አብይ አሕመድና ኢሳያስ አፈወርቂ አደብ እንዲገዙ ምከሯቸው - አቶ ስዩም መስፍን የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር. – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

አብይ አሕመድና ኢሳያስ አፈወርቂ አደብ እንዲገዙ ምከሯቸው – አቶ ስዩም መስፍን የቀድሞ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር.

1 min read
1
አቶ ስዩም መስፍን

በቅርቡ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከኤርትራ ቴሌቪዥን ጋር ባደረጉት ቆይታ የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ጉዳይ መቋጫ እንዳያገኝ ህወሓት እንቅፋት ሆኗል ሲሉ በመተቸት ተናግረው ነበር።

ፕሬዚዳንቱ ስለ ኢትዮጵያ እና አፍሪካ ቀንድ ዘርዘር ያለ ማብራሪያ በሰጡበት በዚህ ቃለ መጠይቅ፤ የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነትም በተመለከተ “በድንበርና በባድመ ጉዳይ ላይ ብቻ ሳንታጠር በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ሪፎርም (ለውጥ) በሙሉ አቅማችን እንደግፋለን” ብለውም ነበር።

ፕሬዚዳንት ኢሳያስ “የኢትዮጵያን ጉዳይ እጃችንን አጣጥፈን የምንመለከተው አይደለም” በማለት መረር ባለ ቃል መናገራቸውን ተከትሎም የህወሓት ነባር ታጋዮችና የቀድሞ ከፍተኛ ባለስልጣናት አልወደዱትም።

“በውስጥ ጉዳያችን ጣልቃ ገብተዋል” በማለት ፕሬዚዳንት ኢሳያስን ተችተዋል።

የቀድሞ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍን እና የቀድሞ የትግራይ ፕሬዝዳንት አቶ ፀጋይ በርኸ ለየካቲት 11 ክብረ በዓል በተዘጋጁ መድረኮች ላይ ፕሬዚዳንት ኢሳያስን በግልፅ ተችተዋል።

አቶ ፀጋይ በርኸ ባለፈው ሳምንት በማይ ፀብሪ ከተማ ተገኝተው ሲናገሩ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ በኢትዮጵያ ጉዳይ “እጁን ካስገባ እጁ ይሰበራል እንጂ የሚያመጣው አንዳች ነገር የለም” ብለዋል።

“ይህ የኢትዮጵያውያን የውስጥ ጉዳይ ነው፤ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አያገባቸውም” ያሉት አቶ ፀጋይ የፕሬዝደንት ኢሳያስን ጣልቃ ገብነት “ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ሊቃወሙት ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል።

አቶ ጸጋይ በርኸImage copyrightTIGRAY TV
አጭር የምስል መግለጫአቶ ጸጋይ በርኸ

“ሃገራችንን ለማፍረስ ነው ይህን እያደረገ ያለው” ሲሉም ፕሬዚዳንት ኢሳያስን የወቀሱ ሲሆን “ሁለት ሶስቴ ያስቡበት” ሲሉም የኤርትራውን ፕሬዚዳንት አስጠንቅቀዋል።

በትናንትናው ዕለት የካቲት 8፣2012 ዓ.ም አክሱም ሲከበር በነበረው የህወሓት 45ኛ አመት ምስረታ በዓል የተገኙት አቶ ስዩም መስፍንም በንግግራቸው ጠንከር ያለ ትችት አሰምተዋል።

”ኢሳያስ አፈወርቂ ‘ወያኔን እና ወያኔ የገነባውን ሕገ-መንግሥት አፈርሳለሁ’ ማለታቸው ነውር” ብለዋል።

“ይሄንን ሕገ-መንግሥት ለማፍረስ የሚመጣ ካለ እሱ ሞሶሎኒ ነው። ሂትለር ነው” በማለት ነው መረር ያለ ትችት ያሰሙት።

አክለውም “ኢሳያስ ግማሹን የኤርትራ ህዝብ በትኖ ሲያበቃ፤ የኤርትራን ህዝብ ማስተዳደር ሳይችል ለኢትዮጵያና ለአፍሪካ ቀንድ ሰላምና ልማት ሊያመጣ አይቻልም” ብለዋል።

የኤርትራ ህዝብም፤ ኢትዮጵያውያን እያደረጉት እንዳሉት ሁሉ ፕሬዝዳንት ኢሳያስን “መጀመርያ የውስጥ ችግራችንን እንፍታ ሊሏቸው ይገባል” ሲሉ ምክር አዘል መልእክት ያስተላለፉት አቶ ስዩም “ከዚያም እንደ ህዝብ፣ እንደ ሀገራት እንደ መንግሥታት አንዱ ሌላኛው ላይ ጣልቃ ሳይገባ መስራት እንችላለን” ብለዋል አቶ ስዩም መስፍን።

ቀደም ሲል የህወሐት ፅህፈት ቤት በጉዳዩ ላይ የሚሰጠው ይፋዊ መግለጫ እንደሌለው ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።

BBC

1 Comment

  1. This is a declaration of war against Ethiopia And Eritrea from the tplf and the federal government should think twice and take a proper action to weaken Tplf once and for good with out going to War, many alternatives are their to use.

Leave a Reply to Abrham Cancel reply

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.