደ አንድነቷ የተመለሰችበትን አንደኛ አመትን በማስመልከት በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ አስራ አንድ አሀጉረ ስብከት ሊቀጳጳሳት በካሊፎርኒያው ግዛት፣ በሎሳንጀለስ ከተማ የምትገኘው የድንግል ማሪያም የኢ/ኦ/ተ/ቤ/ን ካለፈው ነሐሴ 2 -3 2019 እኤአ ባዘጋጀችው አንደኛው የአንድነት እና የስብከተ ወንጌል መርህ ግብር ላይ ተገኝተው ነበር።

ከህብር ራዲዬ ዝግጅት ክፍል ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት መጋቢ ሐዲስ እሸቱ በኢትዬጵያ ውስጥ ፋሽን እየሆነ የመጣው አብያተ ክርስቲያናትን መስጊዶችን እና የእምነት ተቋማትን የማቃጠል፣አገልጋዬችን እና ምእመናኖችን የመደብደብ እና የመግደል፣ንብረት የመዝረፍ…ወዘተ ምንስኤው ምን እንደሆነ ተጥይቀው ሲያስረዱ” መሃይምነት እና ድህነት ሲጋቡ የተፈጠረ ችግር ነው “ብለውታል።

መምህር ሐዲስ እሸቱ ይህን አባባላቸውንም ሲያብራሩት” በመሀይምነታቸው የተነሳ ብዙዎች ዛሬ የተቀረው አለም የት እንደደረሰ አላወቁም፣ እነዚህ ወገኖች ጭንቅላታቸው ከጎንደር ፣ ከወለጋ፣ ከመቀሌ ፣ከሃዋሳ ወይም ከጅጅጋ ….ወዘተ ያልወጣ ነው ። ስለተቀረው አለም ሊመረምሩ አይደለም አይምሯቸው ከቤታቸው ጣሪያ በታች የሆኑ ብዙዎች አሉ።እነዚህ ወገኖቻችንን ማስተማር ያስፈልጋል፣እኔ ቤ/ክርስቲያን እንዲቆረቆርልኝ ስሻ የሙስሊሙን ፣የፕሮቴስትንቱን ፣የካቶሊኩን ሆነ የሌላው አማኝ ተመሳሳይ መብት እንዳለው ጠንቅቄ ማወቅ አለብኝ። ሁልጊዜ የሚያስተሳስረን ጉዳይ ሀይማኖት፣ ፖለቲካ ፣ዘር ሳይሆን ሰው የመሆናችን ትልቁ ምስጢር መሆን አለበት ” በማለት በመድረኮች ላይ ከመወነጃጀል በሚያግባቡ ጉዳዬች እንዴት በጋራ መቆም እንደሚቻል ገልጸዋል ።

መጋቢ ሐዲስ በማያያዝም ሰዎች ከተራቡ ፣ከተጠሙ እና ከታረዙ ምንም ነገር ከመፈጸም ወደኃላ እንደማይሉ የጠቆሙ ሲሆን ድህነት የሚወገድበት መንገድ መቀየስ ተገቢነቱን እና ቅድሚያ ሊሰጠው እንደሚገባም ጠቁመዋል።

ፖለቲካው እና ድህነቱ ስላላቸው መጣመር ለቀረበላቸው
ተከታይ ጥያቄም ሲመልሱ”በሀሳብ ገበያ ማሸነፍ የማይችሉ ፣ብከራከር ሀሳቤ ተቀባይነት ያጣል ብለው የሚፈሩ ሰዎች የጭንቅላታቸውን ባዶነትን በጉልበት ለመሙላት ይሞክራሉ ። እነዚህ ወገኖች ሁልጊዜ መመኪያቸው የሚያደርጉት ዱላ እና ጠመንጃ እና ጉልበት ብቻ ነው። የሚያሳዝነው ነገር ይህ አይነቱ አካሄድ ለእነርሱ ሆነ ለደጋፊዎቻቸው አትራፊ ሀሳብ አይደለም።ዛሬ በምእራቡ አለም የሀሳብ የበላይነት ስለሰፈነ አለምን በቅጽበት ሊያጠፋ የሚችል ኒውክሌየር የሚያህል ክፉ የጦር መሳሪይን በመጋዘናቸው ቆልፈው እየተወያዩ ናቸው።የጦር መሳሪያ የሰው ልጆችን ይፈጃል ፣ መልካም ሀሳብ ግን አለምን ይገነባል” በማለት ምክራቸውን አካፍለዋል።

በስተመጨረም የፖለቲካው ሆነ የሀይማኖቱ ማረፊያ ለሆነው ለወጣቱ ትውልድ ምን መልክት እንደሚያስተላልፉ ለቀረበላቸው ጥያቄም”ወጣቱ ለሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚመጥን አስተሳሰብ ይድረሰው፣ እንደ እየ እምነቱ ይኑር ፣ ለህግ ተገዢ ይሁን ፣ወጣት ለምንም ነገር የተጋለጠ ነው፣ ወጣቱ በአስተሳሰቡ ፣በጉልበቱ ያልሰከነ ሊሆን ይችላል።ወጣቱ ሀይማኖት የሚያዘውን መፈጸም ይጠበቅበታል፣ለውጥ የሚመጣው ፣አገር የሚያድገው በመደባደብ ፣በመገዳደል፣ንብረት በማውደም ሳይሆን በስራ እና በእውቀትብቻ ነው።ዛሬ እነ ቻይና የአለምን ኢኮነሚን እየዘወሩት ያሉት በእውቀት ነው።እነ አሜሪካ ሀያላን የሆኑት በኒውክለር ብቻ አይደለም በእነ ሆሊዊድ፣ማይክሮ ሶፍት፣በእነ ቦይንግ፣በሚዲያዎቻቸው ..ወዘተ ጭምር ነው። የአሜሪካው መከላከያ ተቋም(ፔንታጎን) ከሚያስወነጭፈው ሚሳየል ሆሊዊድ የሚያሰራጨው ሲኒማ አለምን ያተራምስላቸዋል.።ስለዚህ የእኛም አገር ወጣቶች ጭንቅላታቸውን ለበጎ ነገር መጠቀም አለባቸው፣የማንም ፖለቲከኛ ሀሳብ መስጫ ሳጥን መሆን አይገባቸውም፣ ወጣቱ ማንም እንደቀደደው የቦይ ውሃ ወደ ቀኝ ፣ወደ ግራ እየፈሰሰ አገሩን ለጥፋት ፣እርሱንም ለአደጋ ማጋለጥ የለበትም ” ሱለ መክረዋል።

(በታምሩ ገዳ /ህብር ራዲዬ)