በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት - ክፍል 8 | ዘ-ሐበሻ Latest Ethiopian News and Point of View 24/7

በጀርመን የገባውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን በተመለከተ ያለው ቴከኒካዊና ተቋማዊ ልምድና አስተያየት – ክፍል 8

1 min read
1

ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

ለተከበራቹህ ወገኖች

የኮሮና ልምድ ከጀርመን – 2ኛው ዙር  24.10.2020

ይዘት-  [አውሮፓ | አጠቃላይ ጀርመን | ምስራቅ ጀርመን | የበርሊን ሁኔታ | የኮሮና የትራፊክ መብራት | የጀርመን ፍርድ ቤቶች | የኮሮና መከላከል እርምጃ እና ስነምግባር |  ኢኮኖሚያዊ እይታ | ትምህርት ቤቶች | ፊልም ቀረፃ | መደምደሚያ] ከአለፈው በመቀጠል ለኢትዮጵያ ቴክኒካዊ ይዘቱ እና ለአጠቃላይ ግንዛቤ በአጣቃሽነት እንዲረዳ በማሰብ ከተጓዳኝ ነጥቦች ጋር ስለ ወረርሽኙ 2ኛ ዙር የያዘውን ክፍል ስምንትን አቀርባለሁ።

በጀርመን በይበልጥ በአውሮፓ የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ እያሻቀበ ከመስመሪያዊ እድገት ወደ ብዜታዊ እድገት በመቀየር ሁለተኛውን ዙር ጀምሯል።  ኢትዮጵያም የሚደርጉት ጥረቶች ፍሬ እያሳዩ ቁጥሩም በአንፃሩ እየቀነሰ ነው። 7ኛውን ክፍል ስፅፍ ኢትዮጵያ በቀን የሚያዘው ሰው ቁጥር ከጀርመን የበለጠበት ሁኔታዎች እንዳሉ አሳይቼ ነበር። አሁን ደግሞ ወደ ቀድሞው ሁኔታ ተመልሶ እንኳን መላውን ጀርመን ቀርቶ ለምሳሌ በብዛት መራቢያ hot spot የሆነው በርሊን ብቻ በአንድ ቀን ውስጥ በመላ ኢትዮጵያ ከሚመዘገበው እየበለጠ ይገኛል።

 1. አውሮፓ

ሁለተኛው ሞገድ አውሮፓን እያጥለቀለቀ ነው። ቼክ ሪፐብሊክ፣ ቤልጅየም፣ ኔዘርላንድ፣ ፈረንሳይ በአንፃሩ በየ100 ሺ ተመርማሪዎች ከፍተኛ የሆነ ቁጥር የያዙ ናቸው። ለምሳሌ ባለፈው ቼክ ሪፐብሊክ ከ100 ሺ ሰዎች ከ650 ሰው በላይ ለሰባት ቀን በተከታታይ በማስመዝገብ ቀዳሚ ሲሆን፣ ጀርመን ይህ ነጥብ 61.2 ነበር።

ስዊዘርላንድ፣ ቤልጅየም እና ፈረንሣይ የሰዓት እላፊዎች ሲጥሉ፣ በአየርላንድ እና በዌልስ በሙሉ ሎክዳውን ውስጥ ናቸው፣ በቼክ ሪብሊክ ያለው ሁኔታም ከቁጥጥር ውጭ እየሆነ ነው። ለኮሮና ህመምተኞች ከተያዙት የሆስፒታል አልጋዎች 80 ከመቶ የሚሆኑትም ተይዘዋል። ፖላንድም በ24.10.2020 መግለጫ ፕሬዚዳንቱን ጨምሮ በ24 ሰዓት ውስጥ 13,600 ሰዎች በወረርሽኙ ተይዘዋል። መንግስታት ገደቦችን ከማውጣት እና የተጠናከሩ እርምጃዎችም መልሰው ከመውሰድ ውጭ ሌላ መውጫ መንገድ አላገኙም።

በኔዘርላንድ ከጥቅምት 13 ጀምሮ በስራ ላይ የዋለውን የኮሮና መከላከያ እርምጃ በጥብቅ ተጠናክሮ “ከፊል ሎክዳውን” ተተግብሯል፡፡ መጠጥ ቤቶች ፣ ምግብ ቤቶች ለአራት ሳምንታት መዘጋት እንዲኖርባቸው ሃሳብ ቀርቧል፣ ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ የአልኮሆል ሽያጭ ተከልክሏል። ነዋሪዎች የሚፈቀድላቸው ቢበዛ ሶስት እንግዶችን በቤታቸው ውስጥ ማስተናገድ ብቻ ነው። ስፔንም በእጥፍ እየተመታ ይገኝል፣ ሰዓት እላፊም ታውጇል። ይህም የቁጥሩ መጨመር ብቻ ሳይሆን ለማገገም እየዳኸ የነበረውን የስፔን የቱሪዝም ሴክተር እየተጎዳ ይገኛል። የስፔን ኢኮኖሚ የማገገም እድሉም ወደ 2023 ተንሽራቷል። በአንፃሩ የጀርመን ኤኮኖሚ እ.ኤ.አ. እስከ 2021 ለማገገም ተስፋ ይታይበታል።

 1. አጠቃላይ ጀርመን

የፌዴራል እና ስቴት „የክልል“ መንግስታት ጥብቅ በሆኑ የኮሮና እርምጃዎች ላይ ተስማምተዋል።፡ አዲስ ሎክዳውን ከመተግበር ይልቅ የመከላከል እና የመጠንቀቅ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥተዋል፣ በተለይም ኢኮኖሚውን እንዳይጎዳ በሚያስችል መልክ። የፌዴራል ስቴት መንግስታትም የራሳቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች ነድፈው ይንቀሳቀሳሉ። ለምሳሌ በባቫሪያ ግዛት በሚገኝ አንድ ወረዳ የመወስኛ ነጥቡን በከፍተኛ ሁኔታ በመሸጋገሩ በወረዳው ውስጥ የሚገኙ ምግብ ቤቶች፣ ትምህርት ቤቶች፣ ሆቴሎች በሙሉ ተዘግተዋል፣ ዝግጅቶችም የተከለከሉ ናቸው።

ጊዜው ቀዝቃዛው ክረምት የሚገባበት፣ ጉንፋን እና ኢንፍሉዌንዛ ስለሚጨምርም ይህም በኮሮና ከተያዙ እጥፍ የሆነ ጉዳት ሊፈጥር ስለሚችል የኢንፍሉዌንዛ ክትባት እየተሰጠ ይገኛል። በኮሮና ወረርሽኝ ወቅት ጉንፋን ለአረጋውያን፣ ለከባድ ህመምተኞች ፣ ለነፍሰ ጡር ሴቶች እና ለህክምና ባለሙያዎች እና ነርሶች ተጨማሪ አደጋ ነው። አንዳንድ መስሪያ ቤቶች ለሰራተኞቻቸው ይህንን ክትባት እያቀረቡ ይገኛል።

የጀርመን ጤና ተቋም የሮበርት ኮህ ኢንስቲትዩት (RKI) ኃላፊ ከቀናት በፊት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ጀርመን የመጀመሪያውን የወረርሽኝ ማዕበል ከሌሎች ሀገሮች በተሻለ መልኩ በሚገባ የተቋቋመችው ውጤታማ እርምጃዎችን ቀደም ብለው እና በፍጥነት በመተግበራቸው ነው ሲሉ ገልፀዋል። ለሁለተኛውም ማዕበል ተመሳሳይ እርምጃ ይጠበቃል። የመጀመሪያውን ዙር ወረርሽኝ ማዕበል ለመቋቋም ከፍተኛ የህዝብ ድጋፍ አግኝቶ የነበረው የጀርመን መንግስትም እንደመጀመሪያው የሚያስገርም ድጋፍ ባይኖረውም አሁንም አብላጭያዊ ድጋፍ አለው። በቅርቡ በተደርገ የአስተያየት መመዘኛ 87% የሚሆነው ህዝብ ጠንካራ የሆነ የአፍ እና አፍንጫ መከላከያ እርምጃን ይደግፋል። ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ሰኞ እለት ባደርጉት ንግግር አፅንዖት በመስጠት በኮሮና ቫይረስ ላይ በጣም ውጤታማው መድሃኒት ስርጭቱን በማዘግየት ጊዜ መገዛ እንዳለበት እና እንደከዚህ ቀደሙ ሙሉ በሙሉ መዝጋት እንደ መጨረሻው አማራጭ ብቻ እንደሚወሰድ ነው ያስገነዘቡት።

ለመቆጣጠርም ለሰባት ቀናት ያህል በተከታታይ በ100,000 ነዋሪዎች ከ50 በላይ አዲስ የኮሮና ኢንፌክሽኖች መገኘት ወሳኝ ነጥብ ነው። ይህንንም ወሳኝ ነጥብ ጀርመን ካለፈው ቆየ፡፡ የሟቹ ድርሻ ከአንድ በመቶ በታች ቢሆንም የማስያዝ አቅም አንድ ለአንድ ነጥብ ሁለት(1:1.2) አድጓል። በ24.10.2020 የሮበርት ኮህ ኢንስቲትዩት እንደዘገበው በ24 ሰዓታት ውስጥ ብቻ 14,714 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን  በመመዝገብ ሪኮርዱን ሰብሯል። ይህም በተመሳሳይ የናሙና ምርመራ መጠን ከአንድ ሳምንት በፊት ከነበረው ከእጥፍ በላይ ነው። በ21.10.2020 ከተያዙት 11,287 ሰዎች መካከልም በዋናነት የሚጠቀሱት የ40 ዓመቱ የጀርመን የጤና ሚኒስትር ናቸው። እዚህ ላይ ምልክታዊ ትርጉሙ ከፍተኛ በመሆኑ ግራ መጋባትን ቢፈጥርም የጀርመን መንግስትም ሆነ ህዝቡ አልተረበሸም፤ ከሳቸው ጋር የነበሩትም የካቢኔ አባላት ወደ ኳራንቲን አልገቡም፣ ከእርሳቸው በስተቀር። ጀርመኖች የዕለት ተዕልት በሆኑ ሊያስከፉ፣ ሊያስረብሹ ወይም ሊያስደነግጡ የሚችሉ ሁኔታዎች ላይ ስሜት የመቆጣጠር ባህል አላቸው።

 1. ምስራቁ የጀርመን ግዛት

የቀድሞ ምስራቅ ጀርመን ተብሎ በሚጠራው ግዛት ወረርሽኙ አልተስፋፋበትም። ከ25-50 / በ100ሺ በታች ነው። ምክንያት ተብለው ከቀረቡት አንደኛው የውጭ ሀገር ትውልድ ያላቸው ወይም የውጭ ሀገር ሰዎች ቁጥር ዝቅተኛ በመሆኑ እነዚህም ተሰባስበው በአንድ ቤት/ አካባቢ የሚኖሩ፣ ትላልቅ ግብዣዎችን፣ ሰርጎችን ወዘተ የሚያደርጉ ወይም ከጀርመን ውጭ በብዛት የሚመላልሱ፣ ተሳልጠው የማይኖሩትም እንደባዮሎጂካዊ ጀርመኖች መመሪያዎችን በአፅንዖት ላይከተሉ የሚችሉት ቁጥር አነስተኛ በመሆኑ ነው የሚሉ አስተያየቶች ሲኖሩ፤ በሌላ በኩል ደግሞ የምስራቁ ግዛት ስነ ሕዝብ ዘርዘር ያለ፣ የተጨናንቀ የህዝብ ስብስብ የማይታይበት፣ አብዛኛው በእድሜ የገፉ ሰዎች እና እነዚህም ከቦታ ቦታ ተንቀሳቃሽ  እንዳልሆኑ፣ ከቀዬቸውም እንደማይርቁ፣ ወረርሽኙን በብዛት እያስፋፉ ያሉት ወጣቶች ቁጥርም አነስተኛ መሆኑ እና የህክምና ባለሙያዎች የሚሰጧቸውን ሳያወላዱ የሚቀበሉ ስለሆነ ነው የሚል አስተያየት  አለ።

 1. የበርሊን ሁኔታ

በርሊን በመጀመሪያ ከፍተኛው መራቢያ ቦታ (hot spot) በነበረበት ወቅት ከበርሊን ወደ ተለያዩ የፌዴራሉ ግዛቶች መሄድ ላይ በተለይም ወደ ሰሜን ሜከለንቡርግ ፎርፖመን ማልፈ ችግር አጋጥሞን ነበር ወይም እስክናካቴው ዝግ ነበር።

ወረርሽኙ በከፍተኛ ሁኔታ  የተከማቸበት የምንኖርበት የበርሊን ከተማ ሴኔቱ/ምክርቤቱ ማክሰኞ አዲስ እርምጃ የወሰነ ሲሆን 1.5 ሜትር ርቀት ለመተገበር በሚያስቸግርባችው አካባቢዎች በሙሉ ማስክ እንዲደርግ አስቀምጧል። ይህም  ሳምንታዊ የገበያ ሥፍራዎች፣ በተለይም መጨናንቅ እና ህዝብ በሚበዛባቸው የግብይት ጎዳናዎች፣ የገበያ ማዕከሎች እና ወረፋዎች ላይ ይፀናል።  ምግብ ቤቶች እስከ ምሽቱ 5 ሰዓት ክፍት ሲሆኑ በዚህ የምሽት ጊዜም ውስጥ ቢበዛ ከአምስት ሰዎች ጋር ብቻ ወይም የሁለት ቤተሰቦች አባላት በአንድ ቦታ ላይ እንዲገኙ ይፈቅዳል።

የኢንፌክሽን መከላከያ ደንቦችን ለማስፈፀም የወጣው መመሪያ እንደሚያዘውም ለክትትል እንዲያገለገል በተለያዩ ቦታዎች የሚከተሉትን መረጃዎች የያዘ ፎርም መሙላት ያስፈልጋል ፡-

ሙሉ ስም ፣ ስልክ ቁጥር፣ የመኖሪያ ቦታ ሙሉ አድራሻ፣ የኢሜል አድራሻ፣ ስልክ፣ የተገባበት ሰዓት፥ ምግብ ቤት ከሆነ ደግሞ የመቀመጫ ወይም የጠረጴዛ ቁጥር መመዝገብ ያስፈለጋል። የተሳሳተ አድራሻ የሰጠም ቅጣት ይጠብቀዋል።

የአፍ እና የአፍንጫ መከላከያ ማድረግ ቀድሞውኑ በሱቆች፣ በአውቶቡሶች እና ባቡሮች፣ በቢሮዎች ውስጥ፣ በትምህርት ቤቶች (ከክፍል ውጭ ብቻ እና በመጫወቻ ስፍራ አያጠቃልልም) እንዲሁም በምግብ ቤቶች (ሲገቡ፣ ሲወጡ፣ ከጠረጴዛ ተነስትው ሲንቀሳቀሱ) ያስፈልጋል።

በበርሊን የኮሮና ኢንፌክሽን መጠን በቅርቡ ያለማቋረጥ አድጎ በሰባት ቀናት ውስጥ በተከታታይ ከ 100,000 ነዋሪዎች መካከል አዳዲስ ኢንፌክሽኖች ቁጥር በአማካይ ወደ 89.2 አድጓል (ከሰኞ ጀምሮ)።፡ ስለሆነም ዋና ከተማው የወሳኝ ነጥቡን 50/በ100ሺ  ካለፍ ቆየ። ወረርሽኙ ኖይኮልን (Neukölln) በመባል የሚታወቀውን ክፍለ ከተማ በከፍተኛ ሁኔታ አጥቅቷል። የወሳኝ ነጥቡም በከፍተኛ ሁኔታ በመተላለፍ 190/100ሺ ደርሶ ነበር። ይህ ስፍራ የቦታ ጥበት ያለው እና ከፍተኝ ብዛሄነት የሚታይበት፣ ከ160 በላይ የተለያዩ አገራት ዜግነት ያላቸው፣ በተለይም የቱርክ ትውልድ ያላቸው የሚበዙበት እና ከ300ሺ በላይ ሰዎች ተቻችለው የሚኖሩበት የበርሊን ክፍለ ከተማ ነው። እ.ኤ.አ. መስከረም 23 ቀን 2008 በፌዴራል መንግሥት „የብዝሃነት ቦታ“ የሚል ማዕረግ የወሰደ ነው።

በርሊን ውስጥ ከ24.10.2020 ጀምሮ ወደ10 በሚቆጠሩ ሰው በሚበዛባቸው ጎዳናዎች እና የጋራ የመገበያያ ሥፍራዎች ማስክ አድርጎ መንቀሳቀስ  ግዴታ ሆኗል። ይህ ደንብ መከበሩን የሚቆጣጠሩ ወደ አንድ ሺ ፖሊሶች ተመድበዋል። መመሪያውን በሚተላልፉት ላይም አዳዲስ የገንዘብ ቅጣት ተመን እንደሚወጡ ይጠበቃል። ሁኔታዎች ካልተሻሻሉ ሎክዳውን በጀርመን ዋና ከተማ በበርሊን ሊጣል እንደሚችል ከንቲባው ገልፀዋል።

 1. የኮሮና የትራፊክ መብራት ከጀርመን

የትራፊክ መብራት ስርዓት የተፈጠረው በወረርሽኙ ስርጭታዊ ብዜት ላይ ተመሠርቶ ነው፡፡ ለምሳሌ አረንጓዴ ማለት በ100,000 ነዋሪዎች የቫይረሱ የመከሰት መጠን ከ 35 በታች ነው ማለት ነው። ለ100,000 ነዋሪዎች ከ 35 በላይ በሆነ የመከሰት መጠን የኮሮና የትራፊክ መብራት ወደ ቢጫ ይቀየራል። ቀይ ማለት ለ 100,000 ነዋሪዎች ከ 50 በላይ በመሆን 50ን የወሳኝ ነጥቡን ተላልፎ የመከሰቱ መጠን ተፈጻሚ ሲሆን ነው። እዚህ ላይ ይህ የመከስት መጠን ነጥብ ለሰባት ቀናት ሳይቀየር ከቀጠለ እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል። የመከሰት መጠኑ በ100,000 ነዋሪዎች ከ 100 በላይ ከሆነ የትራፊክ መብራት ደረጃው “ጥቁር ቀይ” ይሆንና አስቸኳይ እና የጠበቀ እርምጃ ለመውሰድ ያስገድዳል፡፡

 1. የጀርመን ፍርድቤቶች ኃይል

በጀርመን የኮሮና ወረርሽኙን መስፋፋት ለመቀነስና ለመገደብ የፌደራሉ ግዛቶች የተለያየ እርምጃ እየወሰዱ ይገኛሉ። ቢሆንም እርምጃዎቹን በመቃወም በግል፣ በጋራ ወይም በድርጅት ስም ለጀርመን ፍርድ ቤቶች ክስ በማቅረብ አንዳንድ የተወሰኑት እርምጃዎች እንዲታገዱ ተወስኗል። ከሰውም ያልተፈረደላቸውም አሉ። ለምሳሌም በበርሊን ሬስቶራንቶችን አስቀድሞ ምሽት 21 ሰዓት ላይ (9 p.m.) የመዝጋት ውሳኔን ፍርድ ቤት ሲቀለብስ፣ በሌላ ግዛት ደግም ከሌላ ቦታ የሚመጡ ጎብኝዎችን ሆቴል ለማደር ያለ ኮሮና ምርመራ አይቻልም የሚለውን መመሪያ አስነስተዋል። የብይን ምክንያቱም ሆቴሎች በሽታውን በቀዳሚነት ያላስፋፉ መሆናቸን በመጥቀስ ነው።

 1. ኮሮና መከላከል እርምጃ እና ስነምግባር

የጀርመን የስነምግባር ምክር ቤት (በስራው ኢትዮጵያ ከሚታወቀው የስነምግባር ኮሚሽን ጋር አይገናኝም)፣ የኮሮና በሽታ መከላከል አቅም (immune system) ማረጋገጫ መስጠትን አልተቀበልም።

„ኢሙን“ የመሆን ማረጋገጫ ከተሰጠ “በሽታ የመከላከል ላይ የተመሠረተ ሁለት ክፍል ማህበረሰብ” ሊፈጠር እንደሚችል ስጋቶች በብዛት ሲታዩ ነበር።  የሥነ ምግባር ምክር ቤቱ “በዚህ ጊዜ”  አሁን ባለው ሳይንሳዊ ሁኔታ  ጊዜው ሲደርስ የክትባት ሰርተፍኬት እንጂ በሽታው መከላከያን/ ከበሽታው በመዳን በሽታውን ለመከላከል የሚያስችል አቅም መፍጠርን የሚገልጽ ሰርተፍኬትን አልተቀበለውም። ለስነምግባር አማካሪዎች አማራጭም ሆኖ አልታየም። የስነምግባር ምክር ቤቱ ማስክ ማድረግን እንደሚቀበለው መወስኑ አይዘነጋም። ክትባት ቢመጣም መጀመሪያ ማን ይከተብ የሚለውን ከሚወስኑት አንዱ ይህ የስነምግባር ምክርቤት ነው።

ስለሞራል፣ ስነ-ምግባርና መልካም ባህርይ ማስተማርና ይህንንም እንደየዘመኑ ማስተካከል ተገቢ ነው። የቀድሞው የጀርመን  ቻንሰለር ሽሮይደር የመጀመሪያውን የጀርመን የስነምግባር ምክር ቤትን ያቋቋሙ ናቸው። ከ40 ዓመት በፊት የባይሎጂካል ስነ-ምግባር (ክሎን ማድረግ፣ ኦርጋን መቀያየር) ብዙ ያነጋገረ ነበር። አሁን ደግሞ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ  ኢቲክስ (ስነ-ምግባር) አነጋገሪ ነው። መቼ ነው አንድ መኪና እራሱን ችሎ የሚሄደው? አደጋ ቢያደርስ መኪናው ነው፣ አምራች ኩባንያው ነው፣ ወይንስ ባለቤቱ ነው ሀላፊነት የሚወስደው?… ወዘተ. ሲነጋግሩ ኮሮናንም አንዱ የምክር ቤቱ የስራ ወሰን ሆኗል። ኢትዮጵያ እዚህ ላይ ገና ባትደርስም በባህላዊ ስነ-ምግባር ግን የረዥም ጊዜ ታሪክ ባህል አለን። ይህንን ማደስ ተገቢ ነው።  ኢትዮጵያ የስነ-ምግባር  አማካሪዎች ካውንስል  ያስፈልጋታል ብዬ እገምታልሁ።

 1. ኢኮኖሚዊ እይታ

የቻይና ኢኮኖሚ ማደግ የጀርመን ኤክስፖርት ኢንዱስትሪን ከቀውሱ አድኗል። በወረርሽኙ ወቅት የእስያ ታላቅ ኃይል ቻይና ለጀርመን ኤክስፖርት ኢንዱስትሪ ሁለተኛው ትልቁ የገበያ ቦታ ነው። ከጥር እስከ ነሐሴ ባለው ጊዜ ውስጥ ወደ ቻይና የተላከው የጀርመን የውጭ ንግድ አኃዛዊ መረጃ ወደ 60,3 ቢሊዮን ዩሮ የሚያወጣ ምርት እንደነበር ያሳያል። ቀውስ ቢኖርም ኢንዱስትሪው እስከ 2020 መጨረሻ ድረስ በቻይና  ወደ 20 ሚሊዮን የሚጠጉ የግል መኪናዎችን አንደሚሸጥ ተስፋ አድርጓል። ከአሜሪካ (በ16 ሚሊዮን አካባቢ) ወይም በምዕራብ እና መካከለኛው አውሮፓ (12 ሚሊዮን) ነው። ይህም የጀርመንን የመኪና ኩባንያዎች ያዳነ ክስተት ነው። በምዕራቡ ዓለም በኢንዱስትሪ የበለፀጉ አገራት ሎክዳውን ላይ በነበሩበት ወቅት በ2020 ሁለተኛ ሩብ ዓመት ውስጥ ቮልክስዋግን ብቻ 53 በመቶውን መኪኖቹን በዓለም ዙሪያ ካሉት ሃገራት ለቻይና  ሽጧል።

ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ወረርሽኙ በሀገር አቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ ቢጨምረም የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪ አልታየም። አግበስብሶ መግዛት (panic buying) “በሁለተኛው ማዕበል” ላይ በብዛት ገና አልታየም። ሆኖም አንዳንድ ቦታዎች ላይ የሸማቾች መረበሽ ይታያል።

የማስክ፣ የሳኒታይዘር ዋጋ ቢቀንስም ሱቆች ወይም መስሪያ ቤቶች የሚጠቀሙባቸው ለትፍታ እና ምራቅ መከላከያ – የመስታዋት/የፕላስቲክ መከላከያ ግድግዳ ምርት እና ዋጋቸው እንደጨመረ ነው። ለምሳሌ 1 ሜትር  በ 1 ሜትር የሆነው እስከ100 ዮሮ ይሸጣል።

 1. ትምህርት ቤቶች

ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት መከፈቱ ጥሩ እና አስፈላጊ እርምጃ ነው። ጀርመን ተማሪዎች ትምህርት ቤት የፊትለፊት ትምህርት በአካል በመገኘት ሲከታተሉ፣ የቀለም ትምሀርት ብቻ ሳይሆን ስፖርትም እንደገና ተጀምሯል። በጥንድ ሆነው የሚለማመዱ ከሆነም ሳይቀያየሩ ከጀመሩት ሰው ጋር ብቻ መለማመድ ይኖርባቸዋል። ዩኒቨርስቲዎች በአብዛኛው በዲጂታል ቴክኖሎጂ ትምህርት ሲያቀርቡ፣ ይህም ቀልጣፋ የሆነ ስርዓትን በመፍጠር አስፈላጊ ከሆነም በቀናት ውስጥ በአካል ቀርቦ የመከታተል አቅምንም አዳብረዋል። እንደየአስፈላጊነቱም መቀያየር ይቻላል። እዚህ ላይ እንደ ሃሳብ ለማቅረብ የምፈልገው የዲጂታል መዋቅሮችን በመጠቀም በውጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ምሁራን በፕሮፌሽናቸው ኢትዮጵያ ለሚገኙ ዩኒቨርስቲዎች እና ትምህርት ቤቶች በበጎ ፈቃደኝነት ትምህርቶችን፣ ሌክቸሮችን ማቅርብ እንዲያስችላቸው መልካም አጋጣሚ መፍጠር ጥሩ ይመስለኛል። ለእውቀት ሽግግርም ቀላል፣ ወጪና ጊዜን የሚያድን ትልቅ አስተዋፅኦ ነው።

 1.  ፊልም ቀረፃ

የፊልም ቀርፃ ምን እንደሚመስል በአሁኑ ሰዓት ከበርሊን ወደ ኮሎኝ ለሳምንታት በመሄድ በአንድ የጀርመን ፊልም ላይ እየተወነች  ካለችው ልጄ ልምድ ለመጥቀስ እወዳለሁ። ፊልሙ ወደሚቀረፅበት ከተማ ከመሄዷ 48 ሰዓት በፊት የኮሮና ምርመራ ማድረግ ነበረባት። በጉዞ ላይ K95 ወይም FFP2 ማስኮችን (ቬንትሌሽን የሌለው) ብቻ ማድረግ ግድ ነው። እንደደረሰችም/ ገና ከባቡር እንደወረደች ሌላ ምርመራ ማድርግ ሲገባት ከፊልሙ የቀን ተቀን ስክሪፕት እና የመተግበሪያ ሰነድ (call sheet) ጎንም በአባሪነት ለየቀኑ የኮሮና መከላከያ መደረግ ስለሚገባው እርምጃ የያዘ ፅሁፍ ይታደላል። ፕሮዳክሽኑም አንድ የኮሮና መከላከል ኦፊሰር መድቧል። ይህም የዳይሬክተሩን ትዕዛዝ ማቋረጥ ይችላል። ወደ ቀረፃ ቦታ (set) ሲገባም ሙቀት ይለካል፣ የመቅረጫ ቦታ ዝግ ከሆነ በየ45 ደቂቅም አየር ለ15 ደቂቃ ይናፈሳል። በመሃከሉ የእረፍት ቀን ካለ የኮሮና ምርመራ ይደረጋል። በአንድ ሳምንት ውስጥ ብቻ 3 ጊዜ የኮቪድ 19 ምርመራ አድርጋለች።  ፊልሙ ተቀርፆ እስኪያልቅም የምታደርገው ማህበራዊ ግንኙነት ከፊልሙ ክሪው ውጭ በቁጥር ከሚነገሩ የቤተሰብ አብላት ጋር ብቻ ይሆናል። ይህ የሚያሳየው አንድ ተዋናይ ወይም የክሪው አባል በወረርሽኙ ቢያዝ ሙሉ የፊልም ሂድቱ ስለሚቋርጥ እና ይህም ከፍተኛ አንፃራዊ ክስረት እንዳይፈጥር የሚረዳ የስጋት መከላከያ ስርዓትን ነው።

 1. መደምደሚያ

የኮሮና ወረርሽኝ በመጀመሪያ ወራቶች በይበልጥ የተስፋፋው ከመጓጓዣ ቦታ፣ ከተጨናነቁ ቦታዎች፣ በመዝናኝ ስፍራ ሲሆን ወደ ሰኔ አካባቢ ደግሞ ከስራ ስፍራዎች ነበር። በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ሰው የሚያዘው በግል አካባቢው፣ ከጓደኛ፣ ከቤተሰብ እየሆነ ነው፤ ቸልታም ዋናው መንሳኤ ነው። የላቦራቶሪ ናሙና ምርመራ አቅምን በማጎልበት በአንፃራዊ የሚጨምርውን ቁጥር ግልፅ የማድረግ ስርዓት ተፈጥሯል። ከተያዙትም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት የት እንደያዛቸው መከታተልም ተችሏል። ሁለተኛው ዙር ወረርሽኝ  በብዛት የያዛቸው የመከላከል እቅም ያላቸውን ወጣቶች እየሆነ በመምጣቱ እና የተሻለ ህክምና ማቅረብ በመቻሉ የሟች ቁጥር እንዲቀንስ ረድቷል።

የወረርሽኙን ስርጭት ለመከላከል  ርቀትን በመጠበቅ፣ ማስክ በማድረግ፣ የእጅን ንፅህና በመጠበቅ እና  አየር ማናፍስን በተመለከት ህዝቡ አቅም ገንብቷል፣ ተላምዷል፤ በአብዛኛውም ከስረዐቱ ጋር ተሳልጧል። መሰራት ያለበት ኃላፊነትን ያለ መንግስት መመሪያ እና ግዴታዎች መውሰድ እና ማጎልበት ላይ ነው።

የኢትዮጵያ ትልቁ እድል ከመጀመሪያው የወረርሽኙ ስርጭት ማዕበል ልምድ መቅሰም እንደተቻለ ሁሉ ከሁለተኛውም ማዕበል ልምዶችን በመቅሰም፣ የመከላከል መስርተ ልማትን ለማጠናከር መቻል ነው። የአስተሳሰብ እና የባህሪይ ለውጦችም፣ የግንዛቤ እድገቶች እየታዩ ነው። በዚህ አጋጣሚ በኢትዮጵያ የወጣው ህግ በጣም ጥሩ እርምጃ ነው።ለሌላ ሀገራት ምሳሌ ይሆናል። ይህንንም ህግ በየጊዜው ማሻሻል ያስፈልጋል። ለወደፊትም ወደ ኢንፌክሽን የመከላከል ህግ መቀየር ወይም ማስፋት ይቻላል።

ይህን ፅሁፍ ከጨረስኩ በኋላ ደጋግሜ ማስተካከል ነበረብኝ አሁንም ቢሆን በፅሁፉ ላይ ያሉ አህዞች እና እርምጃዎች በወረርሽኙ ባህርይ በቅፅበት ሊያረጁ እና ሊቀያየሩ እንደሚችሉ እንደምትረዱኝ ተስፋ አለኝ።

ለጀርመን እና የኢትዮጵያ የህክምና ባለሙያዎች እና ጤና ኢንስቲትዩት የተለመደውን ትልቅ ምስጋናዬን አቀርባልሁ።

ከመልካም የጤንነት ሰላምታ ጋር
ፀጋዬ ደግነህ (ዶ/ር)

Dr. Tsegaye Degineh
Berlin, Germany

——

Email: mail@degineh.de

Website: www.degineh.com

Twitter: @TsegayeD4
Facebook: fam.degineh

1 Comment

 1. Ayi Dr. Tsegay

  It is not corona which is committing Amara genocide. Can you write something about Amara genocide if you really care about human life?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.

This site uses Akismet to reduce spam. Learn how your comment data is processed.