የታየ ደንድአ "የድል አብሳሪነት" - ጠገናው ጎሹ – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የታየ ደንድአ “የድል አብሳሪነት” – ጠገናው ጎሹ

1 min read
3

የኦሮሚያው ኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ጽ/ቤት ቃል አቀባይ (አፈ ቀላጤ) አቶ ታየ ደንድአ “በምዕራብ ኦሮሚያ በሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎች ላይ መንግሥት እርምጃ እየወሰደ ነው” በሚል ለቪኦኤ (ለአሜሪካ ድምፅ ሬዲዮ) ተናገሩ የሚል ዜና አነብኩና ቃለ ምልልሱን አዳመጥኩት ። አዳምጨ ስጨርስ በመጀመሪያ የጠየቅሁት ጥያቄ ለመሆኑ የሥራ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል (executive branch of government) የሚመለከተውን ይህን አይነት አገርን (ህዝብን) በከፍተኛ ሁኔታ በማተራመስ ላይ የሚገኘውን ጉዳይ አስመልክቶ ለምን በፖለቲካ ካድሬ በኩል እንዲነገረን ተፈለገ? የሚል ነው ። የጥያቄዬ ጭብጥ በደምሳሳው ለምን ታየ ደንድአ ተናገረ የሚል ሳይሆን  በቀጥታ የሚመለከተው የመንግሥት አካል ለህዝብ መግለፅ ሳይፈልግ ለምን በፖለቲካ ፓርቲ ካድሬ በኩል እንዲነገር ተደረገ ? ነው።

በእርግጥ የሥራ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል (executive branch of government) ብቻ ሳይሆን ህግ አውጭውን (parliament) እና ህግ ተርጓሚ ተብየውን (judiciary) የገዥው ፓርቲ ፖለቲከኞች በሚቆጣጠሩበት ሥርዓተ ኦዴፓ/ ኢህአዴግ /ብልፅግና ውስጥ እንደተዘፈቅን የምንገኝ ስለመሆናችን በሚገባ  ስለምረዳ ቢያሳዝነኝም አይገርመኝም ።

ነገር ግን እነዚህ ፖለቲከኞች “የለውጥ ሐዋርያ ነን” በሚል የሚያታልሉበትን አሠራር ትክክለኛ ለማስመሰል እንኳ አለመሞከራችው (አለመቻላቸው) የሚመነጨው የህዝብን የመገንዘብ አቅም ከደመ ነፍስ እንስሳት በታች የማውረድ (dehumanization) የፖለቲካ ጨዋታ ውስጥ ከመሆናቸው እውነታ ነው ። አዎ! የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞች መከረኛውን ህዝብ “ወሬውን የሚያቀብልህ (የሚነግርህ) ለአንተው ፍላጎትና ጥቅም የቆመው ካድሬያችን እስከሆነ ድረስ የወሬ ምንጭና ነጋሪ ጥያቄ ውስጥ ምን ጥልቅ አደረገህ” በሚል የለየለት “የህጋዊ አናርኪስት” ገዥዎች የፓለቲካ ጨዋታ ውስጥ መገኘታቸውን ለመረዳት  ጨርሶ ከባድ አይደለም ።

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን በፖለቲካ  ወለድ ወንጀል  የተጨማለቁ የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና  ፖልቲከኞች መጫወቻዎች ሆነን መቀጠል ካልፈለግን  በስተቀር ዋቢ መጥቀስ የማያስፈልገው የቀን ተቀን መሪር የፖለቲካ እውነታ ይኸው ነው ። እነዚህ የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞች ከሩብ መቶ ክፍለ  ዘመን በኋላም  “በአዳዲስ” የተለጣፊነት/የአድርባይነት/የልክስክስነት ፖለቲካ  ልክፍት በተለከፉ ፖለቲከኞችና  የፖለቲካ ድርጅቶች እየታጀቡ የማይናወጥ የፖለቲካ ሥልጣን ዙፋን በመትከል የ50ና የ60 ዓመት የማይደፈር ንግሥናን  እውን የማድረግ ቅዠት ቢቃዡ ከቶ የሚገርም አይሆንም ።

ከመግረም አልፎ የሚያሳዝነው አብዛኞቻችን በአገኘነው አጋጣሚ ሁሉ የምደሰኩረው የፖለቲካ ዲስኩርና በመፍትሄነት የምናቀርበው ሃሳብ በዴሞክራሲያዊ አርበኝነት መርህ ላይ ፀንቶ በመቆም መሠረታዊ ዴሞእራሲያዊ ለውጥ እውን ማድረግ የሚችል የፖለቲካ ድርጅትንና የድርጅቶች ህብረትን በመርዳትና በማብቃት ሥራ ላይ የሚያተኩር አለመሆኑ ነው። ከዚህ ይልቅ ሊታደስ በማይችል አኳኋን በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቁትን ኢህአዴጋዊያን ፖለቲከኞችን  “ህግ አስከብሩልን ፣ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት አሸጋግሩን ፣ በሁለንተናዊ ብልፅግና አምበሻብሹን ፣ ወዘተ” እያልን መማፀናችን  ህሊናን በእጅጉ ያሳምማል።

ታዲያ እንደ ታየ አይነቱ የፖለቲካ ካድሬ የሥራ አስፈፃሚውን የመንግሥት አካል (executive branch of government) ተክቶ የአገርንና የህዝብ ደህንነት በእጅጉ እያናጋ ስላለው ጉዳይ መግለጫ ቢሰጥ ምን ይገርማል? ምንም!

ሥራ አስፈፃሚው የመንግሥት አካል ከመደበኛው አስተዳደርና የህግ አስፈፃሚ አቅም በላይ የሆኑ አካባቢዎችን በጊዜያዊነት ሰላምና ፀጥታን የማስከበሩን ሥራ እንዲሠራ በሚል የተቋቋመውን አስተባባሪ አካል ወይም ኮማንደ ፖስት ሰላምና ህግ አስከባሪ እንጅ ኮማንድ ፖስት አይደለም (አይባልም) የሚል ማስተካከያ በፖለቲካ ካድሬ በኩል የመስማታችን  ጉዳይ የሚነግረን  የፓርቲና የመንግሥት የሥራ ድርሻ ከመቀላቀል አልፎ መንግሥት የካድሬዎች መፈንጫ ሆኖ መቀጠሉን ነው ። የተቀየረ ነገር ቢኖር የህወሃት ፖለቲከኞችን በኦዴፓ ፖለቲከኞች የመተካት የፖለቲካ ጨዋታ ነው።

ካድሬ ታየ ደንድአ “ኢንተርኔት ለምን እንደተቋረጠ አላውቅም” ይለንና “ከአካባቢው ችግር ጋር ግንኙነት የለውም” ሲል ምን እያለ እንደሆነ  እራሱም ያወቀው አይመስለኝም። ይህ መሪር ሃቅ የሚነግረን ቁም ነገር በመሬት ላይ ያለውን እውነት ሳይሆን በደካማ ህሊናቸው ውስጥ የሚያጠነጥኑትን እርካሽ የፖለቲካ ድርሰት (ትርክት) እንደ ወረደ  እየዘረገፉ በመከረኛው ህዝብ ላይ ከሚሳለቁ የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ካድሬዎች ለመገላገል ያለብን ፈተና በእጅጉ እልህ አስጨራሽ መሆኑን ነው።

የካድሬ አፈ ቀላጤው ታየ ደንድአ አሁን እየተካሄድ ያለው ፍልሚያ መጭውን ምርጫ “በሰላም” እንዲካሄድ ለማድረግ እንደሆነም ነግሮናል ። አገር  እጅግ አስከፊ በሆነ የፖለቲካ ሸፍጥ እየታመሰ ባለበት ሁኔታ ምርጫን እያሰላ እርምጃ የሚወስድ መንግሥትና ገዥ የፖለቲካ ቡድን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ያሸጋግረናል ብሎ ማሰብ ወይ የለየለት የፖለቲካ እንከፍነት (ቂልነት) ነው ወይም ደግሞ የአድርባይነት (የልክስክስነት) ፖለቲካ  ባህሪ ወይም ሰብእና ነው ። እነ ካድሬ ታየም የሚነግሩን ከእነዚህ ሁለት እጅግ አስቀያሚ ባህሪያት አንዱን ወይም ሁለቱንም መርጥን “ታሪካዊውን” የምርጫ ሂደትና ውጤት በአሜን ባይነት እንድናጅብና “የድሉ ተቋዳሾች ” እንድንሆን ነው።

ለመሆኑ ካድሬ ታየ ደንድአ ሸማቂዎችና ሽፍቶች እያለ የሚጠራቸው ቡድኖች ባንክ ሲዘርፉ፣ ንፁሃንን ሲገድሉና ሲያፈናቅሉ፣ ያሰለጠኑትን ተዋጊ (ገዳይ) ሃይል በጠራራ ፀሃይና በአደባባይ ሲመርቁና ሲያስመርቁ የክልሉ መንግሥትና እርሱ በአፈ ቀላጤነት የሚሠራበት የፖለቲካ ድርጅት እና እንዲሁም የፌደራል መንግሥት ተብየው ምን ሲያደርጉ ነበር?

ታየ ደንድአ በእራሱ የፖለቲካ ድርጅት ማለትም ኦዴፓ/ የኦሮሞ ብልፅግና ፓርቲ ወስጥ ያሉትን ኦነጋውያንን ጨምሮ ይህ ሽፍታ የሚሉት ቡድን ኦነግ በፖለቲካው ባይቀናው እስከአሁን ያለወጠውን (ያላሻሻለውን) ኦሮሚያ የምትባል አገር የመፍጠር ቅዠቱን እውን ለማድረግ እንደ መጠባበቂያ ያሠማራው አለመሆኑን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል?

በእውነት ስለ እውነት ከተነጋጋርን ይህ ተዋጊ (ገዳይ ቡድን) ከመንግሥትና በመንግሥት አካልነት ከተቀላቀለው ኦነግ አቅም በላይ ሆኖ ነው እንደዚህ በጠራራ ፀሃይና በአደባባይ በመከረኛ ህዝብ ላይ የመከራ ዶፍ የሚያወርደው?

እነ ታየ ደንድአ በሸፍጥና በሴራ የተበከለውን የእራሳቸውን የፖለቲካ ጓዳ (ኦነግን ጨምሮ) ለመፈተሽ የሚያስችል  የሞራልና የፖለቲካ አቅም ሲከዳቸው “ሽፍቶችን ድራሻቸውን እያጠፋናቸው ነው” የሚል ሸፍጠኛ ፕሮፓጋንዳቸውን ነው ደጋግመው የሚነግሩን ። በርካታ ተዋጊውን የመንግሥት አካል ያስደረገው ኦነግ ከእርሱ ተነጥለው በጥቅ ትግል ላይ ነን የሚሉ “ተዋጊዎቹን” በገልፅና በቀጥታ ማውገዝ ቀርቶ ትርጉም ያለው ሂሳዊ አስተያየት ያለመሠንዘሩን አንድምታ ጤናማ የፖለቲካ ጨዋታ ነው ብሎ ለማመን የሚቻል አይመስለኝም።

የእኛ (ኬኛ) እያሉ በስሙ ከሚነግዱበት ከኦሮሞ ማህበረሰብ ወይም ለእርካሽ ፖለቲካቸው ይጠቅመናል ከሚሉት ጉዳይ ጋር በቀጥታ የማይገናኝ አገራዊ ራእይና ዓላማ/ግብ ጉዳያቸው ያልሆነ  እንደ ታየ አይነት  የኦሮሞ ፖለቲከኞች  በካድሬነት ለሚያገለግሉት ገዥ ቡድንና መንግሥት ቆንጅዬ ገፅታ ለማላበስ ይረዳል የሚሉትን ድርሰት ፅፈው ሲያስነብቡት ወይም በድምፅ ሲያሰሙት ለምን?እንዴት? ማን/እነማን? በነማንና ለነማን ብሎ ሳንጠይቅ እንደ ወረደ ተቀብሎ “እጠቅሳለሁ ወይም ታየና መሰሎቹ እንዳሉት” በሚል  አደንቋሪ ዲስኩርና መዋዕለ ዜና  ትንታኔ  መልሶ  መከረኛውን ህዝብ ከማደነቆር የባሰ የፖለቲካ ህመም የለም።

የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና የሸፍጥ ፖለቲካን የሚያራግብ ምርኮኛ ጋዜጠኛ እና ምሁር ተብየ ከሚተራመስበት የፖለቲካ አዙሪት ወጣን ስንል ተመልሰን እየተዘፈቅንበት የመሆናችንን ሃቅ ተቀብለን የሚበጀውን ማድረግ ካልቻልን በጠቅላይ ሚኒስትሩ በኩል እንደተነገረን የ50ና 60 ዓመት የሸፍጥና የሴራ የፖለቲካ ሥርዓት ከፊታችን ይጠብቀናል ።

እነዚህ የኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና የበላይ ፖለቲከኞችና ካድሬዎች ሩብ መቶ ክፍለ ዘመን ከዘለቁበት የበሰበሰና የከረፋ ተራ የፖለቲካ ሸፍጥ ፕሮፓጋንዳ (propaganda of political hypocracy) ሊወጡ አልተቻላቸውም ።አይቻላቸውምም ። ለምን ቢባል የተጠናወታቸው የፖለቲካ ባህሪና አስተሳሰብ ጨርሶ ካልተወገደ በስተቀር ከቶ ሊድን የማይቻለው የካንሰር አይነት ነውና ።

ታየ ደንደአም በዚሁ ክፉ የፖለቲካ በሽታ በተለከፈው ኦዴፓ/ኢህአዴግ/ ብልፅግና ውስጥ የሚገኝ ብቸኛ  እውነት ተናጋሪና የምሥራች አብሳሪ ሊሆን እንደሚችል ለማመን የማይገዳቸው ወገኖች ሊኖሩ ቢችሉም መሬት ላይ እየሆነና እየተደረገ ካለው ግዙፍና አስቀያሚ  እውነታ  አንፃር ለማሳመን የሚችሉበት  አመክንዮታዊ አቅምና ችሎታ ግን ከቶ ሊኖራቸው አይችልም

በእርግጥ በእውነትና ስለ እውነት በፅዕናት የሚቆም የፖለቲካ ሃይል ለመፍጠርና ለማብቃት ከተማሩ ልጆቹ ማግኘት ያለበትን እገዛ በመጠንም ሆነ በጥራት ለማግኘት ያልተሳካለት መከረኛ ህዝብ የሸፍጠኛ ፖለቲከኞች ባዶ ዲስኩርና ዜና መዋዕል  ሰለባ ቢሆን ከቶ የሚገርም አይደለም።

“ታየ ደንድአ ከሌሎች የፖለቲካ ጨዋታ ጓዶቹ በተለየ ሁኔታ ግሩም አነጋገር ተናገረ ወይም ፅሁፍ አስነበበ” የሚለው እራስን አደንቁሮ ሌላውንም የሚያደነቁር የፖለቲካ ወግ (ትርክት) ፊደል ቆጠርኩ በሚለው ወገኔ ሲስተጋባ ከማየትና ከመስማት የባሰ የመማር መሠረታዊ ትርጉምና ዋጋን  ዝቅ የሚያደርግ የፖለቲካ ሰብእና የለም።

እየተፈራረቁ በድንቁርና እና በግፍ ሲገዙት ከኖሩትና አሁንም ከጫንቃው ላይ ካልወረዱለት ግፈኛ ገዥ ቡድኖች ለመገላገል በንቃትና ፣ በሥነ ልቦና እና በድርጅታዊ ልዕልና  የነፃነትና የፍትህ ሥርዓትን እውን ለማድረግ የሚያስችል  አቅምና ችሎታ እንዲኖረው በሚያስችል ሁኔታ ያላገዝነውን  ህዝብ/ህብረተሰብ “ይህን ወይም ያንን ማድረግ አለበት” እያልን የፖለቲካ ዲስኩራችን መንደርደሪያ ፣ ማድመቂያና  ማሳረጊያ የማድረጋችን የፖለቲካ አስተሳሰብ ውድቀት ቆም ብለን ለመፈተሽ ለምን እንደ ተሳነን ለመረዳት ያስቸግራል ።

በምርኮኝነት “ለለውጥ መሪዎች (ሐዋርያት)” አገልጋይነት የተሰጡ የሜዲያ ጋዜጠኞችን ጨምሮ አንዳንድ ወገኖች ታየ በድርጅቱ (ኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና) ተራ የፖለቲካ ተውኔት ውስጥ የኢያጎን ገፀ ባህሪ ተላብሶ የሚተውንውን ተውኔተ ፖለቲካ ታየ እንደተናገረው ወይም እንደ ፃፈውበሚል ለንግግራቸው (ለአስተያየታቸው) ትክክለኝነት በዋቢነት ሲጠቅሱ መስማት ምን ያህል የሸፍጠኞች መጫወቻ አሻንጉሊቶች እንደሆን ነው የሚያሳየው።

በድንቁርና አደንዝዘውና ሲያሻቸውም በአስከፊ የፖለቲካ በትራቸው (ዱላቸው) እየቀጠቀጡ  ሲገዙት የኖሩትን መከረኛ ህዝብ  አሁን ደግሞ   በእንደ ታየ አይነት ኢያጎዎች አማካኝነት የሚነግሩንን  ዜና ፖለቲካ ከምር እየወስድን ከሆነ ቂልነታችን ገና ብዙ የመከራና የውርደት ዓመታትን እንደሚያስቆጥረን ከቶ አያጠራጥርም ።

ታየ በቀጥታ ከሚመለከተው መንግሥት ተብየ አካል ወይም ክፍል በላይ አይዞን የጥፋት ሃይሎች እየተደመሰሱ ነው በሚል  “የሚያበስርልልን ብሥራት”  ያለምንም ተጠየቅነት እየተቀበልን ታየ እንደተናገረው ወይም እንደ ፃፈው”  እያልን በዋቢነት በመጠቀስ በመሃይምነትና በግፍ አገዛዝ  የኖረባቸው ዘመናት ያበቁ መስሎት በጎና እውነት የሚያስመስሉ ቃላትን በሰማ ቁጥር በስሜት የሚነጉደውን መከረኛ ህዝብ ማደነጋገር የለየለት ሞራላዊና ፖለቲካዊ ውድቀት ነው።

“የለውጥ ሐዋርያነቱን” በሚመራው ኦዴፓ  ውስጥ እንደ ታየ አይነት  ፖለቲከኞች ስለአሉ ለውጡ ከመደናቀፍ ይተርፋልና (ይድናልና) ሃሳብ አይግባችሁ”   የሚል አይነት የፖለቲካ አስተሳሰብ  ሰለባ ከመሆን  የከፋ  ድህነትና ቂልነት የለም።

እንኳን የነታየ የማስመሰልና የማዘናጋት ማለትም   የለውጡ መሪ የሆነው ኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና ድል እየቀናው  አድርጎ ለማሳየት  የሚደረግ የፖለቲካ ጨዋታ የህወሃት ያዙኝና ልቀቁኝ ባይነትም በኦዴፓ/ኢህአዴግ/ ብልፅግና ሥርዓት ውስጥ የሚገባኝ ቦታ ካልተሰጠኝ ተያይዘን እንጠፋለን  የሚል ማስፈራሪያን እንደ መደራደሪያ ለመጠቀም እንጅ የእውነት የፖለቲካ ጨዋታ ባህሪና አካሄድ አይደለም  ብሎ መገመት ሴራኛ ግምት ሊሆን አይችልም ።

ለዘመናት የመጣንበት በሸፍጥና በሴራ የተበከለ የግፍ አገዛዝ ለምንና እንዴት በቂ ትምህርት (ተሞክሮ) እንዳልሆነን ለመግለፅ በእጅጉ ይከብዳል ። አዎ! የእኩይ ፖለቲካ ልክፍተኞች በሸፍጥና በሴራ የተበከለ ፖለቲካቸውን ስሜት በሚኮረኩሩ ዴስኩሮችና መዋዕለ ዜናዎች እየጠቀለሉ ሲያጎርሱን ለምንና እንዴት እንደማያስታውከንና ከዚህ እራስን ከደመነፍስ እንስሳት በታች ከሚውል እኛነት ለመውጣት  ከምር በቃ ለማለት እንደተሳነን  ለመረዳት በእጅጉ ከባድ ነው ።

ነፃ የሚያወጣንን የእኛው የእራሳችን የሆነን አስተሳሰብና አቋም ከማራመድ ይልቅ የሸፍጠኛ/የሴረኛ ፖለቲከኞችን ዲስኩርና መዋዕለ ዜና “እርሱ/እርሷ/እነርሱ እንዳሉት” የሚል ጥቅስ እያመነዠኩ ከመቀጠል የባሰ ውድቀት የለም። መሠረታዊ ዴሞክራሲዊ ለውጥ ማለትም በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የተዘፈቀው ኦዴፓ/ኢህአዴግ/ብልፅግና በበላይነት  የማይዘወረው  የፖለቲካ  አስተሳሰብና  አካሄድ ላይ ለማተኮር ምነው ተሳነን ?   እውነተኛውን መልስ ለመመለስ የየእራስን የህሊና ጓዳ በእውነት ስለ እውነት መፈተሽን ግድ ይላል ።

በእጅጉ የሚያሳዝነው ግን ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ የሚያበቃንን የፖለቲካ ድርጅት ወይም የድርጅቶች ህብረት መፍጠርና ማብቃት በምንችልበት አጀንዳና አካሄድ ላይ ማተኮሩን ትተነው ለመግለፅ በሚያስቸግር አኳኋን  በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበሰበሰውና የከረፋው ሥርዓተ ኢህአዴግ የአደረጃጀት ቅርፅና ስም በመቀየር የሚሰጠንን እኩይና አዘናጊ  አጀንዳ /ፕሮፓጋንዳ ከማመንዠክ አስከፊ አዙሪት አለመውጣታችን ነው

ይህ እጅግ አንገት አስደፊ የፖለቲካ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አብቅቶ እንደ ሰውና እንደ ዜጋ በነፃነትና በእኩልነት የምንኖርበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ ለመታገል አበረታች የሆኑ እንቅስቃሴዎችን  የሚያደርጉትን እና ለማድረግም እልህ አስጨራሽ ሂደት ውስጥ የሚገኙትን ወገኖች በገንቢ ሂስ የታጀበ የሞራል፣ የሃሳብ (የእውቀት) ፣ የገንዘብ እና የማቴሪያል ድጋፍ ለማድረግ ግድ ከሚለን ሁኔታ ውስጥ ነው የምንገኘው።

አዎ!  የፖለቲካ ተለጣፊነትን ወይም አድርባይነትን ወይም ልክስክስነትን ተፀይፈው ለመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ በአርበኝነት ሰብእና በመቆም  ትግላቸውን ከሲቪክ ንቃናቄነት ወደ ፖለቲካ ፓርቲነት ለማሸጋገር እልህ አስጨራሽ ትግል ውስጥ የሚገኙትን እነ እስክንድር ነጋን እና ቀደም ብለው ከዚሁ ተልእኮ አንፃር እንቅስቃሴ የጀመሩትን ድርጅቶችና ህብረቶች ለማገዝና ለድል ለማብቃት ይቻል ዘንድ ከአድማስ እስከ አድማስ የሚያስተጋባ ጥሪ ላይ  የምንገኝ መሆኑን ተረድቶ ለዚሁ የሚመጥን ሁለንተናዊ አስተዋፅኦ በማድረግ የመልካም ዜግነት (ኢትዮጵያዊነት) ግዴታችን እንወጣ !

ለሩብ መቶ ክፍለ ዘመን የተዘፈቁበት አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል ባቃዣቸው ቁጥር የሚደሰኩሩትን ዲስኩር እና የሚያሰራጩትን መዋዕለ ወሬ (ዜና) እንደ ወረደ በመቀበል መልሰን መከረኛውን ህዝብ የማደንቆራችን ክፉ የፖለቲካ ልማድ ይብቃን !

 

3 Comments

  1. I agree with your observation and judgement of Taye Danda’a and the ruling clique. The degradation of intellectualism and the political decadence is indeed alarming. But how immune are you from the ills you diagnose on others? Taye is a semi-literate political cadre, who can not see his own self contradictions and the fallacy of his illogical and hypocritical assertions. On the other hand, you commend Eskindir, who is even less objective and more divisive in his political rhetoric. He labels Oromos as terrorists and Muslims as non-Ethiopians, alienating more than 60% of the population. How can such a person be a saviour of Ethiopia, or do you mean Oromos and muslims are not part of your “Ethiopians”??
    Yihim yeATeqalay beEwqet na bePoletika yemezqeTu akal new!!

  2. Dear Abba Caalaa, thank you for your comment . But you deliberately distorted who Eskidir is and what he says . Yes, as any human being Eskindir cannot be absolutely immune from making mistakes. But it is absolutely wrong to distort with words and sayings he has never heard saying . a) Can you find words or expressions that he really used to the extent of saying that Muslims are not Ethiopians and convince me ?b) Can you find any word or expression of Eskindir that considers all Oromo are terrorists or all qerros are terrorists and convince me please ? C) Do you really believe that this kind of total distortion of each others’ words and positions helpful to get out from the very terrible quagmire we are trapped in ?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.