የችግኝ ተከላ የሚደገፍና አቅሙ ካለ በቀጣይነት መሠራት ያለበት ለመሆኑ ከጥያቄ አይገባም . . - (ኢትዮጵያችን) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የችግኝ ተከላ የሚደገፍና አቅሙ ካለ በቀጣይነት መሠራት ያለበት ለመሆኑ ከጥያቄ አይገባም . . – (ኢትዮጵያችን)

1 min read

የአንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ (ኢትዮጵያችን) ልሳን

ኢትዮጵያችን ቅጽ 3 ቁጥር 9                                                 ነሐሴ 04 ቀን 2011 ዓ.ም.

ለእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ . . .

የድምጽ ቅጂውን ለማድመጥ እዚህ ይጫኑ

የሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. በመላ ሀገራችን የተካሄደው የችግኝ ተከላ የሚደገፍና አቅሙ ካለ በቀጣይነት መሠራት ያለበት ለመሆኑ ከጥያቄ አይገባም። በ28 ዓመት የወያኔ/ኢሕአዴግ አገዛዝ “ደን ተቃጠለን” ሲሰማ የኖረ ጆሮ ዛሬ በጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ መሪነት የተካሄደው የችግኝ ተከላና የታየው ሕዝባዊ ተሳትፎ ሊቃኝ ይገባዋል። ካልተሳሳትን 350 ሚልዮን ችግኝ በ12 ሰዓት ተከላ ከሀገሪቷ አቅም፣ ከሎጂስቲክ አቅርቦት አንፃር የተለያዩ ጥያቄዎች ቢያስነሳና እንዴት? ቢባልም በአጭሩ ሕዝቡ የሀገር ፍቅሩን አሳይቶበታል። ዘር ሳይለይ የሀገር ችግኝ በአንድነት ተክሏል።

የችግኝ ተከላ ዘመቻ ሙሉ ለሙሉ የሚደገፍ ጅማሮ ነው። የጉዳዩ አሳሳቢነት ትኩረት ማግኘቱ እራሱ ይበል የሚያሰኝ ነው። በተለይ እንደ ኢትዮጵያችን ላለች ድሃና በተደጋጋሚ በአየር ንብረት መዛባትና ተያይዞም በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ድርቅና ችጋር በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝቧ የሚሰቃይባት ሀገር፣ በምግብ አቅርቦትም እራሷን ባለመቻሏ በውጪ ሀገራት ምፅዋዕትና ዕርዳታ ለምትተነፍሰው ሀገራችን የደን ማልማት ሥራ አስፈላጊ ብቻ ሳይሆን የህልውናም ጥያቄ ነው።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና ግብርና ድርጅት ያሠፈረውን ሃቅ ማየት ብቻ የደን ልማት ሥራው ምን ያህል አሳሳቢ መሆኑን ለመገንዘብ ይረዳል። የኢትዮጵያችን የመሬት የቆዳ ስፋት ብቻ 100 ሚሊዮን ሄክታር ወይም 1 ሚሊዮን ካሬ ኪሎ ሜትር ነው። በፈረንጆቹ 2016 በእኛ 2008/9 ዓ.ም. ከዚህ ውስጥ በደን የተሸፈነው 13 ሚሊዮን ሄክታር (130 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር) ወይም 13 በመቶ ብቻ ነው። ለእርሻ የሚውለው 36 ሚሊዮን ሄክታር (360 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር) ነው። ሌሎችም ዓለም አቀፍ ተቋማት ያሰፈሩት መረጃ ደግሞ አስደንጋጭ ነው። ይኸውም ከ1983 እስከ 1998 (በፈረንጆቹ  ከ1990 እስከ 2005) ባሉት የኢሕአዴግ አስተዳደር 15 ዓመታት ውስጥ  ብቻ የደረሰው የደን ጥፋት ከነበረው 14 በመቶ ወይም 2.1 ሚሊዮን ሄክታር (21ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር) ነው። በሌላ አነጋገር በአማካይ በየዓመቱ 140 ሺ ሄክታር (1 ሺ 400 ካሬ ኪሎ ሜትር) ደን ሲጠፋ ነበር ማለት ነው። የደን ጥፋቱን ለመረዳት ያህል ይህ መረጃ የሚነግረን ወርዱ 35 ስፋቱ 40 ኪሎ ሜትር የሆነ ደን በየዓመቱ እየጠፋ እንደሆነ ነው።

የኢትዮጵያችን የደን ሽፋን ከላይ እንደተጠቀሰው ከመሬት ብቻ የቆዳ ስፋቱ ተመናምኖ 13 በመቶ ወይም 13 ሚሊዮን ሄክታር (130 ሺ ካሬ ኪሎ ሜትር) ብቻ ሆኗል። እጅግ የሚያስደነግጠው ይህ የደን መመናመን ብቻውን ሳይሆን የመመናመኑ የፍጥነት መጠን ነው። ይህ ካልተገታና በተቃራኒው አቅጣጫው ወደ ደን ማልማትና ማስፋፋት ካልተቀየረ የደን መመናመኑን ማስቆም ወይም መቀልበስ የማንችልበት አስከፊ የታሪክ ምዕራፍ ላይ መድረሳችንና ኢትዮጵያችንም ከቻድና ከደቡባዊ ሱዳን  ወደታች እየተስፋፋ ባለው የሰሐራ በረሃ መዋጥ የጊዜ ጉዳይ ነው።

የደን መሬት ሽፋን መመናመን የሚሄድበት ፍጥነትና አብሮም የኢትዮጵያችን ሕዝብ ብዛት የሚጨምርበትን መጠን ስናዛምዳቸው የሁኔታው አስጊነት ይበልጥ ግልፅ ይሆናል። ኢሕአዴግ ሥልጣን እንደያዘ ወደ 50 ሚሊዮን ይገመት የነበረው የሕዝብ ብዛት በአማካይ በ2.2 በመቶ እያደገ ባለፈው የፈርንጆች ዓመት 110 ሚሊዮን ደርሷል። የምግብ፣ የኅይል ወይም ኤነርጂ፣ የመጠለያ ፍላጎትም ያን ያህል ስለሚያድግ የደን መመናመኑንም ያፈጥነዋል፤ አፍጥኖታልም።

ስለዚህም የተጀመረውን የደን ማልማት ዘመቻን እየደገፍን በተጨማሪ ሥራው ዘለቄታና ውጤታማ እንዲሆን ከታች የተጠቀሱትን ተያያዥ ጉዳዮችን ለማሳሰብ እንጠቁማለን፦

  • የደን ሽፋን መመናመንና የሚሄድበት ፍጥነት ከመንግሥት የመሬት ይዞታ ፖሊሲ ጋር የተሳሰረ ነው። መሬትን የመንግሥት ያደረገው የ1967ና አሁንም በሥራ ላይ የለው የመሬት ይዞታ በተለይ ደንና ሌላም በመንግሥት ይዞታ ሥራ ያለ መሬት ባለቤት እና ጠባቂ እንደሌለው እየተቆጠረ ለማገዶ፣ ከሰልና ሌሎች ሥራዎች ሰለባ እየሆነ ነው። የመሬት ይዞታው እንደገና ቢመረመርና በንጉሱ መንግሥት ዘመን እንደነበረው የደንና ዱር አራዊት ጥበቃ አስፈጻሚ የፖሊስ ኅይል የማቋቋም ዕቅድ በመንግሥት ሊታሰብበት ይገባል።
  • የደን ልማት ተግባር ሙያ፣ ትምህርትና ልምድን ስለሚጠይቅ ሥራው በባለሙያዎች እንዲመራ ቢደረግና የመንግሥት ባለሥልጣናትና ሹማምንት መደገፋቸው፣ መከታተላቸው ተገቢ ሲሆን ነገር ግን ለፖለቲካ ፍጆታና እኔ/እኛ አደረግኩት/አደረግነው ወደሚል የሕዝብ ድጋፍ ማግኛና ለሚዲያ ሽፋንና ዝና ባይውል ተገቢ ነው።
  • ከዚህ በፊት ከተካሄዱ በተለያየ የሥራ መስክ ከተደረጉ ዘመቻዎች ሊወሰድ የሚገባ ትምህርት አለ። ይኸውም በወታደራዊው የደርግ መንግሥት ዘመን – አምባገነንነቱና ጦረኝነቱ እንዳለ ሆኖ “መሃይምነት የጨለማ ጉዞ ነው” በሚል መሪ ቃል በዙር በዙር ከተደረገው ዘመቻና የተሳካ ውጤት የምንማረው ሃቅ አለ። የመንግሥት መሪዎችና አካላት ድጋፍ ካደረጉና ለወረት ሳይሆን ለዘለቄታው በዘመቻው ግብና ውጤት ዕምነቱ በባለሙያዎች መሪነትና በሕዝብ ተሳትፎ ይሳካል። የደን ማልማት ዘመቻውም እንዲሁ በባለሙያዎች ከተመራና ቀጣይነት ባለው መንገድ ከተካሄደ ሕዝብ ያሳካዋል። የአንድ ሰሞን ሆይ ሆይታና ሬኮርድ የመስበር አባዜ ከሆነ ግን ውጤቱ እንደ ብዙ ጅምሮች ጊዜና ሃብት ማባከን ይሆናልና ይታሰብበት ዘንድ እንጠቁማለን።

ይህ የደን መመናመንና የተጀመረው የደን ማልማት ዘመቻ የሚያስገነዝበን ጉዳይም አለ፤ ይኸውም ችግሩም መፍትሄውም የጎጥ፣ የዘር ክልል ወዘተ ሳይሆን የኢትዮጵያችን ጠቅላላ መሆኑን ነው። ሀገራዊ ችግሮች በጎሣ፣ በነገድ፣ በብሔር ሳይታጠሩ በጋራ መሥራትና መረዳዳት አስፈላጊነትን ያሳየው ይህ የደን ማልማት ዘመቻ የዘር ፖለቲካን ለሚቆምሩት የክሥረታቸው ማሳሰቢያ ደውል ነው። ሌሎችም ኢትዮጵያችንን አጎሳቁለው የያዙ የድህነት፣ የጤናና የትምህርት የመሳሰሉት አገልግሎቶች በአጠቃላይ ወደ ዘላቂ ልማትና መሻሻል እንዳንሄድ ተብትበው የያዙን ችግሮች በሁሉም አካባቢ ያሉ ሀገራዊ ጉዳዮች ስለሆኑ መፍትሄያቸውም እንደዛው ሁሉ ሀገራዊ ነው። በነገድና ጎጥ ታጥሮ ማሰብ የችግሮቻችንን መፍትሄዎች ሀገራዊ አድማስ ማየትን ይከለክላልና ይህ የደን ማልማት ዘመቻ በዚህ ረገድም አስተዋጽዖ ስለሚኖረው ኢትዮጵያዊ ብሔራዊ ስሜትን በማጎልበት ዘረኝነትን ዝቅ ከማድረግ አንፃር ልንጠቀምበት ያስችለናል።

የዛሬ 8 ዓመት በግብጽ ሙባረክን፣ በሊቢያ ጋዳፊን እየበላ የተዛመተው “የአረብ ስፕሪንግ፣ የአረቡ አብዮት የእስላም ወንድማማቾች” እንቅስቃሴ ያስደነገጠው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ወረርሽኙ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይዛመት “ዐባይ! ዐባይ!” የተባለበት ዘመን ነበር። ለኢትዮጵያችን ዐባይ ብሔራዊ አጀንዳ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ የዐባይን ጥቅም ይፈልገዋል። ዐባይ ተዜሞለታል፣ ተገጥሞለታል፣ ተጽፎለታል። ዐባይ እየተወደደ “ከሃዲው” ተብሏል፣ የተቆጩም “ዐባይ ዱር አዳሪ” ብለውታል፣ ስሙ ብቻ “ዐባይ የሀገር ሲሳይ” አስብሎታል ሌላም ሌላ። ይህ በሕዝብ ልብ በቁጭት፣ በብግነት፣ በንዴት ያለን እምቅ ስሜት በመጠቀም በሀገራችን በመለስ ዜናዊና በአገዛዙ ላይ እየተነሳሳ ያለውን ሕዝባዊ እንቅስቃሴ ወደ አብዮት እንዳይቀየር መለስ ዜናዊ ለክፉ ቀን ያስቀመጠውን የዐባይ አጀንዳ ይዞ ብቅ አለ። “ዐባይ የእዳሴው ግድብ፣ ዐባይ ሚሊንየም” ተባለለት፤ ስም ወጣለት። ዐባይ የአገዛዙ እድሜ ማራዘሚያ ይሆን ዘንድ ተለፈፈለት፤ ዳግም ተዜመለት። በወቅቱ በትንሹ በ4 ቢሊዮን ዶላር በጀት፣ በአምስት ዓመት ጽንስ የዐባይ ግድብ ልደተ ዘመን ተሰጠው። ከኢትዮጵያ አልፎ አፍሪካን በብርሃን ያጥለቀልቃል የተባለለት እዳሴ ግድብ ዛሬማ እንኳን ሕዝቡ የወቅቱ ጠ/ሚርም የዘነጉት ይመስላል።

በሰሞኑ ጋዜጣዊ መግለጫቸው በ2012 ዓ.ም. መጠናቀቅ ያለባቸው ብለው የምኒልክ ቤተ መንግስትን፣ በነፍስ ወከፍ 5 ሚልዮን ብር እራት የተበላበትን የአዲስ አበባ ማስዋብን፣ የተለያዩ ጅምር ግንባታዎችን ሲያነሱ የዐባይ እዳሴ ግድብ መኖሩም የተዘነጋቸው ይመስላል። ዐባይ ፖለቲካዊ ጠቀሜታውን የተወጣ ይመስል ከዳር እስከዳር በታላቅ ስሜትና ደስታ ለዐባይ ግንባታ ሆ! ብሎ የተነሳውን ሕዝብ ዘንግቶታል። “ቦንድ” እየተባለ ለዐባይ የተሰበሰበ የሕዝብ ገንዘብ ዐባይ ውጦታል። የዚህ ሂደት ውጤት የዐባይን ብሔራዊ ስሜት በመጠቀም ሕዝባችን በአገዛዙ ላይ ያለውን ጥላቻ በማርገብ በዐባይ ስም ድጋፉን በመስጠት መለስ ዜናዊ እፎይታ ቢያገኝም ከሰማዩ ቅጣት ሊያመልጥ አልቻለም።

በተመሳሳይ መልኩ ዛሬ ሀገራችን በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚውና በማህበረ ሰብ ዘይቤው ቀውስ ውስጥ ገብታለች። ሕዝብን አሻግራለሁ ያለው የጠ/ሚር ዐቢይ አገዛዝ የዘር ፖለቲካ ድልድዩን እያንገዳገደበት በአለበት ወቅት ኢትዮጵያዬ! ኢትዮጵያዬ! ዝማሬው ተግባራዊነቱ ሲሸረሸር በችግኝ ተከላ ስም ትንፋሽ ለመሳብ ሳይሆን ሕዝባዊ አጀንዳን ከፍ ለማድረግ ይጠቀሙበት ዘንድ እንጠቁማለን። በዓለም ደረጃ ሪኮርድ ተሰበረ ተብሎ የተዘገበለትን 350 ሚልዮን ችግኝ እውን የት ቦታ ላይ ተዘጋጀ? በዛሬ የሀገራችን ገንዘብ አቅም አንድ ችግኝ ለማዘጋጀት ምን ያህል ገንዘብ ይጠይቃል? የአንድ ችግኝ ዋጋ በትንሹ በ100 ብር ብናሰላው 35 ቢልዮን ብር ሐምሌ 22 ቀን መሬት ላይ ውሏል ማለት ነው። ሌላውን ወጪ ሳይጨምር። 350 ሚሊዮን ችግኝ ግብርና ሚንስትር ወይም የሚመለከተው አካል የማዘጋጀት አቅም፣ ቦታ አለውን? ይህ 350 ሚልዮን ችግኝ እንዴት ተጓጓዘ? ችግኝ አንዱ በአንዱ ላይ ተጭኖ የሚጓጓዝ ፍሬ እንዳልሆነ ልንገነዘብ ይገባናል። አንድ አይሱዙ የጭነት መኪና ብንወስድ ስንት ችግኝ በአግባቡ ሳይበላሽ ተፈላጊው ቦታ ሊያደርስ ይችላል። ስንት ማጓጓዣ መኪናስ ያስፈልገን ይሆን? እነኚህንና መሰል ጥያቄዎች ባለሙያተኞቹና ፖለቲከኞች ቢያነሱ አያስደንቅም። ከዚህ ስሌት በመነሳት የችግኝ ተከላው ፖለቲካዊ ጠቀሜታ ለማግኘት የሚል ስሜትን ቢፈጥርም፤ እውን ወደ በረሃ እያዘገመች ያለችውን ኢትዮጵያችንን ለትውልድና ለዘለቄታው የተመናመነ ደኗንና የዱር አራዊቶቿን ለመጠበቅ ከሆነ የችግኝ ተከላውና መንከባከቡ ያላቋረጠ ሂደት መሆን እንደሚገባው እንጠቁማለን።

በእርግጥ ለመናገር የችግኝ ተከላው አስፈላጊነት ከጥያቄ ባይገባም በመቶ ሚልዮን የሚቆጠር የኢትዮጵያ ሕዝብ ዛሬ ያረረበት ሌላውን እንተወውና ሽንኩርትና ድንች ነው። ሽንኩርትና ድንች በየጓሮው ተክሎ የለት ጉርሳቸውን ቢቃመሱ የሚመርጥ ሕዝብ ቀላል አይደለም። ረሃብ፣ ልጆችን አጉርሶ ወደ ትምህርት ቤት መላክ፣ ህብረተሰባችን 28 ዓመት ስለሚበላው እያሰበ የኖረበት የሰቀቀን ኑሮ በመጠኑም እንዲቀረፍ ከተፈለገ አጣዳፊ የአጭር ጊዜ ዕቅድ አውጥቶ ማቃመስ ይመረጣል። የሕዝቡን አጣዳፊ የኑሮ ችግሩን እንቅረፍ ከተባለ የአበባ ችግኝ ሳይሆን ጎመን፣ ቲማቲም፣ ቃሪያ፣ ሽንኩርትና ድንች ቢተክል ይመረጣል። ከብት ከብቱን ለሥጋ በሊታዎቹ ኢሕአዴግ/ህወሓት እንተወውና። ዛሬ የአዲስ አበባን የዋጋ ንረት ብንመለከተው 1 ሊትር ዘይት 100 ብር፣ 1ኪሎ ሽንኩርት 30 ብር፣ 1 ኪሎ ድንች 10 ብር፣ 1 ኩንታል ጤፍ 4000 ብር፣  1 እንጀራ 7 ብር ከ50፣  1 ኪሎ ቅቤ 350 ብር፣ አንድ አነስተኛ ዶሮ 250 ብር፣  1ኪሎ ሥጋ ከ 300 እስከ 400 ብር፣ አንድ እንቁላል 5 ብር ከ 50፣ ግማሽ ሊትር የሾላ ወተት 17 ብር ወዘተ. ደርሶ እያንዳንዱን ቤተሰብ ሃሳብ ላይ የጣለበት አጣዳፊ ችግርን “ቻሉት” በሚል የሚታለፍ አይደለም።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሰጡት የሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. መጨረሻ ጋዜጣዊ መግለጫ ችግኝ በቅሎ ዝናብ እስከሚያመጣ መብራት በፈረቃ እንደሚቀጥል እቅጩን ነግረውናል። እንግዲህ የዛፍ ችግኝ ዛፍ ሊባል የዓመታት ጉዳይ ነው። ያውም የተተከለውን ችግኝ የሚንከባከበው ተቋም ከተገኘ። ከሚጠጣና ምግብ መሥሪያ ተርፎ ችግኞቹ የሚጠጡት ውሃ ከተገኘ ነው። በየአካባቢው ለቤት ፍጆታ በየቀኑ ሰልፍ የሚይዙ የውሃ ጀሪካኖችን ለተገነዘበ፤ አገዛዙ ችግኞቹን በውሃ ጥም እንዳይቀጣ እየሰጋን የእግዜር ውሃ አይንሳቸው እንላለን።  እዚህ ላይ ነው እንግዲህ በጥቅሉ የሕዝብን ስሜትና ቁጣ የተቆጣጠሩ፣ የሀገርን ድህነትና ስቃይ የገዙ እየመሰላቸው በተጋነነ የችግኝ ተከላ ግራ የተጋባው የኢሕአዴግ አገዛዝ ለፖለቲካ ችግሩ መቅረፊያ አስቦት ከሆነ ዳግም ስህተት እየተሠራ መሆኑን መጠቆም የፈለግነው።

ጠ/ሚር ዐቢይ አሕመድ አሁንም በሳቸው አባባል በሰኔው “መፈንቅለ መንግሥት” በሰጡት የቁጣ መግለጫ አ . . .ሄ. . .ኤ . . . እሚያሰኝ ትዝብት ውስጥ እራሳቸውን እንዳልከተቱ በዛሬው ጋዜጣዊ መግለጫቸው ደግሞ በነመለስ የሰለቸንን አባባል ይደግሙልናል። በየጊዜው ስለሚታሠሩ ወገኖች ለማስተማመን “በሺዎች የሚቆጠሩ መረጃ ደርሶናል” ሲሉ የቀራቸው ቢኖር “እኔ ልሙት!” መሃላ ነው። “መፈንቅለ መንግሥት ካልሆነ በወቅቱ ከተሰዉት ውስጥ ሐዘኑ ለምን አድሎሃዊ ይሆናል” ይሉናል። እስቲ ይጠየቁና መንግሥትስ ወገን ለይቶ አይደል እንዴ መፈንቅለ መንግሥት ያለው? “ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል” እንዲሉ የእነመንግሥቱ ነዋይን መፈንቅለ መንግሥት ሊያያይዙና “ግርግር” ብለው ሊያጥላሉ ይፈልጋሉ። መለስ ዜናዊ አሸባሪ እያለ በርካታዎችን አስሯል፣ አሰቃይቷል፣ ገድሏል። የግንቦት ሰባት አባላትን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ሲያደርጉ በሚል ከ8 ዓመት በፊት የ80 ዓመት አዛውንት ጨምሮ የሚፈልጋቸውን ዜጎች አስሮ በግፍ አሰቃይቷል። ዛሬም በመፈንቅለ መንግሥት ስም እስርና ስቃይ ተቃውሞን ጋብ ያደርጋል ተብሎ ከሆነ የዋህነት ነው።

የፖለቲካ እስረኞችን የፈታነው እኛው፣ የምናስረውም እኛው አመላለስ ለውጥ አራማጁን ወደ ጥያቄ ከማስገባት አልፎ ወዴት እየተንደረደረ እንደሆነ አመላካች ነው። ዛሬም መንግሥት እራሱ ከሳሽ፣ ወንጃይ፣ መሥካሪ፣ አሳሪ፣ ፍርድ ሰጪ ከሆነበት መድረክ አልተላቀቅንም ስንል ትላንት የነበረው ዛሬም ቀጥሏልና ነው። የወያኔ/ኢሕአዴግን ሕገ መንግሥትን እምቢኝ የምንለው 28 ዓመት ከፋፍሎናልና ሀገራችንን ሳይበትናት፣ ሕዝባችንን ሳይነጣጥል እንደ ችግኝ ተከላው ልንከባከበው ሳይሆን ነቅለን ልንጥለው ይገባልና ነው። የ28 ዓመት የኢሕአዴግ ሕገ መንግሥት ረሃብ፣ እሥር፣ እንግልት፣ በሽታ፣ ሥራ አጥ፣ ስደተኛ፣ የመንግሥት ዘራፊ፣ አበራከተ ሀገርን ወደ በረሃነት ቀየረ፣ የተፈጥሮ ሃብቷን አወደመ እንጂ ለሀገርና ሕዝብ አልበጀምና ሀገር እንድትኖር ኢሕአዴግና ሕገ መንግሥቱ ከሀገርና ሕዝብ ጫንቃ ላይ መወገድ ይኖርባቸዋል።

የኢሕአዴግ ትልቁ ችግር ለፖለቲካ ፍጆታ ሲባል ይዋሻሉ። በአምስት ዓመት ይጠናቀቃል ተብሎ የተፎከረለት ዐባይ ዓመጸኛው “ዶላሩን ወደ በረሃ ይዞት ኮበለለ” ዜና ብንሰማ እንዳይደንቀን። በአምስት ዓመቱ የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አሥር የስኳር ፋብሪካ እንደሚሠራ የተወራላት ሀገራችን ስንቱን አግኝታ ስንቱን ተዋሽታለች? የ 5 ሺ ኪሎ ሜትር ሽፋን የባቡር ሃዲድ ግንባታም ተወርቶ ቀርቷል። በርካታ ዶላር በዚህ ዓመት ያስገባው የጠ/ሚሩ አገዛዝ “ረሃብ ጊዜ አይሰጥምን” ምነዋ ዘነጉት?

የኢሕአዴግ አገዛዝና ህወሓት ከጥፋት የማይማሩ መሆናቸውን አፍ ሞልቶ መናገር ቢቻልም ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ከሐምሌው 22 የችግኝ ተከላ እሳቸውም ሆኑ መሰል ወገኖቻቸው ትምህርት ሊቀስሙ እንደሚገባ ልናሳስብ እንወዳለን። የኢትዮጵያ ሕዝብ ምን ጊዜም ሀገሩን ይወዳል፣ ሰንደቅ ዓላማውን ያከብራል። አራት ነጥብ። ሀገርህ ተነካች ሲሉት ተቃውሞና በደሉን እረስቶ “አለሁልሽ” ባይ ነው። ዐባይ ሲነሳ እናቶች መቀነታቸውን፣ አባቶች የውስጥ ደረት ኪሳቸውን ዳብሰዋል። ሕፃናት ገብቷቸው ፈንጥዘዋል። የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዛቸውን ለግሰዋል፣ ነጋዴዎች፣ ተማሪዎች፣ ወጣቶች ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል ለዐባይ ግድብ  ተግባራዊነት ተረባርቧል። ዐባይ እንደ ውሃ አሳዳጅነቱ የውሃ ሽታ ሆኖ የቀረው በሕዝብ እምቢተኝነት ሳይሆን በአገዛዙ ዝርፊያና ተንኮል ነው። ከሚበላው ቆጥቦ፣ ከልጆቹ ነጥቆ ለዐባይ የቸረን ሕዝብ የዘረፉ የቀን ጅቦች ለጊዜው ተወራባቸው እንጂ በለውጥ አራማጁ ክፍል የተደረገው ቢኖር ዛሬ ላይ ሁነን ስናየው እጅግ ከፍተኛ ከለላ ነው የተሰጣቸው።

ትላንት ለዐባይ ሆ! ብሎ የወጣ ሕዝብ ጠ/ሚር ዶክተር ዐቢይ ለሥልጣን ሲበቁ በዕልልታ፣ በጭብጨባ የተቀበላቸው ሀገሩን ብሎ እንደሆን ሊማሩበት ይገባል። ወያኔ/ህወሓትን ዋልታ ባደረገው ዘረኛ አገዛዝ ሀገሬ ተከፋፈለች በሚል ስጋት ላይ የነበረው ሕዝባችን “ኢትዮጵያችን” ሲባል ሰንደቅ ዓላማውን ከፍ አድርጎ የጮኸው፣ በእልህና በሲቃ የተላቀሰው ለማንም አይደል ለእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ።

ዛሬም እንደትላንቱ ለችግኝ ተከላው ቁጥሩ ይጋነንም አይጋነን በየአካባቢው የታየው እርብርቦሽ እናት ኢትዮጵያን ተብሎ እንደሆን እያስተማረን ነው። ለሀገሩ፣ ለሰንደቁ ያለውን ፍቅር በችግኝ ተከላው ዳግም እያሳየን ነው። ኢሕአዴግን የደገፈ የመሰለን ተታለናል፣ ለዘረኝነት ያጨበጨበ እንዳይመስለን፤ ለእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ። አግባብ በሌለው አፈሳና እሥር የልጆቻቸውን እሥር ቤት ውሎ እያስታወሱ ሀገር ፍቅርን በችግኝ ተከላ እያስተማሩን ያሉ እናቶች ሊከበሩ ይገባቸዋል። ሻይ በዳቦ ያጡ ሕጻናት በችግኝ ተከላው ሲሻሙ “ኢትዮጵያችን ኑሪ! እንወድሻለን!” እያሉ ሲነግሩን ነው። ለሀገርና ለሕዝብ አንድነት ሲሉ በህወሓት/ኢሕአዴግ አገዛዝ ልጆቻቸውን፣ ወገኖቻቸውን ያጡ፣ ለአካልና ለስነልቦና ሰለባ የሆኑ ሳይቀሩ በችግኝ ተከላው በመሳተፍ ይቅር ለእግዚአብሔር ሲያሰሙ፤ መስማት የተሳነው አገዛዝ ትምህርት መውሰድ ካልቻለ እውነት እውነት እንላለን የሀገርና የሕዝብ ጊዜ ሲመጣ ወየው ለተንኮለኞች ቢባል አያስከፋም። ከኢሕአዴግ/ህወሓት አገዛዝ ውስጥ ቅን አሳቢ ወገኖችን በጠ/ሚር ዐቢይ አማካይነት ብቅ ያደረገ አምላክ አካሄዳቸውን ከሳቱ፣ በጠባቡ በር ገብተው ኢትዮጵያን ካላዳኑ፤ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር የዘረጋችው ኢትዮጵያ አንድነቷን አምላኳ ያስታቅፋታል፣ ኢትዮጵያን አትንኳት ያሉት ነብዩ መሐመድ ሌላ ጠባቂ ይልኩላታልና ስጋት አይግባን።

 

የጠ/ሚሩ “አትረብሹን” አባባል ሕዝብም ሆነ የፖለቲካ ድርጅቶች የመረበሽ አባዜ ይዟቸው አይደለም። አሁንም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሌላው ቢቀር እንጀራ በሽሮ ለመመገብ ሲሰቃይ፣ ሕፃናት ዳቦ በሻይ መቅመስ ሲሳናቸው ስናይ ዝም አንልም። ሀገር በዘረኞች በትር ስትወገር፣ ዘር እየተለየ ሲፈናቀልና አውላላ ሜዳ ላይ በረሃብና በበሽታ ሲረግፉ እያየን ዝም ካልን ምኑን ለሕዝብ ታገልን። አንዴ በአሸባሪ፣ ሌላ ጊዜ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ሊንዱ፣ አሁን ደግሞ በመፈንቅለ መንግሥት ሥም መንግሥት እራሱ ከሳሽ፣ ወንጃይ፣ መስካሪ፣ ፈራጅ እየሆነ ዜጎችን በየእሥር ቤቱ ሲያጉርና ሲያሰቃይ እያየን ስለ ሰው ልጅ መብት አቤት ካላልን ምኑን ስለ ዴሞክራሲያ መብት ደሰኮርን። 28 ዓመት ሀገርና ሕዝብ የዘረፈ፣ ያሰቃየ፣ የገደለ፣ ያሳደደ መንግሥት ሕገ መንግሥት እያለ ሲያስፈራራ፣ ለውጡ 28 ዓመት ተኮትኩተው የደለቡ የቀን ጅቦችን ካልዋጠ፣ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ ካላደረገ፣ ዘረኝነትን ቀብሮ ሕዝባዊነትን ካላነገሰ ምኑን ለውጥ ሆነና ከትግል እናፈገፍጋለን። ጊዜ እየጠበቁ፣ የሕዝብን ጥያቄ ማዘናጊያ ብሔራዊ አጀንዳ በመሳብ ሀገር አትገነባም፤ አትለወጥም። ሕዝባችን እያሳየ ካለው የሀገር ፍቅርና የአንድነት ፍላጎት ትምህርት ወስደን ከሕዝብ ጎን መቆም ያልቻለ አገዛዝም ሆነ የፖለቲካ ድርጅት አወዳደቁ የከፋ ነው። የሚጥለው የሚያምጸውና እምቢኝ ለሀገሬ የሚለው ሕዝብ ነውና ጆሮ ያለው ስለ መጨረሻው ቢያስብ መልካም ነው። አገዛዝ ይመጣል፣ አገዛዝ ይሄዳል ሀገርና ሕዝብ ግና ዘላለማዊ ናቸውና። ትግላችን ለእምዬ ኢትዮጵያ እንጂ ለሌላ አይደለም። “አንድ ሀገር አንድ ሕዝብ ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ” ይህ ነው ድጋፋችን፣ ይህ ነው ሀሳባችን፣ ይህ ነው ትግላችን!!!

ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!

ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!

 

“አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ”

 

ነሐሴ 04 ቀን 2011 ዓ.ም. (August 10, 2019)

ማሳሰቢያ ፡

  • ውድ ወገኖቻችን ይህንን «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» «ኢትዮጵያችን» ልሳን በተለይ በሀገር ቤት ኮምፒዩተር የማግኘት ዕድል ለሌላቸው በማባዛት ታሰራጩት ዘንድ ቀና ትብብራችሁን በትህትና እንጠይቃለን።
  • «አንድ ሀገር! አንድ ሕዝብ! ኢትዮጵያችን ሕዝባዊ ንቅናቄ» መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. እራሱን ይፋ ያደረገ ሕዝባዊ ድርጅት ሲሆን የንቅናቄውን ማንፌስቶና ፕሮግራም ethiopiachen.org ከሚለው ድረ ገጻችን ማግኘት ትችላላችሁ።

 

ስልክ፡  703 300 4302

ኢሜል ፡ ethiopiachen2009@gmail.com

ድረ ገጽ ፡ www.ethiopiachen.org , www.ethiopiachen.com

ምሥለ ገጽ ፡ 1H1H Ethiopiachin