ይታየኛል ( ዘ-ጌርሣም) – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

ይታየኛል ( ዘ-ጌርሣም)

1 min read

ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መነፅር
ስሜቴ ተውገርገር
ድምፅህን አሰማ
ህልምህን ተናገር
ቅዠትክንም ደርድር

ምኞትክን አስረግጥ አድማጭ ድንገት ካለ
በአዕምሮው ያመነ የተደላደለ
ከአጥናፍ እስከ አጥናፉ
ሰላም ሰፍኖ በአገር
ፖለቲካው ሰክኖ በውል ሲነጋገር
ከጥፋት ዓለሙ ሁሉም ፊቱን ሲያዞር
መተሳሰብ ሲነግሥ
ልዩነት ሲወንስ
ጠላትን ሲከፋው
ወዳጅ ደስ ሲለው
ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መነፅር
መለያየት ቀርቶ
አንድነት ጎልብቶ
በጋራ በመቆም
ወገንን ለመጥቀም
ሀገርን አልምተን
ከልመና ወጥተን
ዴሞክራሲ ሰፍኖ
ጀብደኝነት በንኖ
አንድነት ጠንክሮ
ሁሉም ጠግቦ ሲያድር
ተርፎትም ሲያካፍል
ገበሬው አልፎለት
ወጥቶ ከድህነት
ተሜ ሲመራመር
አዲስ ግኝት ሲፈጥር
ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መነፅር
መጠፋፋት ከስሞ
አሉባልታ ወድሞ
አዕምሮኣችን ዳብሮ
ከጥፋት ተምሮ
ሲሰለፍ ለልማት
ለሰላም ዋስትና
ለህዝብ አርነት
መሠረት ነውና
ስሜተኞች ሳንሆን
ሀቅን ሳንተፋ
የሌላውን ክብር አውቀን ሳንጋፋ
አድማን ስናወግዝ
ህብረትን ስናግዝ
ቂመኞች ሳንሆን
ይቅር ተባብለን
ክህደትን አቁመን
ስለ ዕውነት ተማምነን
ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መንፅር
ማንም ሳይከፋ ሁሉም ተደስቶ
በዕኩል ዜግነቱ ከልቡ ተኩራርቶ
ኢትዮጵያን በጋራ አልምቶ ገንብቶ
በወንድሙ ማግኘት ሌላው ተደስቶ
ከከተሞች ወጥቶ ገጠሩን አልምቶ
ደንና ጫካውን መልሶ ተክቶ
ለዱር አራዊቶች መኖሪያ አመቻችቶ
ለገበሬው ህይወት ዋስትና መሥርቶ
የልማት ዕቅዱን መዋቅር ዘርግቶ
ደፋ ቀና ብሎ ሲሠራ ምሁሩ
ሁሉም በየሙያው ሲጥር ለሀገሩ
ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መነፅር
ሙስሊም ክርስቲያኑ
የአንድነት ማገሩ
ኦሮሞና አማራው
ትግሬና ጉራጌው
ሐረሬ ሱማሌው
ሐድያና ከፌው
ቤንሻጉል ጋምቤላ
አገውና አፋሬው
ሲዳማ ወላይታው
ሌሎችም በሙሉ ወንዶችና ሴቶች
የኢትዮጵያ ፀጋ የማህፀን ፍሬዎች
ደምቀው የሚታዩት እቅፍ አበባዎች
አብረው ተደጋግፈው
የሕብረቱን ገመድ ሰንሰለት ዘርግተው
በአንድ ላይ በመቆም ጠላትን ሲያስቀኑ
ለኢትዮጵያ ክብር አጥር ግንብ ሲሆኑ
ይታየኛል ያ ቀን መምጣቱ እንደማይቀር
ማስተዋል ከቻለ የዕይታው መነፅር

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.