እናት ቤተ ክርስቲያን አዎ በዶግማ ባትከፈልም በአስተዳደር ተከፍላለች - ከከበደ አገኘሁ – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

እናት ቤተ ክርስቲያን አዎ በዶግማ ባትከፈልም በአስተዳደር ተከፍላለች – ከከበደ አገኘሁ

1 min read
1

ከከበደ አገኘሁ
መከፈል ወይም መከፋፈል የሚለው በማንኛውም ነገር አንድ የነበረ ነገር የመከፈል አደጋ ሲገጥመው መግለጫ የሚሆን ቃል መሆኑን ሁላችንም እናውቃለን። አንድ የነበረ ነገር ከሁለት ሲከፈል ‘ተከፈለ’ ይባላል። ከሁለት በላይ ከሆነ ክፍፍሉ ‘ተከፋፈለ’ ይባላል። ቀጣዩ ጥያቄ ግን በምንና እንዴት ተከፈለ ነው የሚሆነው። በዚህ መሠረት አሐቲ/አንዲት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቀኖናዋ ተጥሶ፥ ፓትርያርኩዋ በመንግሥት ተባረው በመንበሩ ላይ ሌላ ሕገ-ወጥ ሰው በመቀመጡ ምክንያት አስተዳደሯ ከሁለት ተክፍሎ 21 ዓመት እያስቆጠረ ነው። በሕጋዊው ፓትርያርክ በስደት የምትገኘውና ፥በሕገ ወጦቹ መፍቀርያነ መንግሥት በሆኑት ‘ጳጳሳት’ የምትመራው፥ ባገር ውስጥ በታጠቀ ኃይል የምትገዛው ቤተ ክርስቲያን ሁለት የተለያዩ አመራሮች ነው ያሏት። ይህን ገሀዳዊ ሀቅ ማስተባበል አይቻልም። መከፈል የሚለው በዶግማ ብቻ ቢሆንማ ኑሮ ከዐራቱ እህት ኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተዋህዶ አብያተ ክርስቲያናት ጋርም እኮ አንድ ነን። ከ451ዱ የኬልቄዶን ጉባኤ ወዲህ በነገረ መለኮት ያልተከፋፈልን አንድ ነን ። ግን አምስታችንም ባንድ ኣሰተዳደር ስር አይደለንም።
‘’ብላቴናይቱ ታማለች እንጅ አልሞተችም ‘’ በሚል ርእስ፤ ዘሐበሻ በሚባለው ድረ ገጻችን ላይ የጻፉት ወንድም መኳንንት ታየ ስለዚህ ሁኔታ ምን የሚል መልስ ይኖራቸው ይሆን ? እኒህ ወንድም ሁላችንም የምናከብራቸው ውድ አባታችን ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ‘’እናት ቤተ ክርስቲያን አልተከፈለችም’’ ለሚለው መጣጥፋቸው ለሠጠሁት መልስ የሰጡትን ማስተባበያ ተመልክቻለሁ። በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ አሉን ከምንላቸው እውቅ ምሑራን አባቶቻችን መካከል ቀዳሚውን ቦታ ይይዛሉ ብለው ከሚያምኑት ኢትዮጵያውያን መካከል አንዱ ልጃቸው መሆኔን ራሳቸው ያውቃሉ ብየ የማምን ሰው ነኝ። አዎ አከብራቸዋለሁ ፥ እወዳቸዋለሁ ፥ አደንቃቸዋለሁም። የሚወዷትን እናት አገራቸውን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ትንሣኤዋን ለማየት እንዲያበቃቸውም የምመኝላቸው ልጃቸው ነይ። በዚህ አርዕስተ ጉዳይ ላይ ግን ከኒህ አባቴ ጋር ያለኝን ልዩነት በአክብሮት ብገልጽ ድፍረት ይሆንብኛል ብየ ስለማልገምት ነው። እርሳቸውም በዚህ መልክ ያዩታል ብየ ነው የማምነው። ለኔ ጽሑፍ ከሰጡት መልስም እንደተረዳሁት ምንም መራራነትን የሚገልጽ ቃላት በኔ ላይ እንዳልተጠቀሙ ነው። እየተከላከልኩ ያለሁትም እውነት ነው ብየ ያመንኩበትንና ቋሚ የሆነውን ተቋም እንጅ ሃላፊ ግለሰብን በሌላ መመዘኛ መዝኘ እንዳልሆነ በዚህ አጋጣሚ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ወገኖቸ እንዲረዱልኝ እጠይቃለሁ። …
ንግባእኬ ኃበ ጥንተ ነገር..ወደ አርእስቱ ልግባ።
ESAT Special on Ethiopian orthodox church current situation January 2013ለምሳሌ እኔ በምኖርበት ከተማ 3 በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲን ስም የሚጠሩ ቤተ ክርስቲኣኖች ኣሉ። 2ቱ የአዲስ አበባውን አመራር ይከተላሉ ። እኔ አባል የሆንኩባት አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን ግን የስደተኛውን ሲኖዶስ አመራር ነው የምትቀበለው። ካህናቱ በቅዳሴ ጊዜ የሚጠሩት የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስን ስምና በቅዱስነታቸው የሚመራው ቅዱስ ሲኖዶስ የመደባቸውን የሀገረ ስብከቱን ጳጳስ ስም ነው። በየጊዜው የሚወጡ መመሪያዎችንና የሲኖዶስ ውሳኔወችን የምንቀበለው እንዲሁ ከዚሁ ቅዱስ አካል ነው እንጅ አንድም ያስተዳደር ነክ ነገር ከአዲስ አበባው ጋር የሚያገናኘን የለም። አገልጋይ ካህናቱንም የሚመድብልን ይህ ስደተኛው ቅዱስ አካል ነው። ባጠቃላይ ከአዲስ አበባው አካል ሕገ ወጥ ነው ብለን በማመን የምንቀበለው ነገር የለም ። የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንንም አይወክልም በለን ነው የምናምነው። በዚህ ላይ የማያሻማ አቋም ነው ያለን። ሌሎቹ 2ቱ ግን ከኛው ቅዱስ ሲኖዶስ አንድም ነገር የሚያደርጉት ግንኙነት የላቸውም። ለምን? ባስተዳደር ወይም በአመራር መዋቅር ስለተከፈልን !! መከፈል የሚለው ነገር በነገረ መለኮት ብቻ የሚወሰንማ ቢሆን ኑሮ ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እንዲሁ በዚህ ከተማችን የግብጽ ፥ የሶርያና የኤርትራ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ስላሉ ከነሱ ጋር በተጠቃለን ነበር። በተለይ ከኤርትራውያኑ ጋር በነገረ መለኮት ብቻም ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን ቋንቋ በሆነው ግእዝም እንግባባለን። ሥርአተ ቅዳሴያችንና ማኅሌተ ያሬዳችንም አንድ ነው። ግን በተለያየ አመራር ስር ስላለን በየራሳችን ቤተ ክርስቲያን ነው የምንጸልየው። በተለይ ትግርኛ የሚናገሩት መረብ ወንዝ ወዲህ ያሉትና ወዲያ ማዶ ያሉት በትግርኛ ቋንቋም ጭምር ይግባባሉ። ታድያ በአስተዳደር መዋቅር አንድ ናቸው ማለት ይቻላል? በነገረ መለኮት ልዩነት እስከሌላቸው ድረስ አልተለያዩም ማለት ይቻላል ? ‘’እናት’’ የሚለውን ቅጽል መንፈሳዊት፥ ሐዋርያዊትና ዓለም አቀፋዊት ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን ሳይሆን የሚመለከተው ፥ ብሔራዊ ደንበሯ በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ላገኝችው እናት አገራችን ኢትዮጵያ ነው ከተባለ ነገሩ በግልጽ ይቀመጥልና አባባሉን እንቀበለው።
abune hizekel ያ ከልሆነ ግን ‘የኢትዮጵያ’ የሚለውን የሀገር ስም እንደ ሀገራዊ ማንነት ገላጭ ቅጽል በመጠቀማችን ብቻ አልተለያየንም የሚባል ከሆነ ፥ የክርስትና ሃይማኖትን በብሔራዊ ደንበር ከለልነው ማለት ነው። ሁላችንም እንደምናውቀው ሃይማኖት ዓለም አቀፋዊ እንጅ ብሔራዊ ብቻ አይደለም። ያም ስለሆነ ነው የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ዋና ማዕከሏን ሮም አድርጋ በዓለም ዙሪያ ለሚገኙት ተከታዮችዋ አመራር የምትሰጠው። ፖፖቿም ሮማውያን ብቻ ሳይሆኑ ከልዩ ልዩ ሀገሮች የተወለዱ ናቸው ። ፖፕ ለመሆን የትውልድ ሀገራቸው መመዘኛ አይደለም። መመዘኛቸው ካቶሊክነታቸውና ለሥልጣኑ ብቁ ሆነው መገኘታቸው ብቻ ነው። ለምን ? ክርስትና ቦርደር የለሽ ስለሆነ ነዋ ! የማዕከሉም ሮም የመሆኑ ምክንያት በዓለም ከሚገኙት ካቶሉካውያን ምዕመናን ጣልያን ያለው ብዙ ሁኖ አይደለም። ያማ ቢሆን ኑሮ መክሲኮ ሲቲ ውስጥ ይሆን ነበር። የኛም ቤተ ክርስቲያን ማዕከል ለ1600 ዘመን ሀገረ ግብጽ ውስጥ ነበር። ለምን ? ያው ሃይማኖት ብሔራዊ ደንበር የለሺ ስለሆነ ነው እንጅ፥ በሕዝብ ቁጥር የግብጽ ከርስቲያኖች ከኢትዮጵያ ክርስቲያኖች በልጠው አልነበረም። ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የነበረው ጳጳስም በሥጋዊ ትውልዱ ግብጻዊ ነበር። በዚህ መሰረት ነው እኛም አሜሪካን አገር በስደት የሚገኘውን ቅዱስ ሲኖዶስ የኢትዮጵያን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን፥ ባገር ውስጥም ለሚገኙት አብያተ ክርስቲያናት ጭምር ቀኖናዊ ሲኖዶስ ነው ብለን የምንቀበለው። በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት ፓትርያርክ ሁኖ የተሾመ አባት የሚመራው ይህ ስደተኛው ሲኖዶስ ስለሆነ ሁላችንም ልንቀበለው የሚገባ ቅዱስ ሲኖዶስ ነው እንላለን። ላለመቀበል ሌላ ሥጋዊ የሆነ ምክንያት እስከሌለ ድረስ ቀኖናዊም የሆነ ዶግማዊ ምክንያት ማንም ማቅረብ አይችልም።
ቅዱስ ፓትርያርኩ መንጋውን ጥለው በመሰደድ ፋንታ መገደል ነበረባቸው ለሚሉት
‘ከዚያው በወያኔ መገደል ሲገባቸው መንጋውን ጥለው ስለተሰደዱ አንቀበላቸዉም ‘ የሚለው ምክንያትም መሥሪያ ቤቱን ልቀቅ ሲባሉ አለቅም ብለው መሞት ይገባቸው ነበር የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ መራጃ ግን ያቀረበልን እስካሁን የለም። የወያኔ ባለሥልጣኖች ‘የኢትዮጵያ ክርስቲያኖች ኢየሱስ ክርስቶስን አምላካችን ብለው ማምለክ አይችሉም ፣ አብያተ ክርስቲያናት የጣዖት ቤት ወይም እኛ የምንመለክባቸው ይሁኑ ፤ ይህን ኣዋጅ የጣሰ አንገቱ በሰይፍ ይሰየፋል ፥ ወይም በመስቀል ላይ ይሰቀላል’ የሚል አዋጅ አውጀው ቢሆን ኑሮ ብቻ ነው ከዚያው ኢትዮጵያ ውስጥ መሞት የሚገባቸው የነበረው። ቅዱስ ፓትርያርኩ የተባሉት ነገር ቢኖር ሰው ሠራሺ የሆነውን መስሪያ ቤቱን (ኦፊሱን) ልቀቅልን ነበር የተባሉት። ሥልጣኑ እስከ ዕለተ ሞታቸው ስለሆነ ወያኔም ሆነ ሌላ ሥጋዊ ኃይል ሊቀማቸው የሚችለው ነገር አይደለም። ይህም በመሆኑ እኛ ክርስትና እመነታችን አገር ጥለን ስንሰደድ ኢትዮጵያ ውስጥ ጥለነው እንዳልመጣነው ሁሉ፥ ቅዱስ አባታችንም ሥልታናቸውን ይዘው መሰደድ ግድ ሁኖባቸዋል። መንፈሳዊ ሥልጣን በብሔራዊ ደንበር የሚገደብማ ቢሆን ፥ በድያስፖራ የሚኖሩት ካህናትም ሥልጣነ ክህነታቸው ከኢትዮጵያ ውጭ ሊሰራ አይችልም ይባል ነበር።
መሰደድም እንደሚችሉ ቃለ ወንጌል ይፈቅድላቸዋል። ቃሉም እንዲህ ይላል ፤ “ ወሶበ ይሰድዱክሙ በወስተ ዛቲ ሀገር ፥ ጉዩ ውስተ ካልዕታ። አማን እብለክሙ ኢይትፌጸማ አሕጉረ እስራኤል እስከ ሶበ ይመጽእ ወልደ እጓለ እመሕያው። አልቦ ረድእ ዘየዐቢ እምሊቁ ፥ ወኢገብርኒ ዘየዐቢ እምእግዚኡ። መጠኑ ለረድእ ይኩን ከመ ሊቁ ፤ ወለገብርኒ ከመ እግዚኡ” ትርጉም “ ባንድ ከተማ መከራ ቢያበዙባችሁ ወደ ሌላይቱ ሸሹ ፣ እውነት እላችኋለሁ የሰው ልጅ (ራሱ ክርስቶስ) ተመልሶ እስከሚመጣ ድረስ የእስራኤልን (ዓለምን) ከተማዎች ሁሉ አታዳርሱም። ተማሪ ከመምሕሩ አይበልጥም ፥ አገልጋይም ከጌታው አይበልጥም። ስለዚህ ተማሪ እንደ አስተማሪው ፥ አገልጋይም እንደጌታው ከሆነ ይበቃዋል።’’ (ማቴ. 10 ፣ 23-25) ኣዎ ራሱ መዳኅኒታችን ክርስቶስ ሔሮድስ ሥልጣኔን የሚቀማኝ ተወለደ ብሎ ሊገድለው ስለፈለገ እናቱ ቅድስት ድንግል ማርያም ከሺማግሌው ዮሴፍና ከቅርብ ዘመዷ ከሰሎሜ ጋር ወደ ግብጽ ይዛው ተሰዳ ነበር። አሳዳጁ ሔሮድስ እስከሚሞት ድረስ በዚያው በአህጉረ አፍሪካ ቆይቶአል። ያን ለማዘከር ነበር ይህን ከላይ የተተቀሰውን ዘላለማዊ ቃል ጌታ ራሱ የተናገረው። እኛም ዛሬ ዘመነ ስደቱን ለማሰብ በየዓመቱ ከመስከረም 26 እስከ ሕዳር 6 ሥርዓተ ማኅሌተ ጽጌን በመቆም እናስበው አለን።
‘ገዳም መግባት ይገባቸው ነበር’ ስለሚባለው
abune merkoriwos‘ቅዱስ ፓትርያርኩ ባገር ውስጥ ወዳሉት ገዳማት መግባት ሲገባቸው ምቾትን ፈልገው ወደ አሜሪካ ተሰደዱ ‘ የሚሉም አሉ። አንድ ፓትርያርክ ከዚህ ማዕረገ ሥልጣን ከደረሰ በኋላ በዓለም ዙሪያ ሐዋርያዊ ተልዕኮውን ይፈጽማል እንጅ ራሱን ለመደበቅ እንደተራ መነኩሴ ወይም ምዕመን ገዳም ይግባ የሚል መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነ መረጃ አቅርበውልን አያውቁም። እንደ ምሳሌ የሚጠቅሱትም በ1928 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣልያ በብሔራዊ ጀግንነት የተገደሉትን አቡነ ጴጥሮስን ነው። አቡነ ጴጥሮስ የተገደሉት በባዕድ ወራሪ ጦር ነው። ያን ንፁሓን ወገኖቻቸውን ካናቱንና መነኮሳቱን ሳይቀር በመርዝ ጋዝ ጢስ በግፍ እየጨፈጨፈ፥ ገዳማቱንና አብያተ ክርስቲያናቱን እያቃጠለ የመጣውን የባዕድ ኃይል ድርጊቱን በማውገዛቸው በግፈኛው ጠላት ኣዎ ተገድለዋል። ወያኔ ግን 1ኛ አገር በቀል ስለሆነ ኢተዮጵያዊ ሁኖ ወይም መስሎ ነው የመጣው ። 2ኛ ፋሺስት ኢጣልያ የወሰደውን አይነት አሰቃቂ ጭፍጨፋ እያደረገ አልነበረም የገባው። ታድያ ወያኔ እንደ ኢትዮጵያዊ ሁኖ ያደረገው ነገር እና ባዕዱ ፋሺስት ኢጣልያ የፈጸመው በምን መመዘኛ ተመዝኖ ነው ቅዱስ ፓትርያርኩ እንደ አቡነ ጴጥሮስ መሆን ነበረባቸው የሚባለው ? ያኔስ ቢሆን ኢትዮጵያዊ የሆኑት ከፈተኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ እጨጌ ገብረ ጊዮርጊስ፥ ኋላ የመጀምሪያው ኢትዮጵያዊ ፓትርያርክ ፥ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ባስልዮስ እኮ ከንጉሠ ነገሥቱ ጋር ወደ አውሮፓ ተሰደው ነበር። ተሳሳትኩ እንዴ ? ከተሳሳትኩ በቅድሚያ ይቅርታ እየጠየኩ ለመታረም ዝግጁ ነኝ። (ከታሪክ አንብቤ ነው እንጅ በዚያን ዘመን ድርጊቱ ሲፈጸም በዚህ ዓለም ኑሬ አይደለም። )ግብጻዊ የነበሩት አቡነ ቄርሎስም ሸሺተው ወደ ትውልድ ሀገራቸው ነበር የሄዱት። ታድያ ለምን ይሆን የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ስደት ባንዳንድ ወገኖቻችን በኩል ተቀባይነት ያጣው? ምክንያቱን ምን እንበለው ?
‘ገለልተኛነት’
ከሁሉም የሚገርመው ግን እንደ እኛ በስደት እየኖሩ የቅዱስ አባታችንንም አመራር አንቀበልም ብለው ፥ ከአዲስ አበባውም ሆነ ከስደተኛይቱ ቤተ ክርስቲያን አስተዳደራዊ መዋቅር ውጭ ሁነው ፥ በገለልተኛነት ያለ ራስ የተቆራረጡ አካላት መሆንን የመረጡት ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁኔታ ነው። ‘’ቄስ ወይም ዲያቆን ኤጴስቆጶሱን ቢንቀው ፥ ብቻውንም ቤተ መቅደስ ቢሠራ ፥ ኤጲስቆጶሱም ሦስት ጊዜ ቢጠራው መልስ ባይሰጠው ፤ እርሱ (ቄሱ ወይም ዲያቆኑ) ከማዕረጉ ይሻር። ተከታዮቹም ይሻሩ። “ (ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ 6 ቁጥ. 228) ታዲያ ከሁለቱ አመራር ውጭ ሁነው ካህናቱ ብቻቸውን ቤተ ክርስቲያንን መስርተው ያለ ፓትርያርክና ያለ ሀገረ ስብከት ጳጳስ በየግላቸው መኖር እንደሚችሉ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ይፈቅድላቸዋል ? ይህን የአስተዳደር ነፃነታቸውን የሚፍቅድ ቀኖና መኖሩን ቢያስረዱን መልካም ነብር። እንደሚታወቀው የቤተ ክርስቲያን መርሆ ዴሞክራሲ ሳይሆን ቀኖናዊና ዶግማዊ ነው። የቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ጉዳይ ‘ዴሞክራሲያዊ መብቴ ነው ‘ ብለን የምንከራከርበት ነገር አይደለም። ይህን ራስ አልባ መንገድ የሚከተሉት በአውሮፓ ክ16ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ወዲህ የተቋቋሙት የፕሮቴስታንት ቸርቾች ናቸው።
እና የኞቹ እስከ መቸስ ነው ያለራስ በገለልተኝነት የሚኖሩት ? ለዚህ ሁሉ ችግሮቻችን ምክንያት የሆነው ሔሮድሳዊው ሥርዓተ መንግሥት ከኢትዮጵያ እስከሚወገድ ድረስ፥ ለምን በዚህ በተሰደድንበት ድያስፖራ በስደተኛው ሲኖዶስ ስር ሁነን፥ ባንድ ልቦና ወደ ተስፋይቱ ምድር የምንመለስበትን ቀን እንዲያሳጥርልን ፈጣሪያችን አንለምነውም ? በእውነት በስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ ሥር መሆንን የሚያግድ የቀኖናም ሆነ የዶግማ ሥርአት እንደሌለ ከላይ የተቀመጡት መሰረተ ሀሳቦች የማያሳምኑ ናቸው ? ገለልተኛ ነን የሚሉትና በስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሥር ያለነው አይደለንም ወይ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሥርዓት የጥቃት ኢላማዎች ? ‘’ኦርቶዶክስንና ዐምሐራን መትተነዋል’’ ያሉት እቡይ ስብሐት ማንን ማለታቸው እንደሆን እኮ እናውቃለን። ስደተኛው ፓትርያርክ ተመልሰው መንበሩ ላይ የሚቀመጡ ከሆነ የራሳችን ፓትርያርክና ሲኖዶስ እናቋቁማለን እስማለት የደረሱት የአገዛዙ ‘ጳጳሳት’ ማንን ጠልተው ይመስላችኋል? እነዚህ ዘረኛ የወያኔ ‘ጳጳሳት ‘ እኮ ናቸው የአዲስ አበባውን ሲኖዶስ የሚገዙት። እርቅና ሰላምን አሻፈረን ብለው ለ2ኛ ጊዜ ቀኖና ጥሰው የካቲት 21 ቀን ሌላ ካድሬ ‘ፓትርያርክ’ ብለው ለመሾም እየተዘጋጁ እኮ ነው። እርቀ ሰላሙን ከነቀፉበት አንዱ ምክንያታቸው በስደት ያሉት አባቶች በፖለቲካው ምክንያት የተለያዩት ምዕመናንም ሆኑ ሌሎች ኢትዮጵያውያን መካከል ብሔራዊ እርቅ ይደረግ የሚል ሃሳብ በማቅረባቸው ነው። ሰላምንና እርቅን የሚነቅፍ አካል እኮ ነው ‘በመንፈስ ቅዱስ የሚመራ የማይሳሳት ቅዱስ ሲኖዶስ ‘ እያሉ የሚጠሩት። ታዲያ በዚህ ፀረ ሰላምና ፀረ አንድነት በሆነው የዘረኞች ጥርቅምና ፥ በነዚህ ዘረኞች በግፍ ተሰደው ከኛ ጋር ባሉት መካከል ልዩነት እንደሌለ ተቆጥሮ ከሁለቱም አንሆንም ተብሎ ገለልተኛ መሆን እንዴት ይቻላል ? እረ ተው ወገኖቸ እውነቱ የት እንዳለ በተደጋጋሚ እግዜብሔር እራሱ ግልጽ እያደረግልን እኮ ነው። የምንለያየው ማንን ለማስደሰት ? ማንንስ ለመጉዳት?
ስለዚህ ቤተ ክርስቲያናችን ቀኖናዋ የዛሬ 21 ዓመት በመጣሱ አስተዳደራዊ መዋቅርዋ ከሁለት ፥ ገለልተኞችን ስንጨምር ደግሞ ከሦስት መከፈሉን ዐይናችን እያየ ‘’አልተከፈለችም’’ ብለን እውነታውን መካዱ ችግራችንን አይፈታምና ፤ ሁላችንም በስደተኛው ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሥር ሁነን ለዚህ ሁሉ ችግራችን ምክንያት የሆነውን ሔሮድሳዊ ሥርአት እግዜብሔር እንዲያስወግድልን ባንድ ልቦና ሁነን እንንገረው። መንፈሳዊውም ሆነ ማኅበራዊ ሕይዎታችን የሚጠናከረው ባንድ አመራር ሥር ወደ አንድ አቅጣጫ ስንመመጣ ብቻ ነው። ተበታትነን በየግላችን መቆምን በመረጥን ቁጥር ችግሮቻችን የበለጠ ውስብስብ እየሆኑ ይሄዳሉ እንጅ የምንፈልገውን መፍትሔ አናገኝም። እናት ቤተ ክርስቲያናችንንም ሆነ እናት አገራችንን በተናጠል ሁነን ከከፋ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ አናድናቸውም። ተለያይተን በመቆማችን ጥንተ ጠላታችን ድያብሎስና የርሱ መንፈስ ያደረባቸውን ፀረ አንድነት ኃይሎችን እንጅ እግዚአብሔርንም ሆነ የአንድነቱን ናፋቂ ወገን አያስደስተውም። አንድ የምንሆንበት ቀነ ቀጠሮ የሚሠጠው ሳይሆን ሳይውል ሳያድር አፋጣኝ መልስ የሚጠይቅ ጉዳይ መሆኑን አምነን ፥ በአንድ አመራር ሥር ባስቸኳይ እንጠቃለል የሚል ነው የዛሬው አቤቱታየ። ኦ እግዚኦ ! አብርህ ዐእይንተ አልባቢነ=አቤቱ ጌታ ሆይ ! የልቦናችን ዐይኖች እባኪህ አብራልን ። ዓሜን።
ከበደ አገኘሁ ዘውእቱ ስምአ ጽድቅ።