እሳት አቃጠለኝ! - በላይነህ አባተ | ዘ-ሐበሻ: Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

እሳት አቃጠለኝ! – በላይነህ አባተ

1 min read

ጠላቴ ሌት ተቀን ሴራ ሲያሴርብኝ፣
በጨለማው ዘመን ብርሃን ከጅሎኝ፣
አጠንክሬ አካሌን ጨምቄ አይምሮዬን፣
በአስታቡልቡል ዘዴ እሳትን ፈጠርኩኝ፡፡

የፈጠርኩት እሳት እኔን እያሞቀኝ፣
ጨለማን ገሽልጦ ሌባውን ሲያሳየኝ፣
ድል ስላበሰለ ለዓመታት ደስ አለኝ፡፡

የድሉን እንጀራ ተምጣድ ሳልስበው፣
እባብ አፍ አውጥቶ ኢሳት ሲሳይ ሲለው፣
እንደ ሄዋን ስቶ ወዲያው አሳረረው፡፡

እንጨት ለቃቅሜ የቀለብኩት እሳት፣
ዕጸ-በለስ ጎርሶ እባብ የጠራው ለት፣
እሳቱ ሲሳይ ነው ይማሰል ያለ ወቅት፣
በነበልባል ምላስ ገረፈኝ በክህደት፡፡

በለስ የቀመሰ ትዕዛዝን አፍርሶ፣
እባብን የላሰ ሰማእት አምላክ ክዶ!
መወርወሩ አይቀርም በጥንተ ሐብሶ!

ድሮም እኔ አማረ እጄ አመድ አፋሽ ነው፣
የፈጠርኩት እሳት እያቃጠለኝ ነው!

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)
የካቲት ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.