"የአባይ ወንዝ ከአድዋ  እኩል ኩራታችን ነው።" - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ  – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

“የአባይ ወንዝ ከአድዋ  እኩል ኩራታችን ነው።” – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ 

1 min read
2
 የአባይ ወንዝ ከአደዋ እኩል ኩራታችን ነው።ከአደዋ እኩል ክብራችን ነው።ከአደዋ እኩል ትምክህታችን ነው።አባይ ከእኛ አፈራችንን ወሰዶ ለግብፅ መሥጠቱ ለጋሥነታችንን ፣ፍቅራችንን ለማሣየት፣ለማሥገንዘብና ለማሳወቅ እንደሆነ ዛሬም የግብፅ መንግሥት አልገባውም።ወይም እየገባው እንዳልገባው ለመሆን ይሞክራል።
   ይህንን ማዘናጋቱን፣ ከአንድም ሁለት ግዙፍ ግድብ ገድቦ ሲያበቃ የእኛን አንድ የኃይል ማመንጫ ግድብ አይቶ አይኑ በቅናት ደም መልበሱ ያረጋግጥልናል። በእኩይ ቅናቱም በዓለም ባንክ ውስጥ ባሉት ደጋፊዎቹ በመታገዝ፣ (ምናልባትም በሙሥና) የሀገራችን መንግሥትን በአሜሪካ መንግሥት አማካኝነት  እጅ ለመጠምዘዝ  ሞክሯል።
   ይህ ሙከራ የቀቢፀ ተሥፋ ሙከራ ነው።ከቶም የሚሳካ አይሆንም።የህዳሴው ግድብ የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ አሻራ ያለበት እንደአይን ብሌኑ የሚያየው የልማት ሥራ ነው።ይህ የልማት ሥራ ነገ መላውን ህዝብ በቀን ሦሥት ጊዜ እንዲመገብ የሚያደርግ ብልፅግናን ይዞለት የሚመጣ እንደሆነ ጠንቅቆ ያውቃል።እናም በአባይ እና በአይኑ ቀልድ እንደማያውቅ እና አባይም ልክ እንደ አድዋ የኩራቱ ምንጭ እንደሆነ የኢትዮጵያ ጠላቶች ሁሉ ከወዲሁ ቢገነዘቡት መልካም ነው።
     የግብፅ ህዝብ 100% የኤሌትሪክ እና የንፁህ ውሃ አገልግሎት በአባይ ወንዝ  ተጠቃሚ ሆኖ፣ኢትዮጵያ 85% ለወንዙ ውሃዋን እየሰጠች 56% የኢትዮጵያ ህዝብ ዛሬም በጨለማ ውስጥ እንዲኖር በጉልበተኞች ለማሥገደድ  መሞከር ከታሪክ ያለመማርን የሚመሰክር ሆኖ አግኝቸዋለሁ ።
     በታሪካችን ጥቂት ኢሌቶች እና አማራጭ የሌላቸው በቅኝ ገዢዎች ቁጥጥር ሥር የዋሉ “የኢትዮጵያ ደም ያላቸው ባንዳዎች” ብቻ ናቸው ይህቺን ሀገር ከፋሺሥት ጋር የወጓት።ዛሬም ለሆድ እና ሥልጣን ለሚያሥገኘው ብዝበዛ እና ተገቢ ያልሆነ ሀብት እና ጥቅም ሲሉ ብቻ  የባለአገሩን ጥቅም አሣልፎ ለመሥጠት ፣”የበህል ክፍል በሆነው እና የማንም ንብረት ባልሆነው ቋንቋ “ሥም በህቡ የሚቀሳቀሱ እንዳሉ አንዘነጋም።
    ምናልባትም በነዚህ ላይ የግብፅ መንግሥት ተሥፋ በማድረግ ና በአሜሪካ መንግሥት “የዓለም ቁጥር አንድ ጉልበተኝነት ”   በመሥፈራራት የግብፅን ህዝብ የማይጓዳውን ነኃይል ማመንጫ ግድብ አሥተጓጉላለው ብላ ካሰበች በእጅጉ ተሣሥታለች።መሣሣቷንም የኢትዮጵያ መንግሥት በመግለጫው አሥገንዝቧታል።
   የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ በታች ያሰፈርኩትን ፣መግለጫ ፣ የኤሜሪካ የገንዘብ  ሚኒሥቴርን ህግን ያልተከተለ አካሄድ  በመቃወም አውጥቷል ።አንብቡት።
አዲስ አበባ ፣ የካቲት 21 ፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ የተሰጠ መግለጫ::
     የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የውሃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒሰቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ28 ፌብሩዋሪ 2020) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን የፕሬስ መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ ተመልክተውታል። ስብሰባው የተካሄደው ኢትዮጵያ አስቀድማ ለግብጽ፣ ለሱዳን እና ለአሜሪካ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳውቃ እያለ ነው፡፡
      የግድቡ ባለቤት የሆነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሰረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊ እና ምክንያታዊ አጠቃቀም እና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሰረት የምታከናውን ይሆናል።
      ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሰጠውን መግለጫ አትቀበልም።
በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሶስቱ ሀገራት የድርድርም ሆነ የሕግ እና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም።
       የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ሆነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብ የሚዘጋጀው በሶስቱ ሀገራት ብቻ እንደሆነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች።
ኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን በሚያውቁት እና በተስማሙበት እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀጽ ስምንት አድናቆታቸውን በሰጡት ሂደት መሰረት ሁሉንም የግድብ ደህንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሃሳብ መሰረት የተሰጡትን ምክረ-ሃሳቦች መፈጸሟን ትቀጥላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌት እና የውሃ አለቃቅ መመሪያ እና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሰረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ እና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሂደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።
     የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ
     ይህ የኢትዮጵያውያን ሁሉ አቋም ነው።በየካቲት 23 / በ124 ኛው ድል በአል አከባበር  ላይ የአሜሪካን መንግሥት፣ የተንኳል ቀለበት ውስጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ና ህዝብ  እንደማይገባ   ፣ምኒልክ  በውጫሌ ውል ላይ ያሳዩትን ያለመፈረም ጀግንነት ና ቆራጥነት  በድጋሚ ለጥቅማቸው ብቻ ለቆሙ፣የደሃ ቁሥል ለማይሰማቸው ተገቢውን ምላሽ በመሥጠት በጀግኖቹ ሰማእታት ሥም ቃል የገባበት መግለጫ እንደሆነ አስባለሁ።በግሌ።…
    የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ  ፣ “ቀደም ሲል የነበረውና ግንባታው በታችኛው የተፋሰሱ አገራት ላይ ጉልህ ጉዳት እንዳይደርስ በሚለው የመርህ ስምምነት መሰረት “ግድቡን በውሃ የመሙላትና ሥራውን የመሞከር ሂደት ስምምነት ሳይደረግ መከናወን የለበትም።” ሲል፣ ምን ማለቱ ነው?
   ይህ የገንዘብ ሚኒሥቴር መግለጫ “የአሜሪካ መንግሥትን አቋም ያንፀባርቃል።” ብለን ከወሰድን እና በፕሬዝዳንት ትራምፕ የሚደገፍ ከሆነ፣የአሜሪካ መንግሥት በግልፅ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጋር የማይፈታ ቅራኔ ውስጥ መግባቱን ይውቃልን??? የአሜሪካ ህዝብ  የኢትዮጵያዊያን የልብ ወዳጅ መሆኑን ዘንግቶት ነው ይህንን የግብር ይውጣ መግለጫ ያወጣው?። የአሜሪካ  ህዝብ እንደህዝብ የሌላውን ጉሥቁልና አይሻምና መግለጫውን እንደገና እንዲፈትሸው እንመክራለን።
   የህዝብን ጉሥቁልና የሚሹት ፣የህዝብን እልቂት የሚያባብሱት፣የህዝብን ህመም እና ሥቃይ  ለሀብታቸው ምንጭነት የሚጠቀሙበት፣የጦር መሣሪያቸውን፣ልዩ ልዩ ሸቀጣቸውን ፣ ማራገፊያ እና የጥሬ ዕቃቸው ምንጭ በማድረግ ለዘላለም አለም የማፈልጉ አንድ ፐርሰንቶቹ ሀብታሞች ናቸው።  የአሜሪካ መንግሥት ደግሞ የሚመራው  በአንድ ፐርሰንቱ ባለሀብቶች እንደሆነ ይታወቃል።
      እነዚህ ባለሀብቶች እኮ፣   በኢትዮጵያ ውስጥ ፣በተለይም በአባይ ወንዝ  እና በአባይ ገባሮች  ሰፊ የልማት ፕሮጀክት ቢኖራቸው ኖሮ ወይም የህዳሴውን የኃይል ማመንጫ ፕሮጀክት ግንባታ የእነሱ ባለሀብቶች ቢገነቡ እና ሙሉ ለሙሉ ኤሌትሪክ ቢሸጡ ኖሮ፣ግንባታውን አልጋ በአልጋ እንደሚያደርጉት የታወቀ ነው።….
     ይህንን ሳስታውል ዛሬም አፍሪካውያንን በመበዝበዝ፣ አሁን ከሚገኙበት እጅግ የተቀናጣ ኑሮ የበለጠ የሚመኙ ሠግብግቦች በአሜሪካ እና በአውሮፖ ሥላሉ ፣የአፍሪካ መከራ ቀጣይ እንደሚሆን አሠተውላለሁ።ይሁን እንጂ ህዝብን ለታላቅ ዓላማ የሚያሠልፍ የአፍሪካ መንግሥት እንደ ምኒልክ  ድል እንደሚቀዳጅ አምናለሁ ።
     ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፣ጥንቻማ ከበርቴ በመሆናቸው፣ከግል ጥቅማቸው  አንፃር ከግብፅ ጋር መወገናቸው  ባያሥገርመንም ፣የአሜሪካ ምክር ቤት የሳቸውን አቋም የደግፋል ብይ አላምንም።
   ኢትዮጵያ በገለለተኛ ባለሙያዎች ተጠንቶ  የቀረበውን የግድቡን የውሃ አሞላል እና የውሃውን አለቃቅ መሠረት በማድረግ የግብፅ ህዝብን በመይጎዳ መልኩ ግድቦን ሞልታ ፣ኤሌትሪክ እያመነጨች ውሃውን እንደምትለቅ እየታወቀ፣ ከግብፅ አሥዋን ግድብ እጅግ የሚያንሰውን የህዳሴ ግድብ “ድርድሩን ሳትፈርሚ አትሞይም”ማለት እጅግ ጫፍ የወጣ አምባገንነት ነው።
    የአሜሪካ ምክር ቤት ይህንን አምባገንነት ሊያሥቆመው ካልቻለ፣ “የአሜሪካ ዴሞክራሲ የይስሙላ ነው ።” ለማለት እገደዳለሁ ።
     ደሃ ሀገራት ለእድገትና ለብልፅግና የሚያደርጉትን ጥረት ፣ባላቸው ዕውቀት፣ቴክኖሎጂና የገንዘብ አቅም ከ ከማገዝ ይልቅ፣ የበለጠ ለማደህየት መጣርም የሤጣን ተግባር እንጂ ኃይመኖት ያለው ሰው ተግባር ያለመሆኑንም አሠገነዝባለሁ ።
      እኛ እንደ ህዝብ ኩሩዎች፣ጨዎዎች፣እንዲሁም ኃይማኖተኞች  ነን ።በኩራታችንም ሰበብ ” አያሌ የባርነት  ሥጦታዎችን አንቀበልም።” በማለት ፣ከምዕራባውኑ ጋር ትላንት ሥንፋለም ኖረናል።
    ትላንት ከመሐዲሥቶች ፣ከድርቡሾች ፣ከግብፆች ፣ከኢጣሊያኖች ጋር ተወግተን ድልን የተቀናጀነው ኩሩ ህዝብ በመሆናችን ነው።
     የዛሬ 124 ዓመት  የካቲት  23/1888 ዓ/ም በሞሶሎኒ መንግሥት የሚመራውን ወራሪውን  የፋሺስት ኢጣሊያን መንግሥት “አደዋ” ላይ ሥናሸንፈው ፣ እንዲህ ተብሎልን ነበር፣
  “የጀርመንና የኢንግሊዝ መንግሥት ፣የአደዋን ድል የሰሙት ‘ይህ እንደምን ሊሆን ቻለ?’ በሚል የመገረምና የቁጭት ስሜት ነው።በዚህ ምክንያት የኢንግሊዝ ምክር ቤት ተከፍቶ ጉዳዩ በሚጤንበት ወቅት የኢንግሊዝ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሎርድ ጀ.ናትናኤል የሚባለው ሥለአደዋ ድልና፣ሥለ ኢጣሊያኖች መሸነፍ ንግግር  ሲያደርግ’…የሐበሾች ማሸነፍ የኢጣሊያንን ጦር፣መፍረስ ብቻ ሳይሆን፣ለግብፅ አደገኛ እና በአፍሪካ ላለው የአውሮፓ አቋም አሥጊ ነው።ሥለዚህ ወደፊት ገፍቶ አደጋውን መቆም፣የተከበበውንም፣ከሰላን አድኖ የግብፅን ወሰን በደንብ መከላከል የሥፈልጋል።…ኢጣሊያም ለባንዲራዋ ክብር ሥትል እንደገና ተዋግታ የመሸነፍ ብድሯን እንደምትመልስ እተማመናለሁ ።….’…..
   የሎንዶን ታይምስ ጋዜጣም እንዲህ ብሎ  ነበር ።
“…የኢጣልያኖች  በሚኒልክ መሸነፍ በታሪክ ሲታወስ የሚኖር ነው።ይኽም ድል አድራጊነት፣እሥከዛሬ አረመኔ እየተባለ፣በአውሮፓውያኑ ይናቅ የነበረውን የአፍሪካዊያኑን መንፈሥ የሚቀሰቅስ ነው።” (ከተክለፃዲቅ መኩሪያ የታሪክ መፅሐፍ ፣ዓፄ ምኒልክ እና የኢትዮጵያ አንድነት ገፅ 450 እና 451)
     ዛሬ የአደዋ ድል ስናከብር ፣እንደትላንቱ ሁሉ ለሃገራችን ብልፅግና ጠላቶች ፣ለማሳወቅ የምንፈልገው፣ እኛ ኢትዮጵያውያን በውርደት እና ባርነት ከመኖር፣  በክብር እና በኩራት ለሀገራችን ለመሞት ዝግጁ መሆናችንን ነው።
    በዚህ አጋጣሚ፣ የአሜሪካ የገንዘብ ሚኒስትር ስቴቨን ምኑቺን ባወጡት መግለጫ  “ከዚህ በፊት በነበሩ ስምምነቶች መሰረት ግድቡን በውሃ የመሙላቱ ሥራ ከመጀመሩ በፊት በአገራቱ መካከል ስምምነት መፈረም አለበት።” ቢሉንም ያልፈረምነው ሥምምነት አይመለከተንም። የግብፅን  ህዝብ በማይጎዳ መልኩ ፣ የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለአፍታም አናቆምም እንላቸዋለን።
    ለመሆኑ የአሜሪካ ገንዘብ ሚኒስቴር “ሥለ ጉና ተራራ እና ሥለ ገባሮቹ አራት ወንዞች ደህንነት ተጨንቆ ያውቃል?”” የግብፅስ መንግሥት የውሃ ምንጩ ለሆነው ለዚህ አካባቢ ሥነ ምህዳር ተንሰፍስፎ የውቃልን? ዝም ብሎ ፣ፈጣሪ በሰጠን ሥጦታ፣ “የእኔ የውሃ ድርሻዬ ፣የህን ያህል መሆን አለበት ብሎ “ሙጭጭ ማለት ” እና “ከዚህ ከጎደለ ውርድ ከራሴ “የሚል ስምምነት ፈርሙ መለትስ ከአንድ አሥተዋይ መንግሥት የጠበቃልን? … ኢትዮጵያ “በገዛ ዳቦዬ   የሚገባኝን ድርሻ ማጣት የለብኝም ።” ማለትዋሥ በየትኛው መሥፈርት ይሆን ሐጥያተኛ  አሥደርጎ እንዲህ፣ የሚያሥዶልትበት?
   ሥለ ጉና ተራራ የውሃ ጋንእነት  ካላወቃችሁ ላሳውቃችሁ።….
   የጉና ተራራ የሚገኘው  በደቡብ ጎንደር አስተዳደር ዞን ውስጥ ነው፡፡  ከደብረ ታቦር በቅርብ ርቀት ላይ ከከተመችው ታሪካዊቷ የኢንዱስትሪ መንደር ‹‹ጋፋት›› በ30 ኪ.ሜ ርቀት ላይ ፡፡  የጉና ተራራ ከባሕር ወለል በላይ 4 ሺህ 233 ሜትር ወይም 13 ሺህ 888 ጫማ በላይ ከፍታ አለው፡፡
      እስቴ፣ ጋይንት፣ ጉና ክምር ድንጋይ እና ፋርጣ የጉና ተራራን የሚያካልሉ ወረዳዎች ናቸው፡፡
      የጉና  ተራራ የአባይ ወንዝ ገባሮች የሆኑት የተከዜ እና የበሽሎ ወንዞች እንዲሁም የጣና ሃይቅ ገባሮች የሆኑት የርብ እና የጉማራ ወንዞች መነሻ ነው፡፡
      በአጠቃላይ የጉና ተራራ ከ41 በላይ ወንዞች እና ከ77 በላይ የሚሆኑ ምንጮች መነሻቸው ጉና መሆኑን የጥናት ውጤቶች ያመላክታሉ፡፡ ለዚህም ነው የዘርፉ ምሁራን የጉና ተራራን ‹‹የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ›› ሲሉ የሚጠሩት፡፡
  ይህንን እውነት ተረድቶ የአባይ ውሃ ከአመት ዓመት መጠኑ እያነሰ እንዳይመጣ ለጋራ ጥቅም በጋራ በመሥራት የግብፅን እና የኢትዮጵያን  ህዝቦች ተጠቃሚ እንደማድረግ ፣ለምን በተፈጥሮ ላይ ታላግጣላችሁ? ነገ ተጎጂ የምትሆኑት ግብፆች ናችሁ።ተፈጥሮን በተፈጥሮ እንጂ በኃይል መቆጣጠር እንደማይቻልም ዛሬ ነው፣መገንዘብ ያለባችሁ።…
 ኢትዮጵያ ግዙፍ ግድብ መሥራት ያሥፈለጋት ከድህነት ለመላቀቅ እንጂ ለቅንጦት እንዳይደለ ፣በመዘባነን፣ሰማይን በእርግጫ እያሉ የሚኖሩትም፣ ልብ ሊሉት ይገባል።
  ይህ በብዙ ቢሊዮን ብር ወጪ የሚገነባው የሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ ዕድገት የሚያፋጥን ነው። ግድቡ ሲጠናቀቅ 6ሺህ ዋት የኤልክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል።
46% ሕዝብ  ብቻ የኤሌክትሪክ ኃይል  ለሚያገኝባት ኢትዮጵያ የግድቡ አስፈላጊነት የማያጠያይቅ ነው። ከዚህ ባለፈም እያደገ ለመጣው የኢንዱስትሪ ዘርፍ ትልቅ እፎይታን የሚሰጥ ነው።
ኢትዮጵያ ግድቡ ሙሉ በሙለ ኃይል ማመንጨት ሲጀምርላት ለጎቤት ሃገራትም ኮረንቲ መሸጥ ትችላለች።
     የህዳሴ የኃይል ማመንጫ ግድብ  የብልፅግናችን ምንጭ መሆኑ ይታወቃል። ይህንን እንደአይናችን ብሌን የምናየውን  ፕሮጀክት ለማደናቀፍ መሞከር በራሱ እብደት ነው።ይህንን እኩይ ድርጊትም የኢትዮጵያ ህዝብ እና መንግሥት በዋዛ እንደማይመለከተው እና ለኢትዮጵያ ክብር ና ለህዝቦቿ ብልፅግና ሢል ማንኛውንም መሥዋትነት እንደሚከፍል እምነቴ የፀና ነው።የአባይ ወንዝ ከአድዋ  እኩል ኩራታችን ነውና!!!!!!!!
  “ክብር ፣ የሠለጠነውን የአውሮፓ ጦር አሸንፈው፣ መላው ጥቁር ህዝብን ቀና ብሎ እንዲራመድ ላሥቻሉት፣ የአድዋ ሰማዕታት !!
     ክብር   አኩሪ ታሪክ  ላለው ለኢትዮጵያ ህዝብ!!
     ክብር፣ ለመሪዋ ለንጉሥ ምኒልክ !!
     ክብር ፣ ለብልሃተኛዋ ንግሥት ለእቴጌ ጣይቱ!!

2 Comments

  1. The GERD dam is below any safety standard . To make it functional it will need major retrofitting , noway the water filling will start in this next decade since the retrofitting process by itself will take more time and more money than the actual construction is taking.

  2. Gerd dam filling is not an urgent issue which we need to mobilize towards . One billion dollars worth emergency foodaid is urgently needed for Ethiopians mostly for those who are residing in Oromia region since the Oromia regional government of Ethiopia has completely failed to properly protect the citizens from the locust invasion which is not disclosed publicly to protect the images of ODP, the extent of the locust disaster had been undermined by the authorities in Oromia region which is known to be plagued by conflicts from Ambo to Wollega which now is said to be in a brink of starvation feared to cause migrations to major cities such as Hawassa and Finfine in search of food.

    If the aid is not gotten in time from foreign donors the only choice left is said to be borrowing from international financial institutions such as World Bank and IMF in a form of loan by securing the development projects that are already underway.

    https://www.ethiopianreporter.com/index.php/article/18057

Leave a Reply to Anissa Cancel reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.