የባለ አደራ መንግሥት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቆቆሙ፣ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ጣምራ መንግሥት ይመሥርት - ሚሊዮን ዘአማኑኤል – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የባለ አደራ መንግሥት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቆቆሙ፣ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ጣምራ መንግሥት ይመሥርት – ሚሊዮን ዘአማኑኤል

1 min read

ለውጡ በዴሞክራሲ አብሪ ጥይቶች ከሸፉ!!! የፖለቲካ ልሂቃን ታላቅ አሳቢዎች አፈና ይቁም!!! ሃገሪቱ የጋራችን ናት!!!

የኢትዮጵያና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በጋራ ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት መጀመሪያ ይመሥርቱና የብልፅጋና ፓርቲ ጋር ጣምራ መንግሥት መመሥረት ይኖርባቸዋል እንላለን፡፡ በተለያዩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፎች መበረታታት ይኖርባቸዋል፡፡ በሰላማዊ መንገድ ለቀረቡ ጥናቶችን እንደ እጅ ቦንብ መፍራት የዲጂታል አንባገነናዊነት አዲስ  የኮሮና ቨይረስ የፖለቲካ ሥልጣን ማቆያ ሥርዓት ዘይቤ ሆኖል፡፡   በትረ-ሥልጣን በትግል እንጂ በልመና አይገኝምና!!! ሃገራችን ከገባችበት የፖለቲካ ክስረትና የኢኮኖሚ ቅርቃር በልጆቾ ህብረት እንድትወጣ የሚሻ ሁሉ በክልሎች መኃል የተደገሰው የድንበርና ወሰን የማያባራ ጦርነቶችን ማስወገድ የምንችለው ቁጭ ብለን በዴሞክራሲያዊ መንገድ በጠረጴዛ ዙሪያ ስንወያይ ብቻ ነው እንላለን፡፡  በሃገር ውስጥና በባህር ማዶ የሚገኙ ምሁራን ከቪዥን ኢትዮጵያና ከአገር ውስጥ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች በመምህራን የተመረጡ ምሁራን በሃገሪቱ የፖለቲካ፣ኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ፁሁፎች በማቅረብ፣ ስለ ህገ-መንግሥት ጥናታዊ ምርምር በማድረግ፣ የሃገሪቱን የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ መመሪያ በማዘጋጀት፣ የሰው ኃይል በሁሉም መስክ በማሰልጠን ለዲጂታል ቴክኖሎጅ ዘመን የሚመጥኑ የተማረ የሰው ኃይል ሙያዊ እውቀትና ክህሎት ያለው ሰው በፈተና ውድድር በተፈላጊ ቦታ ሥልጣን እንዲይዝ በማድረግ ከገባንበት የፖለቲካ ካድሬዎች ቡረቃና ጫጫታ ለአንዴና ለሁሌም እፎይ እንበል፡፡ ከደርግ ወታደራዊ መንግስት ዘመን የተተከሰተው ግራ ዘመም፣ የማርክሲስት ሌኒኒስት የፖለቲካ ፓርቲ የፈለፈላቸው ካድሬና ኮሚሳሪያት የሲቨልና ወታደራዊ ሹማምንቶች ሥርዓት አርባ አምስት አመት አስቆጠረ፡፡  የግራ ፖለቲካ  ካድሬ ሹማምንት እውቀት አልባ የድንቁርና ሥርዓት እመሩ የፖለቲካ ፕሮፓጋንዳ ብቻ በማናፋት ሳይሠሩ እየበሉ ሃገር አዋርደውና ህዝብን አደህይተው ይገዙ ነበር፡፡ በፖለቲካ ፣በኢኮኖሚና ማህበራዊ ጉዳይ ትምህርት የሌላቸው ካድሬና ኮሚሳሮች ለግል ጥቅማቸው የመንግሥት ቤት ሲወስዱ፣ መኪናና መሬት ሲቀራመቱ በሙስና ተጨማልቀው ህዝብ ሲዘርፉ 45 ዓመታት አስቆጠሩ፣ በቃ ልንላቸው ይገባል!!! ፖለቲካና የመንግሥት አስተዳደር መለያየት አለባቸው፣ ፖለቲካ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና በኢንዱስትሪ፣ በፋይናንስና በባንክ  ዘርፎች ሙያተኞች አካዳሚሽያን፣ ቴክኖክራቶች ሥራ ጣልቃ መግባታቸው ለሃገራችን ኢኮኖሚ ውድቀት፣ለህዝብ ድህነት ዳርጎናል፡፡ የደርግ ኢሠፓ፣ የህወሓት/ኢህአዴግና የኦዴፓ ብልፅግና ፓርቲ ካድሬዋች ለአንዴና ለሁሌ ከላዕላይታ ታዕታይ መንግሥታዊው መዋቅር ውስጥ ከነሰንኮፉ ተነቅሎ መጣል አለበት እንላለን፡፡  ምርጫ አሸንፈው መንግሥታዊ አስተዳደሩን ሥልጣን እርከን ከሚወስዱት በስተቀር በሙያተኞች የሚያዙ መንግሥታዊ መዋቅሮች የሥራ ዓይነትና የሥልጣን እርከን እየተሰፈረ በእውቀትና በችሎታ በፈተና ያለአንዳች አድሎ የሚሰጥበት ሥርዓተ መንግሥት መመሥረት አለበት እንላለን፡፡

ኦዴፓ ብልፅግና የዶክተር አብይ አህመድ መንግሥት የህግ የበላይነትን የማስከበር፣ የህዝብ ደህንነትን ማስጠበቅ መንግሥታዊ ኃላፊነቱን የመወጣት የመጨረሻ እድሉን ሊጠቀምበት አልቻለም!!!

  • የህወሓት፣የብአዴን፣ ኦህዴድና የደቡብ/ኢህአዴግ አመራሮች የነበሩ ለዓለም አቀፍ ፍርድ እንዲቀርቡና በኤችአር 128 የስብአዊ መብት ጥሰት እንዲጠየቁ በማድረግ በፈፀሙት ወንጀል እንዲጠየቁ ማድረግ ይኖርበታል፡፡
  • በህወሓት ኢህአዴግ ዘመን በህዝብ ኃብትና ገንዘብ በዘረፋ የተገነቡ የፓርቲ የንግድ ድርጅቶች ኢፈርት፣ ወንዶ፣ ዲንሻ፣ ንብረትና ትላልቅ የክልል ባንኮች፣ ማይክሮ ፋይናንስ ባንኮችና የመገናኛ ብዙሃን ቴሌቪዝንና ሬዲዬ ወዘተ ተወርሰው የህዝብ ኃብት እንዲሆኑ እንጠይቃለን፡፡ የህወሓት/ ኢህአዴግ ሹማምንት ለ27 አመታት የተጠቀሙበት የመንግሥት ቤቶች፣ መኪኖች፣ ልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅሞች  ተቆርጠው ለህዝብ አገልግሎት እንዲውሉ ማድረግ
  • በህወሓት ኢህአዴግ የትግራይ ክልል ሹማምንቶች ላይ ከተቃዋሚ የትግራይ ድርጅቶች ጋር በመምከር የኢኮኖሚ እቀባ ማድረግ፣ ወያኔ ከመቐለ በመገናኛ ብዙሃን ቴሌቪዝንና ሬዲዬ የሚያናፋው የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ ማስቆም ይገባል እንላለን፡፡ የዶክተር አብይ መከላከያ ሠራዊት የሚበረታው ለሱማሌ ክልል (አብዲ ኢሌ!!!)፣ ለአማራ ክልል (አሳምነው ፅጌ!!!)ና ለደቡብ ክልል (ሲዳማ ህዝብ ግድያ!!!) እርምጃ ሲወሰድ በአድሎዊ ፍርደ ገምድል ዳኝነት የትግራይ ክልል (ደብረፂዎን) ዝም ማለት በአንድ አገር ሁለት መንግሥት በመፍጠር በኢትዮጵያ ታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡
  • የኦህዴድ/ኦዴፓ የሴራ ፖለቲካና የተረኝነት አባዜ የኦነግ ሸኔ የወለጋን ህዝብ በስብዓዊ ጋሻነት ይዞ ምሁራን ኦሮሞዎችን ሲገልና ባንክ ሲዘርፍ ዝም እየተባለ፣ በኦነግ ቄሮዎች በአዲስ አበባ፣ ድሬዳዋና ሐረር እየተፈፀመ ያለው የህዝብ መብት ጥሰትና አድሎዊ የመሬት ወረራና የህዝብን ስብጥር ከምርጫ በፊት ለመቀየር የሚደረግ ሴራ የዶክተሩን የአገዛዝ እድሜ ያሳጥረዋል፡፡ የህዝብ በደልንናየእናቶች ለቅሶን፣ የታገቱትን የዩኒቨርሲቲ ሴት ተማሪዎች ለቅሶ እያዩ እንዳላየ መሆን አንድ ቀን በፍርድ ያስጠይቃል እንላለን፡
  • በኢትዮጵያ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በይፋና በህቡዕ ጊዜዊ የባለአደራ መንግሥት ተቆቆሞ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር የጋራ መንግሥት በመመስረት የወደፊቱን ህዝባዊ ምርጫ ሥርዓት ማመቻቸት ያስፈልጋል እንላለን፡፡ ዶክተር አብይ በሃገሪቱ ህግ እንዲከበር ማድረግ መንግሥታቸው ስላልቻለና ሃገሪቱ በዲፕሎማሲ ዘዴና ችሎታ እጦት በህዳሴው ግድብም አጣብቂኝ ውስጥ መግባቶ፣ በኢትዮጵያና ኤርትራ መርህ አልባ ግንኙነት አፈታት የዶክተር አብይ የልጅ መንግሥት እውቀትና አቅም ስላነሰው አማካሪዎቹም የድሮው ኢህአዴግ ጭፍራ ካድሬዎች ይሄን ሃገር ወደ ባሰ ጨለማ አዘቅት ውስጥ ይከቶታል እንላለን፡፡ ከመስከረም 30 በፊት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት አቆቁመው ከመስከረም 30 በኃላ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ጥምር መንግሥት መመሥረት አገሪቱን ከችግር ያድናታል እንላለን፡፡
  • በጣምራው መንግሥት (ብልፅግና ፓርቲና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት) በወያኔ የረቀቀው ‹‹ሕገ መንግሥት›› በዴሞክራሲያዊ መንገድ ለህዝብ ለውይይት ቀርቦ እንዲሻሻል    ይደረጋል፡፡
  • የብልፅግናና በባለ አደራ የሚያቆቁሙት ጣምራ መንግሥት ከምርጫው በፊት በመላ ሃገሪቱ የህዝብ ቆጠራ ያስደርጋሉ፡፡
  • በፖለቲካ ካድሬዎችና በቴክኖክራቶች(ሙያተኞች) የሚያዙ መንግሥታዊ መዋቅሮች የሥራ ዓይነትና የሥልጣን እርከን እየተሰፈረ በእውቀትና በችሎታ በፈተና ያለአንዳች አድሎ የሚሰጥበት ሥርዓተ መንግሥት ለመመሥረት አስተዳደራዊ ጥናት ቀርቦ የሚፀድቅበት ሁኔታን ማመቻቸት አለበት እንላለን፡፡
  • የፖለቲካ ልሂቃን ታላቅ አሳቢዎች አፈና ይቁም!!! ሃገሪቱ የጋራችን ናት!!! አቶ ልደቱ አያሌው፣ ጅዋር መሃመድና አቶ እስክንድር ነጋ ሌሎች የፖለቲካ ሰዎች ባቀረቡት ጥናታዊ ፁሁፎች በውይይት መሞገት እንጂ በስድብ ጥንብ እርኩሳቸውን ማውጣት ዴሞክራሲያዊ ባህላችንን ያቀጭጫል!!! በአዲሱ ለውጥ በዴሞክራሲ አብሪ ጥይቶች ከሸፈዋል፡፡ ሃሳቡን ከተስማሙበት የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት መሥርተው፣ከእዛ በኃላ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ጣምራ መንግሥት ይመሥርቱ እንላለን አንዱ አማራጭ መፍትሄ ነው እንላለን ሃሳባችሁ ይናፍቀናል አንገት አትድፉ፣ የእናንተ እድሜ ወጣቶች የግራ ፖለቲካኞችን ሳትፈርጁ አቅርባችሁ፣ የዲጂታል ቴክኖሎጅ የወጣቶች ህብረት ከኃይማኖት፣ ከዘር፣ ከብሄር ነፃ የወጣ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት መሠረት ድንጊያ አኑሩ እንላለን!!!

 

ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት በተፎካካሪ ፓርቲዎች ያቌቁሙ!!!

የተፎካካሪ ፓርቲዎች ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት፣ ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ጣምራ መንግሥት ይመሥርቱ!!!

ተፎካካሪ ፓርቲዎች  ጊዜዊ የባለ አደራ መንግሥት በጋራ ለመመሥረት ተሰባሰቡ!!! ታገሉ!!!

ከብልፅግና ፓርቲ ጋር ባለ አደራ የሚያቆቁሙት ጣምራ መንግሥት ይመሥረት!!!

መሥከረም 30 ቀን 2013ዓ/ም በጣምራው መንግሥትይቌቌም!!!

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.