በሰኔ ወር ለግድቡ ግንባታ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

በሰኔ ወር ለግድቡ ግንባታ ከ87 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ ተገለጸ

1 min read

ለታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ከውጭና ከአገር ውስጥ በተደረገ ድጋፍ በሰኔ ወር ብቻ 87 ሚሊዮን 250 ሺ ብር ገቢ መሰብሰቡን የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ህዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሄራዊ ምክር ቤት ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።

በጽሕፈት ቤቱ የህዝብ ግንኙነት የሚዲያ ኮሚኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ መንግሥት ለግድቡ ግንባታና በግድቡ የውሃ ሙሌት የሦስትዮሽ ድርድር ላይ ባሳየው ቁርጠኛ አቋም ተቀዛቅዞ የነበረው የህብረተሰቡ ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል። በሰኔ ወር ብቻ ለግድብ ግንባታ ከውጭና ከአገር ውስጥ በቦንድ ግዢ፣ በስጦታና በ8100 A አጭር የጽሑፍ መልዕክት በተደረገ ድጋፍ 87 ሚሊዮን 250 ሺ ብር ገቢ ተሰብስቧል። በበጀት ዓመቱ ደግሞ ለግድብ ግንባታ ከውጭና ከአገር ውስጥ በቦንድ ግዢ፣ በስጦታና ከ8100A አጭር የጽሑፍ መልዕክት ደንበኞች በተደረገ ድጋፍ ከ745 ሚሊዮን 250 ሺ ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል። ከዚህ ውስጥ 29 ሚሊዮኑ ከ8100A አጭር የጽሑፍ የተገኘ ድጋፍ ሲሆን፤ ቀሪው በቦንድ ግዢና በስጦታ መገኝቱን አመልክተዋል።

በበጀት ዓመቱ ለግድቡ ግንባታ የተደረገው ከፍተኛው ድጋፍ በሰኔ ወር መመዝገቡን ጠቁመው፤ በሰኔ ወር ብቻ ለግድቡ ግንባታ ከውጭና ከአገር ውስጥ በቦንድ ግዢ፣ በስጦታና ከ8100A አጭር የጽሑፍ መልዕክት ደንበኞች 87 ሚሊዮን 250 ሺ ብር ገቢ መሰብሰቡን አስታውቀዋል።

ግብፅ ስምምነት ላይ ሳይደረስ ኢትዮጵያ ግድቡን ውሃ እንዳትሞላ የሚል ቅድመ ሁኔታ ብታስቀምጥም ኢትዮጵያ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ግድቡን ከሐምሌ 1/ 2012 ዓ.ም ጀምሮ እንደምትሞላ ቁርጠኛ አቋም በመያዟና መንግሥት ቃሉን ጠብቆ በተያዘው ቀነገደብ የግድቡን የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት ማጠናቀቁን ተከትሎ በተፈጠረው ህዝባዊ መነቃቃት፤ የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ከሐምሌ 1 እስከ 15/2012 ዓ.ም ባሉት 15 ቀናት ውስጥ ብቻ በቦንድና በድጋፍ 22 ሚሊዮን ብር መሰብሰቡን ተናግረዋል።

በተለይ የግድቡ የመጀመሪያ ዙር የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ ከውጭና ከአገር ውስጥ ለግድቡ ግንባታ የሚደረገው ድጋፍ በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያመለከቱት ዳይሬክተሩ፤ ለግድቡ ግንባታ በ8100A አጭር የጽሑፍ መልዕክት ድጋፍ የሚያደርጉ አንድ ሚሊዮን 290ሺ ደንበኞች መኖራቸውን ጠቁመዋል።

ከዚህ ውስጥ 290ሺዎቹ የግድቡ የመጀመሪያ የውሃ ሙሌት መጠናቀቁን ተከትሎ በተገኘው ድል የ8100A አጭር የጽሑፍ መልዕክት ደንበኛ በመሆን ለግድቡ ድጋፍ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም በተገኘው ድል ከውጭና ከአገር ውስጥ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው የቀጠሉ ሲሆን፤ ከትናንት ወዲያ ብቻ ኒያላ ኢንሹራንስ የ12 ሚሊዮን ብር ቦንድ ሲገዛ፤ ሦስት ሕፃናት ደግሞ ለልደት በዓላቸው የሚያወጡትን ወጪ ለግድቡ ግንባታ ድጋፍ በማድረግ የ20 ሺ ብር ቦንድ መግዛታቸውን ተናግረዋል።

የግድቡ ግንባታ 72 በመቶ ቢጠናቀቅም 28 በመቶው ስለሚቀር ህብረተሰቡ አሁን ላይ የተገኘውን ድል ከዳር ለማድረስ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ጥሪ አቅርበዋል።

አዲስ ዘመን ሐምሌ 25 ቀን 2012 ዓ.ም
በ ሶሎሞን በየነ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.