ኮ/ሌ መንግስቱ ኃ/ማርያም ፣ዶ/ር አብይ አሕመድ...(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዬ) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

ኮ/ሌ መንግስቱ ኃ/ማርያም ፣ዶ/ር አብይ አሕመድ…(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዬ)

1 min read
1

ጋሳን ቻርቤል ይባላል ፣በሙያው ጋዜጠኛ ሲሆን ውልደቱ እና እድገቱ በእርስ በርስ ጦርነት አበሳዋን ያየቸው ፣ያም ጠባሳ ዛሬ ድረስ ካለቀቃት የመካከለኛው ምስራቅ አገር ሊባኖስ ነው።
ጋዜጠኛ ጋሳን መቀመጫውን ለንደን/እንግሊዝ በደረገው እና እለታዊው አል ሻሪክ አልዋሳት ጋዜጣ ላይ ሰሞኑን ኢትዬጵያን በድሮ እና በዘንድሮ ለመቃኘት ሞክሯል። በአሁኑ ወቅት ለጋዜጣው በዋና አዘጋጅነት የሚሰራው ጋሳን በቀደመ ጊዜ እኤአ 1980ዎቹ አጋማሽ በኢትዬጵያ ስሜናዊ ክፍል በተለይ ኤርትራ ውስጥ ከሻቢያ ጋር ይደረግ የነበረው ውጊያን እንዲታዘቡ (እርሱ ከሊባኖሱ ከአን ናሃር ጋዜጣ )ጨምሮ የተወሰኑ የውጪ አገር ጋዜጠኞች በሻቢያ ጋባዥነት ወደ አካባቢው በመጡበት ወቅት ጦርነቱ ፣ረሀቡ እና ስደቱ በሰዎች ላይ ያሳድር የነበረውን አሳዛኝ ገጠመኝን በአይኑ ለመመልከት መቻሉን ያወሳል።

ጋዜጠኛ ጋሳን በበረሃ ቆይታቸው ለእርሱ እና ለጓደኞቹ ይቀርብላቸው የነበረው ምግብ እና መጠጥም ነፍስን ለማቆያ ያህል እንጂ እርሱ የሚያውቀው እውነተኛ ምግብ እና መጠጥ እንዳልነበር ይናገራል። በኢትዬ- ሱዳን ድንበር አቅራቢያ ከሚገኝ አንድ የስደተኞች መጠለያ ካምፕ ውስጥ ሰዎች በረሀብ የመሞታቸውን ዜናን ያዳመጠው የአለም ማህበረሰብ ዝምታን መምረጡን ለማመን የከበደው የያኔው ወጣቱ ጋዜጠኛው ጋሳን ” አለማችን ከዚህ የከፋ ሰቆቃን በዝምታ እያስተናገደች ስለመሆኗ የጋዜጠኝነት ሙያዬ በሚገባ አስተምሮኛል” ባይ ነው።

ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማሪያምን በአጭሩ ሲገልጻቸው:-

ጋዜጠኛው ጋሳን ኢትዬጵያን ለአስራ ሰባት አመታት የገዙት ኮ/ል መንግስት ኃ/ማርያምን በተመለከተ ሲገልጻቸው” ለሰላዬች፣ለከሀዲዎች ፣ለተቀናቃኞቻቸው፣ለተገንጣዬች ወይም ለሚቃረኗቸው ትእግስት ወይም ርህራሄ የሚባል ስሜት የሌላቸው እና ለቀድሞዋ ሩሲያ በአፍሪካ አህጉር ውስጥ ታማኝ ወኪል የነበሩ መሪ “ሲል የ ሰማኒያ ሁለት አመቱ ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያምን ያወሳቸዋል ።

የችግኞች ተከላ ፓለቲካው እና ተስፋዎች:-

ሰሞኑን ከአንዲት ኢትዬጵያዊት ጋር በአጋጣሚ ለመገናኘት እድል የገጠመው የ አልሸሪክ አልዋሳት ጋዜጣ ዋና አዘጋጁ ጋሳን በጨዋታቸው መካከል ሙያው ምን እንደሆነ ከኢትዬጵያዊቷ ጥያቄ ይቀርብለታል፣ እርሱም ማንነቱን ሳይሸሽጋት ይነግራታል ። እርሷም የተንቀሳቃሽ ሞባይል ስልኳን ከፍት በማድረግ “ይህንን ምስል ተመልከት” ስትል ትጋብዘዋለች።

ጋዜጠኛ ጋሳንም እንዲመለከት የተጋበዘው ምስልን ሲመለከት ባለፈው የካቲት 2019 እኤእ ተካሄዶ በነበረው በስዊዘርላንድ የአለም የኢኮነሚ ፎረም ላይ በመድረክ ላይ ያያቸው ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድ ኢትዬጵያ ውስጥ ሰሞኑን” በአረንጓዴ ዘመቻ” ላይ ችግኞችን ሲተክሉ የሚያሳየውን ምስል ይመለከታል። ያቺ ኢትዬጵያዊትም ቀጠል በማድረግ “አየህ የእኛ መንግስት በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ 350 ሚሊዬን ችግኞችን ለመትከል ችሏል ” በማለት በኩራት ትገልጽለታለች።

ጋዜጠኛው ጋሳን ቻርቤል እየወደቁ እና እየፈራረሱም እንደ መልካም ስኬት እና ጀግንነት ከሚቆጠርባት ከሊባኖስ አፈር የበቀለ በመሆኑ ብዙ መሰል ልማታዊ ነክ ዜናዎችን በቶሎ ለማመን እንደሚቸግረው ይገልጻል።ተሞክሮውንም በምሳሌ ሲያስረዳ “በአገሬ ሊባኖስ ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ ችግኞችን ለመትከል በብሔራዊ ደረጃ የጦፈ ክርክር ይደረጋል፣ ችግኞች የሚሰራጩባቸው አካባቢዎች(ክልሎች) እና የችግኝ ግዢው ውጪም ቢሆን አንገብጋቢ እና አነጋጋሪ ጉዳይ ሲሆን ለችግኝ ተከላ የሚደረጉ ውይይቶች በአብዛኛው በስኬት ሳይሆን በይደር ይታለፋሉ።ከዚህ አኳያ ከአረንጓዴነት በረሃማነትን የመረጥን እንመስላለን ” ሲል የፈረሰች ሪፖብሊክ የሚላት የአገሩ ሊባኖስን ችግሮችን ለመግለጽ ይሞክራል።

“ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድን እንዴት እገኘሻቸው?”:-

ጋዜጠኛው ጋሳንም በድንገት ያገኛት ያቺ ኢትዬጵያዊት በአገሯ ጉዳይ ንቁ ተሳታፊ መሆኗን ለተገፉ እህቶች መብት መከበር የምትሞግት እና መረጃዎችን የምታሰራጭ (በዘመኑ አጠራር አክቲቪስት) መሆኗን አለመጠርጠሩን እና የማህበራዊ ድህረ ገጾች በሰዎች እለታዊ ህይወት ውስጥ ሳይቀር ያመጡትን (አሉታዊ/አውንታዊ)ለውጦችን ከግንዛቤ ውስጥ በመክተት እርሱም ለመሆኑ ጠ/ሚ/ር አብይ አሕመድን እንዴት ትመዝኛቸዋለሽ ? ሲል ሙያዊ ጥያቄ ያቀርብላታል ። ኢትዬጵያዊቷም እህት የሰጠችው ምላሽ” ጠ/ሚ/ሩ ዘራቸው ከኦሮሞ ብሔር ይሁን ፣ከአማራ አለዚያም ከ ትግራይ …ወዘተ እኔ ብዙም እይጨንቀኝም።ሀይማኖታቸውም እንዲሁ።ለእኔ ትልቁ ጥያቄ በድህነት ፣በፍትህ እና በሰላም(ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነትን ጨምሮ በእነዚህ ጉዳዬች ዙሪያ ያላቸው አቋም ላይ ነው”ስትል የግል አቋሟን ገልጻለታለች።

እንግዳው በሩን እያንኳኳ ነው?:-

ተፈጥሮ ሳትበድላቸው በእኔ ልብለጥ የፖለቲካ ቁርቋሶ ፣የእርስ በርስ ጦርነቶች እና የጎሳ ተኮር ግጭቶች …ወዘተ ሳቢያ ሰላማዊ እና ምስኪኒን የማህበረሰቡ ክፍልን ለ ከፋ ረሃብ ፣ለእርዛት እና ለሞት ሲዳርገው በቆየው እና አሁንም በሚገኘው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢን(ኢትዬጵያ እና ሱዳንን ጉዳይን ከዚህ ቀደም በግንባር ተገኝቶ የታዘበው) እና ላለፉት ሶስት አመታት የአልሻሪክ አልዋሳት ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ የሆነው ጋሳንም በአካባቢው “ተስፋ” የተባለ ለረጅም ጊዜያት ተረስቶ የነበረ እንግዳ በሩን በማንኳኳት ላይ እንደሚገኝ፣በኢትዬጵያም ቢሆን የተጀመረው የሽግግር ሂደት እውን ከሆነ ፣ለዜጎች ሰብአዊ መብት መከበር፣ዳቦ እንዲበሉ፣ህክምና እንዲያገኙ የሚያስችል አገዛዝ ከመጣ በአገር ቤት የሚኖረው ዜጋ ብቻ ሳይሆን በስደቱ አለም የሚባዝነው (ዲያስፖራው)ጭምር ወደ አገሩ ጥሬቱን እንዲልክ እንደሚያደርገው እና ብዙዎችም “እንግዳ የሆነው ተስፋን” እቅፍው እና ድጋፈው እንደሚቀበሉት ምኞቱን እና ተስፋውን ሰንዝሯል።

(በታምሩ ገዳ/ህብር ራዲዬ)