የፍቅርና መተሳሰብ ተምሳሌት የሆነውን የልደት በዓል ስናከብር፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ለሀገር ሰላም በጋራ በመቆም ሊሆን ይገባል – የኃይማኖት አባቶች – ዘ-ሐበሻ (ZeHabesha): Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

የፍቅርና መተሳሰብ ተምሳሌት የሆነውን የልደት በዓል ስናከብር፣ የተቸገሩ ወገኖችን በመርዳትና ለሀገር ሰላም በጋራ በመቆም ሊሆን ይገባል – የኃይማኖት አባቶች

1 min read


ፍቅርና መተሳሰብ ተምሳሌት የሆነውን የገናን በዓል ስናከብር ችግረኛና አቅመ ደካማ ወገኖችን በማሰብ ለሀገር ሰላምና አንድነት በጋራ በመቆም እንዲሆን የተለያዩ የሐይማኖት አባቶች አስታወቁ፡፡

ነገ የሚከበረውን የልደት በዓል ምክንያት በማድረግ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን፣ የኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተክርስቲያንና የኢትዮጵያ ወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያን የኃይማኖት መሪዎች ለእምነት ተከታዮቻቸው የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የኃይማኖት አባቶቹ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት በዓሉን ስናከብር የተቸገሩና አቅመ ደካማ ወገኖችን ማሰብ ይኖርብናል፣ አብሮ መብላት የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው ለሌለው መስጠት ይገባዋል ብለዋል።
የኃይማኖት አባቶቹ አክለውም ኢትዮጵያ አሁን ላይ በተለያየ ምክንያት የሰላም እጦት እየተፈታተናት መሆኗን ጠቅሰው ሁሉም አካላት ህዝብን ከሚከፋፍሉና ከሚያራርቁ ነገሮች ተቆጥበው ለአገር ሰላም መረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባቸዋል ብለዋል።
የኃይማኖት አባቶቹ አክለውም ህዝቡም የአገሩን ሰላም መጠበቅ እንደሚገባው አሳስበው፤ ሰላም የሚረጋገጠው ደግሞ በሁሉም አካላት ርብርብ በመሆኑ ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል።
የሀይማኖት መሪዎቹ በመጨረሻም በህመምና የአልጋ ቁራኛ ሆነው በየሆስፒታሉ ላሉ ምህረትን፣ በየማረሚያ ቤቶች ላሉ መፈታትን፣ ላዘኑት መፅናናትን፣ ለተቸገሩ እርዳታን፣ ከቤታቸውና ከቀዬአቸው ለተፈናቀሉ መሰብሰብን ተመኝተው፤ በአገር ድንበርና ፀጥታ በማስከበር ስራ እንዲሁም በውጭ አገራት ለተሰማሩ ኢትዮጵያዊያን ሁሉ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
(ኢፕድ)