" ኦሮማይ ! "  በቋንቋ ና በዘር መቧደን አከተመ፡፡… - መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ | ዘ-ሐበሻ Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

” ኦሮማይ ! ”  በቋንቋ ና በዘር መቧደን አከተመ፡፡… – መኮንን ሻውል ወልደጊዮርጊስ

1 min read
1

አንድ ባለፀጋ የሆነች አገር፣ በአፍሪካም ትኑር፣ በላቲንአሜሪካ፣የበዙትልጆቿ በእውቀት ባለመበልፀጋቸውና በጥበብ ባለመካናቸው የተነሳ በድህነት ውሥጥ ለዘመናት ልትዳክር ትችላለች ከዚህ እወነት አንፃር የኢትዮጵያ በድህነት ውሥጥ ለዘመናት መዳከሯ አያሥገርምም።የሚያሥገርመው አገራችን በድህነት ውሥጥ ላለፉት ሺ ዓመታት ስትዳክር የኖረችው፣ከእውቀትና ከጥበብ እንዳትወዳጅ ባደረጓት የራሥዋ ሥግብግብ ባንዶች ከጠላቶቻችን ጋራ፣በጥቅም ተገዝተው ግምባር ቀደም በመሆን ከፍተኛ ትብብር በማድረጋቸው ነው።

ታሪክ እንደሚመሰክረው ፣ባንዳነት ወይም ቅጥረኝነት እና ለሆድ ሲሉ ብቻ፣ለሌሎች ጥቅም እሥከሞት የኢትዮጵያን ጠላቶች ማገልገል እጅግ ተንሰራፍቶ የታየው ከ1928 እሥከ 1933 ዓ/ም ባለው የሞሶሎኒ ወረራ ግዜ ነበር።

በዚህ የኢጣሊያን ወረራ ወቅት ፣ባንዳነት በእጅጉ የተሥፋፋው፣ብዙሃኑ ዜጋ ከእውቀትና ከጥበብ በመራቁ የተነሳ ፣በቀላሉ በሐሰተኛ ፕሮፖጋንድ፣በመወናበዱም ጭምር ነው።

ከጦርነቱ በኋላ ንጉሱ እውቀት በአገር እንዲሥፋፋ፣ጥበበኛ እንዲከበር እና ጠቢባን እንዲበዙ ጥረት አድርገዋል ( ባንዳዎችን ሳይለዩ ) ።ንጉሡ ለሥልጣናቸው ቀናኢ ከመሆን በዘለለ የሚታይባቸው የጎላ ድክመት አልነበረም። ይህን ሥል እንደሚከተሉት የገባር ሥርዓት ፣ህዝብን የሳቸው የግል ንብረት እንደሆነ አይቆጥሩም ፣ማለቴ እንዳልሆነ ይታወቅልኝ።

ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣የገባር ሥርዓተ ማህበር በኋላ፣ወደመንግሥት ሥልጣን የመጡት መንግሥታት ማለትም የደርግና የወያኔ አገዛዛቸው ፍፁም የተለያየ ነበር።

ደርግ በሶሻሊዝም ርእዮት አሥገዳጅነት የጋርዮሻዊ አሥተሳሰብን ለመትከል በእጅጉ ጥሯል።እርግጥ ነው የእያንዳንዱን ዜጋ የእውቀት ብልፅግና እና ጥበብ ለማሳደግ ባጋጠሙት ጦርነቶች ምክንያት እንዳልቻለ ይታወቃል።ለአገሪቱ በሥልጣኔ መመንደግ ቀና ፍላጎትና ዝግጁነት ቢኖረውም የወቅቱ የዓለም ቀዝቃዛ ጦርነት አንድ ኢንች እንዳይራመድ አድርጎት እንደነበርም አይዘነጋም።ይሁን እንጂ የደርግ መንግሥት በወቅቱ በነበረው የማርክሲዝም ኃይማኖት ሰበብ ጨካኝ እና ገድሎ ፎካሪ አልነበረም ማለት አይቻልም።..( የይርጋ ዱባለን ቀረርቶ ያሥታውሷል።)

እርግጥ ነው፣እንደደርግ ያልተረጋጋ፣ከወዲህ በወያኔ ፣ከወድያ በሻብያ ፣ከውሥጥ ደግሞ በሥርዓቱ ተቃዋሚዎች አበሳውን ያየ፣ቻይ ጫንቃ ያለው መንግሥት በኢትዮጵያ ውሥጥ ተፈጥሮ አያውቅም።ደርግ በታላቅ አበሳና ፍዳ ውሥጥ ነበር ፣ አገርን ሲመራ የነበረው።በዛ ታሪክ በመዘገበው የበዛ ፍዳ ውሥጥ ግን ህዝቡ የእውቀት ብልጭታ እንዲያይ፣በመሰረተ ትምህርት ሚሊዮኖች ማንበብና መፃፍ እንዲችሉ በማድረጉ ዓለም አቀፍ አድናቆት ማግኘቱም መካድ የለበትም።

ዘመነ ወያኔ ግን፣የእነ እንብለው ወይም በሰው አምሳል የተፈጠሩ አውሬዎች ዘመን ነበር።በጠመንጃ አፈሙዝ የተከሉት ሥርዓትም፣ሰው ያለልፋት በምላሥ ጉልበት ብቻ የተቀማጠለ ኑሮ እንዲኖር የሚፈቅድ ነበር።

በ27 ዓመታት የጠመንጃ አፈሙዝ አገዛዛቸውም ምን ያህል ሥግብግብ፣ይሉንታ ቢሥ ፣ ርህራሄ አልባ ና ፀረ ኢትዮጵያ መሆናቸውን በተግባር አሳይተዋል።

አሣሪ (ጠርናፊ) በሆነው የካድሬ አገዛዛቸውም፣ለእውቀትና ለጥበብ ግድ እንደሌላቸው ከማሳየታቸውም በላይ ፣የፓርቲው ታማኝ አባል እሥከሆንክ ድረሥ ከፈለጉ ከጥበቃ ላይ አንሥተው ሚኒስትር ሊያደርጉህ እንደሚችሉ በአደባባይ ያለ ሃፍረት የተናገሩ ናቸው።

በዚህ ሀገር ና ትውልድ ገዳይ ድንቁርናን በሚያበረታታ የጠርናፊ ካድሬ አሥተሳሰብም ለ27 ዓመት ይህቺ አገር ሥትመራ ነበር።በዘላቂ ጥቅም ላይ የተመሠረተው የኃያላን መንግሥታት ርእዮትም ገዢዎቻችንን ዜጎችን በቡድን አሥተሳሰብ በኃይል ጠርንፈው እንዲገዙ አሥችሏቸዋል።

ለዘላቂ ጥቅማቸው ሲሉ፣ለጠርናፊው ወያኔ አገዛዝ ጉልበታማነት፣ቱጃሮቹ የምዕራብና የኢሲያ መንግሥታት መንግስታት ጭምር ትልቁን ሚና እንደነበራቸው አይዘነጋም።የእኛ በኢኮኖሚ መበልፀግም የእነሱ ሞት የሚመሥላቸው ሥግብግብ መንግሥታትም የዘራፊዎቹ መሠሪ እቅድ ተባባሪ ሆነው ተገኝተዋል።

በተፈጥሮ በምንጋራው ሀብት፣በአባይ ምክንያት ሳንጠላቸው የጠሉንም ፣በእሳት ላይ ነዳጅ በመጨመር ብቻ ሳይሆን እሳት በመፍጠር እንደሚታወቁ ሲያቃጥሉን እነደነበር ታሪክ ይነግረናል።

ታሪክ እንደሚያሥረዳን ፣የግብፅ መንግሥታት፣በገንዘብና በወታደራዊ ሥልጠና፣በትጥቅና ሥንቅ ጭምር የራሳችንን ዜጎች አደራጅተው ኢትዮጵያ በነገድ እንድትከፋፈል ለማድረግ በብርቱ ጥረዋል።የኃይማኖትና የጎሣ ቡድን እንዲፈጠር በማድረግም ሰው ከሰው ተራ ዝቅ ብሎ አውሬ እንዲሆን ለዓመታት ሰርተዋል።

ዛሬም ይህ እኩይ እና መሠሪ ዓላማቸው ቀጣይነት እንዲኖረው በብርቱ በመጣር ላይ ይገኛሉ።

እርግጥ ታሪካዊ ጠላቶቻችንም ሆነ ማሥተዋል የልፈጠረባቸው የበለፀጉት አገራት ቱጃሮች ዋና እና ተቀዳሚ ፍላጎታቸው፣በዝበዛና ዘረፋ መሆኑ የታወቀ ነው።በየትም አህጉር፣ደካማ ሆኖ ግን በተፈጥሮ ሀብት በልፅጎ ያገኙትን አገር ሁሉ ከሚገኝበት የድህነት አረንቋ እንዳይወጣ አንገቱን ያንቁታል።ሐሰተኛ ትርክቶችን በመፍጠር ብቻ ሳይሆን ኃይማኖትን ቡድናዊ በማድረግና በመከፋፈል ብሎም ከመሐል ተንኳሽ በመፍጠር እርስ በእርሱ እንዲጋደል ያደርጉታል።ሀገሩ በከርሰ ምድሯ ያከማቸችውን ጥሬ ሀብት ለመበዝበዝ ሲሉም፣በጎሣዎች መካከል ከዘመናት በፊት የነበረን ያለመግባባትና መጠፋፋት በመቆሥቆሥ ትውልዱ በበቀለኝነት እጁን በወገኑ ላይ እንዲያነሳ ይቆሰቁሱታል።

ይህን የሚያደርጉት ከጥበብ እና ከእውቀት የራቀ ዜጋ በብዛት እንዳለን ሥለሚገነዘቡ ነው።ይህ ያልተማረ ና የዋህ የሆነ ፣ ጥቂት የማይባል ዜጋ የእያንዳንዱ አገር ግዛት፣ትልቅ አገር ለመመሥረት በቆረጡ ጀግና ሰዎች የመሰዋትነት ተጋድሎ ሀገር  እንደተገነባች ታሪክን አንብቦ ያልተረዳ ነው።በዚህ ምክንያትም በቀላሉ ለሐሰተኛ ትርክት እጁን ይሰጣል፡፡የአገሩ የኢትዮጵያ ሥሞ በዓለም ከፍታ ላይ የወጣው በጀግና ልጆቿ ተጋድሎ እንደሆነ የሚገነዘበው የበዛ አይደለም።በገዛ ታሪካችን ትምህርትም እንዳንኮራ ተደርገን እጅግ ጠበን እነድንቀረፅም  ባለፉት 27 ዓመት  ተደርጓል።በትምህርት ቤት ውሥጥ የኢትዮጵያ ታሪክ የሚባል ትምህርት በመደምሰሱ ራሳችንን ለማወቅ እንዳንችል ተደርገን ነበር።…

በዚህ ሰበብም ትላንት ቅኝ ገዢዎችን ያንቀጠቀጡ እና ይህቺን ውብ አገርያ ሥረከቡንን የአገር ኩራት የሆኑ ጀግኖቻችንን እና መሪዎቿን በሐሠተኛ ትርክት ሥማቸውን በማጠልሸት የአንዱ ጎሣ ወዳጅ፣የሌላው ጠላት አድርጎ በመሳል፣ባልተቋረጠ ፕሮፖጋንዳ ትውልዱ ቂመኛ ና በቀለኛ እንዲሆን አድርገዋል። (የአኖሊን ሐውልትና የተስፋዬ ገ/አብን የቡርቃ ዝምታን ይጠቅሷል።)

ከዚህ እውነት አንፃር በአፍሪካ አህጉር የምትገኘውን፣ዓለም በጀግና ህዝቧ ኩሩነት አትንኩኝ ባይነት እና ጀግንነት ዓለም ሁሉ የሚያውቃትን፣ውድ ሀገራችንን፣ለመበዝበዝ እንዲያመቻቸው ልጆቿን በገንዘብ ና በጥቅም ደጋግመው ደልለዋል።(ይህንን እውነት ለማጠናከር ከማጨው ጦርነት እልቂት በፊት ለኢጣሊያ የገበሩትን እና በሽፍታ ወታደሮቻቸው ከጣሊያን ጋር ወግነው በደፈጣ የወገንን ጦር ሲወጉ የነበሩትን ደጃዝማች ኃይለሥላሴ ጉግሳን ይጠቅሷል።)

ይህ የራሥን ዜጋ የማሥኮብለል እና ለራሥ ዓላማና ጥቅም የማሰለፍ  ተግባርን፣የበለፀጉት አገራት መንግሥታት ለዘላቂ ጥቅማቸው ሲሉ ሁሌም የሚተገብሩት ነው።በዚሁ በረቀቀና በተጠና መንገድ ኃይለኛ ከሚሉት ጋራ በማበርና በግንባርም በመሠለፍ አፍሪካ በጠመንጃ አፈሙዝ ተገዢ ሆና እንድትኖር አድርገዋል።

አፍሪካዊው በባለጠመንጃ ሁሌም ተገዢ ሆኖ እንዲቀር በማድረግና ያ በእነርሱ ድጋፍ ባለጠመንጃ የሆነው መንግሥትም የእነርሱ ፈቃድ ፈፃሚ ሆኖ እንዲዋቀር በማድረግ፣ዛሬም በእጅ አዙር ቅኝ አገዛዝ ብዝበዛቸውን እንደቀጠሉ ይታወቃል።

ይህቺን በዓለም ሥልጣኔ ቀደምት ና የሰው ዘር መገኛ የሆነችን ውብ አገርም ( ለሰው የዕለት፣ዕለት ኑሮ አየሯ እና ምድሯ እጅግ ተስማሚ በመሆኑ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት የተለየ ፀጋ እንዳላት ይታወቃል)   እነዚህ ለብዝበዛ የቋመጡ የበለፀጉ አገራት ቱጃሮች፣በግልፅና በሥውር ለዘመናት እንዳትረጋጋ ያላሰለሰ ሴራ ሲፈፅሙባት ኖረዋል።ከጥቂት እበላ ባይ ህሊና ቢስ ባንዳዎችም ጋር በመመሳጠር ሲበዘብዟት ና ሲመዘብሯት እንደኖሩ ታሪክ ምሥክር ይሆንባቸዋል ።

ታሪክ እና አውነት እንደሚመሰክሩልን የሀገርን ሀብት ማሥበዝበር ና መመዝበር የተጀመረው በዘመነ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለሥላሤ ዘመነ መንግሥት ነበር።ብዝበዛውም ለንጉሡና በጣት ለሚቆጠሩ መሳፍንትና መኳንንት ብቻ የተፈቀደ ነበር።በተለይም ቀኃሥ እና ቤተሰባቸው፣ብር፣ወርቅና አልማዝ በአውሮፓ እና በአማሪካ የግል ባንኳች እንደሸሸጉ ይታወቃል።ይህ ተመክሮነው፣ዛሬም አድጎ የወያኔ መሣፍንቶች በአገሪቱ የደሃ ጓዳ ያለውን ሳይቀ ርአራግፈው በመዝረፍ በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር በውጪ አገር ባንኳች እንዲያሥቀምጡ የመጀመሪያውን ትምህርት የሰጣቸው።ማን ከማን ያንሳል??? (አዲስ ንጉሥ እንጂ ለውጥ አልመጣም ተብሎ የተዜመውም ይህንን እኩይ ድርጊት ጨምሮይመሥለኛል።) ።

የዛሬው የጦርነት እውነትም የሚነግረን ወያኔዎች፣ከዚህ በታሪክ ከሚያሶቅስ  እኩይ ተግባራቸው ከቶም ያለመፀፀታቸውን ነው። በሥመ ወያኔ በጠመንጃ ኃይል የነገሡት ጥቂት የወቅቱ መሣፍንቶች በህዝባዊ ተቃውሞ የመጣው ለውጥ የሻይ ሥኒ ማዕበል እንዳልሆነ ባለመረዳታቸው እና ባላቸው ነፍሠ ገዳይ ኃይል በመተማመናቸው ለዛሬው ውድቀትና አሣፋሪ ታሪክ ሊበቁ ችለዋል።

ኢትዮጵያዊያኖቹ ትግራዊያን ለኢትዮጵያ ዳር ድንበር መከበር ለ3000 ዘመናት እንዳልደሙና፣እንዳልቆሰሉ፤እንዳልሞቱና አጥንታቸው እንዳልተከሠከሠ .መስዋትነታቸውን በመናቅ እና ከንቱ በማድረግ ፣ መሳፍንቶቹ ለብዝበዛ እንዲያመቻቸው፣ “አማራ ኦሮሞ የሚል ፣የመለያያ ና የማጋጫ ክልል ና ሌሎች የፈጠራ ትርክቶችን በመፍጠር ” ይህንን ትርክትም በራሳቸው ሰዎች ተዋናይነት፣በገሃዱ ዓለም የጥፋት ድራማ ሰርተው በማሳመን፣ኢትዮጵያ ሠላም እንዳይኖራት ብቻ ሳይሆን የተረጋጋ እና በሙሉ አቅሟ ልማት ላይ እንዳታተኩር አድርገዋል።

የመሠረቱትም መንግሥት የጥቂት የማፍያ አሥተሳሰብ ያላቸው ዘራፊዎች አገልጋይ እንዲሆን አድርገዋል።ሥትሰርቅ ከተያዝህ ሌባ ትባላለህ እንጂ እሥካልተያዝክ ድረሥ ሥራህን ቀጥል።ሌብነትም ሥራ ነው።በማለት፣የወያኔ ፋሺሥታዊ መሪዎች የሰርቆት ባህልን ፈጥረውልናል።

የወያኔ ፋሺሥታዊ አገዛዝ፣ከ1983 በፊት በትግራይ ህዝብ ልብ አና አእምሮ ከ1983 በኋላ ደግሞ ጥቂት በማይባሉ ኢትዮጵያዊያን አእምሮና ልብ ውሥጥ ሃሰተኛ ትርክት በመፍጠር አጥፊዬችን የሆነ የጎሣ፣የነገድና የቋንቋ ካንሰርን አራብቷል።ከአንድ ኢትዮጵያ ከተሰኘ ወርቃማ ግንድ ላይ ያለን ብዙ አልማዝ የሆንን ቅርንጫፍ መሆናችን እና ሰው መባላችን ቀርቶ ጎሷ ነገድ፣ብሔርና ብሔረሰቦች በመሆን ራሳችንን በግብዝነት እንድናጃጅልና የሥልጡኑ ዓለም መሳቂያና መሳለቂያ እንድንሆን ፈርዶብን ነበር።

ወያኔ በደርግ የተደመሰሰውን ጭቆና አራጋቢ የሆነትበት ና በሶሻሊዝም ርእዮት ሰው ሁሉ እኩል የሆነበትን ሥርዓት ፍፁም በመካድ፣የባላባታዊውን ወይም የገባሩን ሥርዓት በደልና ግፍ ከመቃብሩ በመቆስቆስ ለብዝበዛው እንዲያመቸው በማራገብና በማንደድ ጥቂት የማይባሉ ዜጎች፣ቋንቋ እንጂ ሰው እንዳልሆኑ እንዲያምኑ እና በዚህ በእጅጉ በተራቀቀ 21 ኛው ክ/ዘ እየኖሩ ልክ እንደ 18 ኛውና 19 ክ/ዘ እንዲያሥቡ አድርጓል።

በነገራችን ላይ፣ወያኔዎች ትላንት የተመሠረቱበትን ዓላማ ዛሬም ለጥቅማቸው ሲሉ አለቀቁም።ይኸው ዛሬም ለመሞት እየተንፈራገጡ  ” ወያኔ ወይም ሞት!” ይሉናል።ዛሬ ወያኔ የሚመራው በባንዳ መሆኑ ግን መታወቅ አለበት።

ኢትዮጵያዊውን ትግራዊ፣ከእናት አገሩ እገነጥለዋለሁ የሚል ሥያሜ የያዘው ይህ አጥፊ ከይሲ የባንዳ ጥርቅም የሆነ ጥቂት ቡድን፣ደርግን ከሥልጣን ለማሶገድ በምእራብያዊያን ድጋፍ በሻብያ አሠልጣኝነት በእጅ ጣታችን በሚቆጠሩ ሰዎች ት/ህ/ነ/ግ   (ትግራይ ህዝብ ነፃ አውጪ ግንባር ) ተብሎ መመሥረቱ ይታወቃል።(ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ )

ይህ ቡድን የጥቂት ሤረኞች ወይም ማፍያዎች ጥርቅም ነው።ይሁን እንጂ የወቅቱ የዓለም ፖለቲካ በፈጠረለት አመቺ ሁኔታ ለሥልጣን መብቃቱ ይታወቃል። በለሥ ቀንቶት ” ጨርቅ በሆነ መንገድ ” የኢትዮጵያ አንድነት ተምሳሌት በሆኑት በምኒልክ ቤተመንግሥት፣በደርግ ወንበር ላይ ደርግን ተክቶ ለ27 ዓመት ሥሙን ሳይቀይር የኢትዮጵያን ደም እየመጠጠ መቀመጡም አይዘነጋም።

የረጅም ጊዜ እቅዱም፣ኢትዮጵያን በእጅ አዙር ቅኝ ግዛት በመያዝ ብዝበዛውን ዘላቂ ማድረግ ነበር።ለዚህ እቅዱም ሥኬት በብዙ ደክሟል።ከጅምሩ የመሐል አገርን የኢንዲሥትሪ ንብረቶችን በመዝረፍ ምን ያህል ሥግብግብ እንደሆነ አሣይቶን ነበር።

በረዢም ጊዜ እቅዱ ወሥጥ፣ራሱን በኢኮኖሚ እና በወታደራዊ አቅም አደራጅቶ፣ሌላውን ዜጋ በቋንቋ አናቁሮ እርሱ ብቻ በሠላም የመኖር ህልምም ነበረው።አልተሣክቶም እንጂ።

ዛሬ ላይ የተሳካለት በቢሊዮን የሚቆጠር ዶላር፣ወርቅና አልማዝ ወደ አውሮፓና አሜሪካ አግዞ ኢትዮጵያን ማደህየት ብቻ ነው።የተሣካለት ኢትዮጵያ በኢንዱስትሪ እንድትለማ ከማድረግ ይልቅ ኪራይ ሰብሥበው የሚጠፉ የውጪ አገር ቱጃሮች እንዲበዙ ማድረግ ነበር።የተሳካለት ለብዝበዛ እንዲያመቸው ራሱን በጦር ኃይል ብቻ ሳይሆን በኢኮኖሚም አቅም ማሳደግ ነበር።የተሳካለት ቆሜለታለሁ፣እገነጥለዋለሁ የሚለው ህዝብ አናት ላይ ፊጥ ማለት ነው። የተሳካለት በትግራይ ገበሬ፣ማጅር ግንድ ላይ፣በጉልበቱ በመቆም ዜጋው የእርዳታ ሥንዴ እየተሰፈረለት እንዲኖር ማድረግ ነው።

ይህ በቁሙ የሚቃዥ፣በጠመንጃ የሚያምን ህሊና ቢስ የጥፋት ቡድን ደሃው የትግራይ ገበሬ ፈፅሞ አያሳዝነውም።ምክንያቱም ከላይ እንዳብራራሁት እርሱ መሳፍንትና እጅግ የተከበረ መኳንንትነውና!!! ይህ ግብዝና ከይሲ ቡድን እንደብዙዎቹ የአፍሪካ አገሮች ጠመንጃ ምን ጊዜም ገዢ ና አሸናፊ ሆኖ  ይቀጥላል ባይ ነው። ህዝብ በጠመንጃ ኃይል ተጨቋኝና እሺ ብሎ አዳሪ፣ፈሪና አዝማሪ ቆሞ ግፋ በለው ካላለው ለመብቱና ነፃነቱ የማይሟሟት እንደሆነ የሚያምን ግብዝም ነው።በሌሎች ጡንቻ ራሥ ግብዝ ተባባሪዎቹም የአውሬነት ባህሪ የሚተማመን ከመሆኑም በላይ ማንም ሰው በቢላዋ ቀልድ የለም ማለት እንደሚችል የሚገነዘብ አእምሮ የለውም።

እርግጥ ነው፣የአፍሪካ ታሪክ የሚነግረን ባለጠመንጃዎች በእውቀት ሳይሆን በጉልበት መንግሥት ሥለሚኮን ጥበብና እውቀት ባይኖራቸው የሚገርም አይሆንም።ባለጠመንጆች የህዝቡን ድምፅ የማያከብሩና ምንጊዜም ጠመንጃ የለው አሸናፊ ነው፣ብለው የሚያምኑ እና ጦር ሠራዊታቸውን ገዢ በሆነው ቡድናቸው አሥተሳሰብ ካጠመቁ ለህዝብ ወይም ለዜጋ ደንታም እንደማይኖራቸው ደጋግመው አሣይተዋልና ከአምባገነኖች መልካም ነገር አይጠበቅም ።

በለጠመንጃዎቹ አምባገነን መንግሥታት ለዜጎች ደንታ የላቸውም።በጦር መሣርያ ለሚደግፏቸውና ለጠባቂዎቻቸው እንዲሁም የመሣሪያ ድጋፍና ሥልጠና ለሚሰጡላቸው ባለፀጋ መንግሥታት ብቻ በመሆኑ፣እነዚህ ባለፀጋ አገሮች እንዳሻቸው፣የ ኢኮኖሚ፣ የባህል፣የፖለቲካ የበላይነትን በአፍሪካ አህጉር እንዲኖራቸው እንደሚፈቅዱላቸው ታሪክ ይመሠክራል።

ታሪክ እንደሚነግረንና እውነቱን ከእያንዳንዱ የአፍሪካ አገር የባህልና የቋንቋ መበረዝ ጋራ እያነፃፀርን ሥንመለከተው ይህ ደምዳሜዬ እውነት መሆኑንን መገንዘብ ይቻላል።

በዙዎቹ የአፍሪካ አገራት በልማት ተመንድገው ያልበለፀጉት፣የራሳቸውን ሀብት ከማደለብ እና የሚኖሩበትን አገር፣ከማበልፀግ የዘለለ ህልም በሌላቸው ህሊና ቢስ የውሥጥና የውጪ የብልፅግና ጠላቶቻቸው ጭምር ነው።ከዚህም እውነት ተነስተን በአፍሪካ ውሥጥ የሚካሄዱትን ግጭቶች፣ ጦርነቶች፣ሽበሮች በማባባሥ፣በአገር ውድመትና ከለማት ወደኋላ መቅረት ለመበልፀግና ለመክበር የሚፈልጉ የበለፀጉ ሀገራት ቱጃሮች እንዳሉ በቀላሉ ለመገንዘብ እንችላለን።

እነዚህ የአፍሪካ ህዝብ የድህነት ኖሮ እና የህይወቱ ሰቆቃ፣ከቶም የማይገዳቸው ህሊና ቢስ የምዕራብያውያን ቱጃሮች በአገራቸው መንግሥት ሠውርና ግልፅ ድጋፍ እያገኙ፣ዛሬም አፍሪካን ከማበልፀግ ይልቅ አፍሪካ ለብዝበዛ እንድትመች እያደረጓት ነው።ድብቅና ግልፅ በሆነ የብዝበዛ መንገዳቸው ዛሬም ገፍተውበታል።

ትላንት የአፍሪካውያንን እጅ በጦር መሣሪያቸው ኃይል ተጠምዝዞ ለዘመናት በቅኝ እየተገዙ፣ሲበዘበዙ መኖራቸውን ይታወቃል። ዛሬ ደግሞ አፍሪካ ለአውሮፓ ፣አሜሪካ እንዲሁም ለኢሲያ አገራት የኢኮኖሚ ና የቴክኖሎጂ ቅኝ ተገዣ ሆናለች።ይህ የዕወቀትና የጥበብ ተገዢነቷም አፍሪካ ሳትወድ በግድ ቋንቋቸውን ብቻ ሳይሆን ጎጂ ባህላቸውን ጭምር እንድትጋት እንድትጋት እንዳደረጋት ይታወቃል።ዛሬም ይኸው ቀፋፊ እውነት አላባራም።

ይህ ቀፋፊ እውነት፣አፍሪካዊያኑን ዛሬም ከድንቁርና እንዳይወጡ አድርጓል።እውቀቱ እና ብቃቱ ሥለሌላቸውም በቴክኖሎጂ ለተራቀቁት ምእራባዊያን ብዝበዛ ተጋልጠው፣ህይወትን በሰቆቃ ይገፋሉ።

ዛሬም፣አፍሪካ፣ቴክኖሎጂን ገዢ በመሆን፣ጥሬ ሀብቷን ለብዝበዛ አጋልጣ በድህነት ኗሪ ናት።በዚህ በ21ኛው የዲጂታል ቴክኖሎጂ በተራቀቀበት፣ዓለም በጠበበችበት ክፍለ ዘመን እነኳን በድንቁርና ተጀቡና እንድትኖር የሚፈልጉ፣ሥግብግቧች እዛ ና እዚህ አሉ።

አብዙኛዎቹ የአፍሪካ አገራት እሥከዛሬ ድረሥ ያልበለፀጉበት ምክንያት ይኸው ቀፋፊ የብዝበዛ እውነት ደንቃራ ሆኖባቸው ነው።

ይህ ቀፋፊ የብዝበዛ እውነት በገሃድ እንዳይታይ የሚያደርገው መሠሪ ፕሮፖጋንዳ ደግሞ የበለጠ የአፍሪካን ህዝብ እንዲደነዝዝ አድርጓታል።

ነበራዊው እውነት የአፍሪካ ህዝብ፣በእውቀትና በጥበብ የለመበልፀጉን እየመሠከረ፣በየጊዜው የሚነዙት መሠሪ ፕሮፖጋንዳቸው የበለጠ ከጥበብና ከእውቀት እንድንርቅ የሚያደርግ እንጂ ዘላቂ ሠላም ና ብልፅግና በአፍሪካ የሚያሥከትል እንዳልሆነ በተግባር የታየ ነው።

በአፍሪካ አህጉር በመሠሪ የውሸት ትርክቶችና ፕሮፖጋንዳዎች አያሌ ጦርነቶች፣የእርሥ በእርሥ ግጭቶች፣ጠልፎ መጣሎች ሌሎች አያሌ እኩይ ድርጊቶች በዜጎች መካከል እንደሚፈጠሩ ይታወቃል። ይህም የሚሆነው የነቃ፣የተማረ እና በጥበብ የተደራጀ በግሉ ለምን ?ማን? መቼ ? የት፣ ? ምንድን…?  የሚል ዜጋ በብዛት ሥለማይገኝ እና አብዛኛው ያለ ጥያቄ ሐሰተኛ ትርክቶችን በወገናዊነት መንፈሥ እንደወረደ ሥለሚቀበል ነው።

ዛሬ የሀገር መከላከያ ሠራዊቱ እየተዋጋ ያለውም፣የሐሰተኛ ትርክት ሰለባ ከሆነ፣ፈጣሪ በሰጠው አእምሮ ተጠቅሞ ራሱን በመጠየቅ ከሥህተት ለመዳን ባልቻለ የጥፋት ኃይል መሪ ጋር ነው።ባንዳ ና ከይሲ ከሆነ የአገርና የህዝብ ቁጥር አንድ ጠላት ጋር ነው።ይህ ከይሲ የጥፋት ኃይል ደግሞ በውሸት የተካኑ በሺ የሚቆጠሩ ፕሮፖጋንዲሥቶች ያሉት መሆኑ ይታወቃል።

እነዚህ ፕሮፖጋንዲሥቶች ከጦር መሣሪያ እኩል አገሪቱን ሲወጉ የኖሩ ናቸው።ጦርነቶች የሚካሄዱት በአጥፊ ወይም በገዳይ መሣሪያዎች ታግዘው ብቻ አይደለም።ጦርነት በተለያዩ መንገዶች በሚነዛ እውነተኛ እና ሐሰተኛ ወሬም አማካኝነት ይካሄዳል።በቀጥታና በግልፅ ተዋግተህ የምትሞትበት በጦር መሣሪያዎች የሚደረግ ጦርነት ከወሬ ጦርነት አይብሥም። ለዚህ ምነው፣ጦር ከፈታው ይልቅ ወሬ የፈታው በቁሙ እንደሞተ የሚቆጠረው።ለምን ቢሉ በጠላት ፕሮፖጋንዳ ወኔው ተሠልቧልና።

በትግራይ የተጀመረው ጦርነት፣በጥቂት አንጃዎች፣ማለትም የኢትዮጵያን ጦር በከዱ ጥቂት የአገር መከላከያ ሠራዊት አባላትና ጥጋብ ባሳበዳቸው፣ባንዳዎች ጥምረት የተጀመረ ቢሆንም የፕሮፖጋንዳ ጦርነቱ ቀድሞ ነበር።

ሌለው መታወቅ ያለበት ደግሞ፣ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት ወያኔ/ኢህአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ፣አማራነት፣ትግሬነት፣ኦሮሞነት ወዘተ።በትውልዱ ውሥጥ በብርቱ እንዲቀነቀን ማድረጉ የአሸናፊነት ሥነ ልቡና እንዲኖረው የራሱን አሥተዋፆ ማድረጉ አይካድም።

በዚህ በባንዳ አድራጎቱም ያንን አሳፋሪ፣ምንጊዜም በቆሻሻነቱ የማይረሳ፣የታሪክ አተላዎችን ተግባር ፈፅሟል።ትላንት በማጨው ፣በአዲግራት፣ በአምባላጌ ጦርነት ቅኝ ገዢዎች ኢትዮጵያኖችን በመከፋፈል በጥቅም በመግዛት እርሥ በእርሥ እንዳይተማመን በማድረግ ና ከጀርባ በመውጋትና በመዝረፍ የፈፀሙትን አሥነዋሪ ተግባር ከእነሱ በባሰ ሁኔታ የተገበረውም ከዚህ የተሳሳተ ድምዳሜ ተነሥቶ ነው። (በተጫነ ጆብሬ መኮንን የተተረጓመውን የአዶልፍ ፓርላሳክ “የአበሻ ጀብዱ “ የተሰኘውን ፣በእውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ መፅሐፍ ያነቧል።)

ይህ ጦርነት በጥቂት ከሃዲ ወታደሮች ድጋፍ በተመሠረተ ጁንታ አማካኝነት የተጀመረ የአገር ክህደት ጦርነት ነው። ቀደም ሲል ጥጋብ ያሳበደው፣አንጃ መሥርቶ ኢትዮጵያን ወግቷል። ቀደም ሲልም አያሌ፣አንድነታችንን የሚሸረሽሩ ፀረ_ኢትዮጵያ ቅሥቀሳዎችን በማድረግ እና የብሔር በሔረሰቦች መብት በሚል ሽፋን ዜጎችን በቋንቋ በመከፋፈል፣ቅንጥብጣቢ ሥልጣንን በመሥጠት የብዝበዛ መረቡን ያለሃይ ባይ በመዘርጋት የራሱን ንግሥና በትግራይ ህዝብ ሥም አሥፍኖ እንደነበረም አይረሳም።

ዛሬ ሳይሆን ቀደም ብሎ በፀረ ኢትዮጵያ ኃይሎች ተደግፈው የሚንቀሳቀሱ መሠሪዎች ነበሩ። ከእነሱም ጋር፣ሳያውቁም ሆነ አውቀው በቋንቋ ተቦድነው ከወንድማማችነት እና ከእህትማችነት ይልቅ ባድነትን፣ጠላትነትን፣መጠፋፋትን፣ቅሚያና ዘርፍያን፤ሥቃይና ግድያን የሚያስፋፉም ነበሩ።

እኛም በተቀደደልን የመጠላላት፣የመለያየት የመገነጣጠል መሥመር ውሥጥ ዛሬም እየተጓዝን ነው።ይሄ የእኔ ድንበር፣የእኔ አጠር፣የእኔ ጎሣ በማለትም -ከኢትዮጵያዊነት ይልቅ፣ት“ግሬነት፣ኦሮሞነት፣አማራነትን ወዘተ። “ እያቀነቀንን ለየብቻ በመኮፈሥ ላይ ነበርን።

ከዚህም በባሰ መልኩ፣ ” እትዮጵያ ትውደም ! ” እያልን፣“አማራ፣ትግሬ ኦሮሞ …ይቅደም! በማለት ዘረኝነትን ማሥፋፋታችን ይታወቃል።እንዲህ ዓይነቱ አሥተሳሱብ እና የአደባባይ ዝማሬ በአሜሪካና በቻይናም ቢሆን አይፈቀድም፡፤ ግለሰብም ሆነ ቡድን፣ገጀራና ዱላ ይዞ ሊያቀነቅነው ይቅርና ባዶ እጁን እንዲህ አይነት ከንቱ አገር አፍራሽ ንግግርና ጩኸት በአደባባይ ቢያሰማ በሰከንድ ወደ ዘብጥያ አልያም ወደ ህክምና ተቋም ይወሰድ ነበር።

በእነዚህ አገሮች ውሥጥ በዜግነትህ ኮርተህ መብትህ ተከብሮ ደህንነትህ ተጠብቆ እየኖርክ ሁሌም የምትለው ፣ “ቻይና ትቅደም! አሜሪካ ትቅደም !“ ነው እንጂ ፣ዜጋ ሆነህ ቻይና ትውደም ! አሜሪካ ትውደም ! ከቶም አትልም።

ይህ አገርን የመውደድ ትልቅ ተግባር ነው።በኢትዮጵያም ይህን መሠሉ የአገር ፍቅር ሥሜት ከወያኔ ፍፃሜ በኋላ እንደሚገነባ እና የቀድሞ የአገር ፍቅር ሥሜታችን እንደሚመለሥ ተሥፋ አደርጋለሁ።ይህ በንግድ ድርጅቶች እና በባንኮች ጭምር የሚታየው አጥር የማጠር የወያኔ አሥተሳሰብ ያከትማል።ወያኔ ትግሬ ባንክ ብሎ አልከፈተም።ነገር ግን ውህድ የሆነው የኦሮሞ ጎሣ እንዲከፍት አድርጓል። አማራም ዛሬ የአማራ ባንክ እከፍታለሁ እያለነው።ለመሆኑ የአማረ እና የኦሮሞ ገንዘብ የሚባል አለ እንዴ???

የእኛ አገርን የጎሣ ፖለቲካ ፍፁም ቀያሬ የሆነ ሁኔታ ዛሬ እንዳጋጠመ ስንረዳ ይህ ሀገርን አፍራሽ መንገድ ከድሉ በኋላ እንደሚስተካከል ተስፋ እናደርጋለን።የአገር አጥፊውን የወያኔ ፍፁም ዘረኛ እና ከፋፋይ የሆነ ፀረ ሰው አሥተሳሰብ የምንገላገልበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።

በዚች የእግዜር አገር ዘረኝነት እሥከወዲያኛው ሲቀበር ማየታችን አይቀርም።የዚች አገር ጎሳዎችም እጅ ለእጅ ተያይዘው በእኩልነት ወደብልፅግና በመጎዝ ለቀጣይ ትውልዳቸው መመኪያና መኩርያ እንደሚሆኑ አልጠራጠርም።ይህ እውነት በንዳዎችን፣ ዘረኞችን፣ፋሺስቶችን የማውደም ተልዕኮ በድል ሲጠናቀቅ እውን ይሆናል የሚል ተስፋ አለኝ። የዘርና የቋንቋ ፖለቲካም ያከትማል።ኦሮማይ !

1 Comment

 1. Yes, although all what you are saying is not immune from controversies that emanate from different perspectives of different people, most of what you are trying to describe and explain is true.
  Yes, the very inner circle of TPLF is and should be at the very forefront of being responsible and accountable for the very an imaginable general (political, economic, social, moral, ethical, cultural, spiritual/religious belief) crisis we have to deal with for more about three decades.
  Yes, it is unbelievably painful to see going back to the very tragically disgraceful political arena of killing each other (brothers/sisters against brothers/sisters) after going through the same tragic story for the last three decades.

  However. it is politically stupid for us to continue just decrying this tragic political animalism of our own making and crying because of the very unbearable pain it has caused and keep causing to us without making any meaningful difference as far as dealing with the politics of deeds , not words is concerned . Let’s slow down and take deep breath and think big and deep on the very question of why and how we as individual citizens, groups, and above all as people terribly and repeatedly failed to come together and defeat the very deadly or bloody politics of ethnocentrism . Does the politics of just decrying and blaming the very much known political madness of the mastermind of all the tragic consequences we keep facing make a real sense of finding the right solution? It absolutely doesn’t!
  Do you really believe that politicians of Oromization -led Prosperity of the same if not the worst banana (EPRDF) whose hands are directly or indirectly stained with the very blood of innocent citizens can be heroes of fundamental democratic change? I do not think you will be stupid enough to believe this very crystal clear reality of political crime we are dealing with.
  Your conclusion “things will change for the better after the end of the war “is very clumsy and delusional as it tries to simplify the very tragically messed up and complicated political reality of pour country. I wish it could be as simple as you express your very wishful thinking without calling for the continuation of the struggle for the realization of a fundamental democratic change that could and should be willing and able to defeat this senseless war and then defeat the very hypocritical, cynical, dishonest, conspiratorial, and of course cancerous politics of so called Prosperity which is the very tricky renaming of EPRDF.
  I strongly argue that yes, the very-evil minded inner circle of TPLF must be defeated once and for all. But I also strongly believe and argue that this victory should immediately follow by the continuation of the struggle to defeat those politicians of Prosperity who would definitely lead us to not only the lingering of unrest and instability but also to the very danger of falling apart into small ‘countries’ that would totally belong to those evil-minded and evil-driven politicians or elites of ethnocentrism.

  With due respect buddy!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.