ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር አቶ አሻድሊ ሃሰን | ዘ-ሐበሻ Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር አቶ አሻድሊ ሃሰን

1 min read
ግልጽ ደብዳቤ ለክቡር አቶ አሻድሊ ሃሰን
የቤኒሻንጉል ጉምዝ ብ/ክ/መ ርዕሰ–መስተዳድር
አሶሳ፣ ኢትዮጵያ
ጉዳዩ፡– ኃላፊነትዎን በገዛ ፈቃድዎ እንዲለቁ ስለመጠየቅ፣
ክቡርነትዎ እንደሚያውቁት የሚመሩት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በተለይም የመተከል ዞን ዛሬም እንደትናንቱ የንጹሃን አማሮችና አገዎች መታረጃ ቄራ ሆኖ ቀጥሏል። እርስዎን ጨምሮ በተለያየ የኃላፊነት ደረጃ የተቀመጡ የክልሉ አስተዳዳሪዎች ለደረሰው ሰብዓዊና ቁሳዊ ጥፋት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታችን የተፈጸመ ዕልቂት አድርገው በመውሰድ ያገጠመውን ወይም እያጋጠመ ያለውን ችግር ከሥር መሰረቱ በመለየት፣ በመገንዘብ፣ በመተንተን፣ የተለየ መፍትሄ አማራጭ/አማራጮችን ቀርጸው ወደ ተግባራ በመግባትና ጥብቅ የክትትልና ቁጥጥር አመራር ለእልቂቱ ዘላቂ መፍትሄ መስጠት ይህን ለማድረግ የሚያስችል የአመራር ቁመና ከሌላቸው ደግሞ በራሳቸው ፈቃድ ኃላፊነታቸው በመልቀቅ ለተሻለ መሪ ማስረክብ ቢገባቸውም ይሄንን ማድረግ ግን አልቻሉም።
የኢትዮጵያ ሕዝብ “ሥልጣንን የመግራት ባኀል” ባለመገንባቱ ችግሩ የእርስዎ ወይም የክልሉ ሳይሆን አገራዊ መሆኑን እገነዘባለሁ። ወደ አመራርነት የመጡ ግለሰቦች ሹመቱን ለሰጣቸው አካል ፖለቲካዊ ታማኝ ሆነው በመገኘታቸው ብቻ ኃላፊነት (Responsibility) ሲቀዳጁ ኃላፊነትን ተከትሎ የሚመጣ ተጠያቂነት (accountability) ግን የለባቸውም – ፖለቲካዊ ታማኝነት የሹመት አልፋና ኦሜጋ ነው  ልጓም አልባ የሆነው አገራዊ ሥልጣን እንዲሁም ሹመት የተሰጣቸው ግለሰቦች ለሹመት ያላቸው የተንሸዋረረ አረዳድ ሹመኞች “ለተመሳሳይ ችግር ተመሳሳይ ሰበብ እየደረደሩ” በአልጋቸው (ወንበር ለማለት ይከብደኛል የሚቀጥሉበት ኑባሬ የአገራችን መገለጫ ሆኗል – መራራ ሐቅ
እርስዎ እንደሚገነዘቡት አንድ የበላይ መሪ የሚመራውን ተቋም/ድርጅት/ክልል/… ወዘተረፈ እያንዳንዷን ዕለታዊ ተግባራትን በዝርዝር እንዲከታተል ወይም እንዲረዳ ባይጠበቅበትም (በአቅምና በጊዜ ውስንነት) በመሪነት ስለተቀመጠበትን ተቋም ጥቅል የሆነ ዕይታና አረዳድ (aka Helicopter View and understanding) ሊኖረው የግድ ነው። በዚህ አግባብ እርስዎ በበላይነት በሚመሩት የቤኒሻንጉል ጉምዝ ብ/ክ/መ በአማራና አገዎች ላይ ተደጋጋሚና አሳዛኝ የዘር ጭፍጨፋ (Ethnic cleansing) እየተፈጸመ ነው።
ይሁን እንጂ እርስዎና የእርስዎ ካቢኔ ለሚደርሰው ተደጋጋሚ የዘር ጭፍጨፋ ተጠሪዎች “አኩራፊው ህወሃት፣ ከማዕከላዊ መንግሥት ተባሮ መቀሌ የመሸገው ህወሃት፣ የህወሃት ጁንታ፣ ጥቅማቸው የተነካባቸው የህወሃት ተለላኪ የሆኑ ታጣቂዎች፣ የኦነግ ሸኔ ታጣቂዎች፣ አኩራፊ የቀድሞ የክልሉ ባለሥልጣኖች፣… ወዘተረፈ” የሚሉ የተለያዩ የሚመስሉ ነገር ግን ተመሳሳይ የሆኑ ‘ስበቦችን’ ከመደርደር ውጪ በቡድንና በግለሰብ ደረጃ ለተፈጠረው ችግር ተጠያቂ ማድረግና ለችግሩ የመጨረሻ እልባት ማበጀት ባለመቻሉ የዘር ጭፍጨፋው ደግሞ ደጋግሞ የሚከሰት በመሆኑ ሰቆቃው እንዲለመድ ተደርጎ ዛሬ ዛሬ ትኩረቱና ውይይቱ ሰቆቃው መሆኑ ቀርቶ በሰቆቃው ላይ ባጋጠመው አሃዝ (number of casualities) ላይ ሆኗል።
Henry Cloud የተሰኙ ጸሐፊ ‘የተፈጸመን የትኛውንም ድርጊት የሚክዱ፣ የሚያሳንሱ እንዲሁም በሌላ ሦስተኛ ወገን ላይ የሚደፈድፉ ሰዎች መፍትሄ ማምጣት የማይችሉ ‘አድሮ ቃሪያ’ ናቸውና ሊወገዱ ይገባል (People with a style of denial and blaming are definitely on the list of unsafe people to avoid) እንዲሁም ‘የዓሳ ግማቱ ከአናቱ (the fish sting from the head) በሚለው አገራዊ ብሂላችን መሰረት እርስዎ ለክልሉ ሕዝቦች ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ “አቅምዎ በፈቀደልዎት መጠን” ላበረከቱት አስተዋፆ እያመሰገንኩ ከርዕሰ–መስተዳድር ኃላፊነትዎት በፈቃድዎ መልቀቂያ አስገብተው ሥልጣን በመልቀቅ ታሪክ ይሰሩ ዘንድ እማጸንዎታለሁ።
ሠላም ለሰው ልጆች ሁሉ – ሻሎም
ረዳት ፕሮፌሰር ጌትነት አልማው ጥሩነህ
ባህርዳር

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.